ከህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
«ዝምታችንን አትፈታተኑት!»
ረቡዕ ጥር 22/2011 አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ያለፈ በደል እያነሳን የምንቆዝምበት ዘመን ከተገባደደ ዓመታት ተቆጥረዋል። ነገር ግን ዛሬም ወደኋላ ሊጎትቱን የሚሹ የውስጥና የውጭ አካላት አሳፋሪ ሙከራዎችን ሲያደርጉ እያየን እንገኛለን። ለአገሪቱ ለውጥ ፋና ወጊ የሆነው ህዝበ ሙስሊም ይህንን በፍጹም አይቀበልም። ለአገሪቱ ወጣች የምትባል የትኛዋም የለውጥ ጸሃይ ህዝበ ሙስሊሙንም ትመለከታለች። እንደማትመለከት ለማስመሰል የሚደረግ ማንኛውም ጥረትም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ አያጠራጥርም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእምነት ተቋም ግንባታን ማሳለጥ የሚገባው መንግስት ቢሆንም በአዲስ አበባ እና በአካባቢዋ የሚገኙ የእምነት ተቋሞቻችንን «ህገ ወጥ» በሚል ሽፋን በተጠና መልኩ በዘመቻ የማፍረስ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው። በህጋዊ መንገድ ተገነቡ የተባሉ የእምነት ተቋማት አሉ በማይባልባት አዲስ አበባ ባልተመጣጠነ ሁኔታ ተደሰቁው የሚገኙትን መስጊዶቻችንን ይባስ ብሎ ማፍረስ ዳግም ህዝበ ሙስሊሙን መተንኮስ ነው። ድርጊቱ እየተፈጸመ ያለው በአንዳንድ የመንግስት አካላት መሆኑ ሲታይ ደግሞ ዛሬም «የሃይማኖት አባት» እያሉ በቴሌቪዥን መስኮት ከማሳየት የዘለለ እኩልነት ስለመስፈኑ ዋስትና የሚሰጥ አይመስልም።
በተለያዩ ጊዜያት ሙስሊሙ በገዛ አገሩ የአኗኗር ሁኔታውንና ሃይማኖታዊ አስፈልጎቱን ያገናዘበ የአምልኮ እና የመቃብር ስፍራ እንዳያገኝ በማድረግ ስልታዊ በሆነ መልኩ በመከልከሉ ቦታ የማግኘት መብቱን በማጣት ለአምልኮ የማይመጥኑ ቦታዎችን በገንዘቡ እየገዛ እስከመጠቀም ደርሷል። ይህም ሆኖ ግን «ህገ ወጥ» እየተባለ ጥቃት ይፈጸምበታል። ቤተ አምልኮዎቹ ይፈርሳሉ። ምእመናን ይታሰራሉ። አካል ጉዳት ይደርስባቸዋል። ለህልፈተ-ህይወትም ይጋለጣሉ።
ህገ ወጥነት የሚደገፍ አይደለም። ነገር ግን በአገሪቱ ለቤተ እምነቶች ቦታ የሚያሰጥ ህግ በሌለበትና ህጉ ቢኖርም ያለአድልዎ ማስተናገድ በማይችልበት፣ በመስጊድነት የተያዙ በርካታ ትናንሽ ቦታዎችም ህጋዊ እንዳይደረጉ ሆን ተብሎ በሚቀረጽ ህግ በሚታገዱበት ከባቢ ውስጥ ህጋዊ አማራጮችን መከተል አልተቻለም። ይህም ሆኖ መስጊዶች ብቻ ከብዙ ህገ ወጥ የአምልኮ ቦታ ግንባታዎች መካከል ተለይተው የህገ ወጥነት ስያሜ እየተሰጣቸው እንዲፈርሱ እየተደረገ ነው። መስጊድ ማፍረስ እንደቀላል እና ተራ ነገር እንዲታይ የማድረግ ጥረት የሚመስሉ ተግባራትንም እየተመለከትን ነው።
እኒህ ተግባራት በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል። በመሆኑም ሙስሊሙን እርስ በርሱ እንዲጋጭ በማድረግ አጋጣሚውን ተጠቅሞ መስጊዶቹን ለመድፈር እና ለማስደፈር በየትኛውም አካል (እስካሁን የለውጥ ንፋስ ያልታየበትን መጅሊስ፣ አንዳንድ አመራሮቹን እና ደጋፊዎቹን ጨምሮ) የሚፈጸምን ተግባር ኮሚቴው በዝምታ የማያልፈው መሆኑን የሚመለከተው አካል ሁሉ እንዲገነዘብ እናሳስባለን! በተጨማሪም ውዲቷ አገራችን የሁላችንም እንደመሆኗ መጠን በእኩልነት የአምልኮ መፈጸሚያ እና የሃይማኖት ትምህርት መስጫ ተቋማቶቻችንን የምንገነባበት ቦታ በበቂ ሁኔታ ሊዘጋጅልን የሚገባ ሲሆን የሃይማኖት ተቋማትን የሚመለከቱ ህግጋትም የሙስሊሙን የእምነት ተቋማት ባህሪ እና ይዘት ግምት ውስጥ ባስገባ፣ ሙስሊሙንም ባሳተፈ መልኩ መቀረጽ እንዳለባቸው ለማሳሰብ እንወዳለን!
አላሁ አክበር!
የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ