የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የልዑካን ቡድን የተቃጠሉትን መስጊዶች ጎበኘ! ለአካባቢው ህዝብ አጋርነታቸውን ገልጸዋል! ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል! አርብ የካቲት 8/2011 ደቡብ ጎንደር/እስቴ
****
©ድምፃችን ይሰማ
የህዝበ ሙስሊሙ የመትፍሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የልዑካን ቡድን በደቡብ ጎንደር እስቴ የተቃጠሉትን ሁለት መስጊዶች ጎበኘ! በኮሚቴው ሊቀመንበር ኡስታዝ አቡበክር አህመድ፣ በታሪክ ምሁር አህመዲን ጀበል፣ በሸኽ ሱልጣን እና በኡስታዝ በድሩ ሁሴን የተወከለው የልዑካን ቡድን ሁለቱ መስጊዶች በሚገኙባቸው ቦታዎች ከማህበረሰቡ ጋር የተገናኘ ሲሆን ለአካባቢው ማህበረሰብ ያለውን አጋርነትም ገልጿል። ዘረፋ የተፈጸመባቸውን የንግድ ሱቆች በመጎብኘትም በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካላት እንዲያገግሙ እገዛ የማድረግን አስፈላጊነት ጠቁሟል።
የልዑካን ቡድኑ መስጊዶቹን በተሻለ መልኩ ለመገንባት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በሚችሉት ሁሉ ማገዝ የሁሉም አገር ወዳድ ዜጎች ኃላፊነት መሆኑን አያይዞ ያወሳ ሲሆን ለገንዘብ መዋጮ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ሁሉም የአቅሙን እንዲረዳ እና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪውን አስተላልፏል።
በተጨማሪም ቡድኑ ከክልሉ ፕሬዝደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር በስልክ ተገናኝቶ መነጋገሩ የታወቀ ሲሆን ከክልሉ የጸጥታ ኃላፊ ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋርም በግንባር ተገናኝቶ ተወያይቷል። የወንጀሉ ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ዛሬ ነገ የማይባል መንግስታዊ ኃላፊነት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቶ አሳስቧል። ከሌሎች የፖሊስ ኃላፊዎች ጋርም በስልክ ግንኙነት አድርጎ ጉብኝቱን በሰላም አጠናቅቆ ተመልሷል።
አላሁ አክበር!