በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ አስተባባሪነት የተዘጋጀ የኡለማዎች የስምምነት ሰነድ

በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ አስተባባሪነት የተዘጋጀ የኡለማዎች የስምምነት ሰነድ (ለተጨማሪ ውይይት የቀረበ) 
******************************
ክፍል ሁለት(የቀጠለ)
I. ለሊቃውንቱ (ለዓሊሞች) ስምምነት የቀረቡ ነጥቦች፣ 
1. የእስልምና የኢማን (ተውሂድና አቂዳ) ምንጮችና መሠረቶች እንደ ቅደም ተከተላቸዉ ቁርኣን፣ ሀዲስ (ሱና) እና ኢጅማዕ መሆናቸውን እናፀናለን፤

2. የእስልምና ሕግጋት (አህካም) ዋነኛ ምንጮችና መሠረቶች እንደ ቅደም ተከተላቸዉ ቁርኣን፣ ሀዲስ (ሱና)፣ኢጅማዕ እና ቂያስ መሆናቸውን እናፀናለን፤

3. የነቢዩን ሶሀባዎች፣ የአማኞችን እናቶች እንወዳለን፡፡ ከነርሱ በኋላ የመጡና እነርሱን በቅንነት የተከተሉ ሙእሚኖችን (አላህ ስራቸውን ይውደድላቸው) ማለትም ታላላቅ መሪዎችን፣የዲናችንን ፉቀሀዎች ከመጀመሪያው ትውልድም ሆነ ከእነርሱ በኋላ የመጡትን በኪታብና ሱንና የጸኑትን የአህለ ሱንና ወል ጀማዓ ትውልዶችን ማለትም የሀዲስ አዋቂዎችን (ኡለማኡል ሀዲስ ወል አሰር)፣ የፊቂህና የተውሂድ ጽንሰ ሀሳብ (ነዞር) ዑለማዎችን፣ የዙህድ፣ የኢባዳ፣ የሱሉክ፣ የወረዕና ሀቅ ባለቤት የሆኑትን ደጋጎች በሙሉ እንወዳለን፡፡ ይህም አላህ (ሱ.ወ. ) በቁርአን እንድንከተለው ያዘዘዘው አቅጣጫ መሆኑን እንገነዘባለን፡-
“እነዚያም ከበኋላቸው የመጡት ጌታችን ሆይ ለኛም ለነዚያም በእምነት ለቀደሙን ወንድሞቻችን ምሕረት አድርግ፡፡ በልቦቻችንም ውስጥ ለነዚያ ለአመኑት (ሰዎች) ጥላቻን አታድርግ፡፡ ጌታችን ሆይ! አንተ ርኅሩኅ አዛኝ ነህና ይላሉ፡፡” (አል ሐሽር 10)

4. የአላህን አንድነትና የነብዩ ሙሐመድን (ሶ.ዐ.ወ.) መልዕክተኝነት የመሰከረንና ወደ ቂብላ ዞሮ የሚሰግድን (አህሉል ቂብላን) ሁሉ የሙስሊሙ ኡምማ አካል አድርገን እንቆጥራለን፣ ወዶና ፈቅዶ፣ እንዲሁም ከዚህ ኃይማኖት ሊያወጣው እንደሚችል አውቆና ተገንዝቦ ከኃይማኖቱ ለመውጣት በመወሰን ከእስልምና መውጣቱን በማያሻማ ሁኔታ በንግግር ወይም በተግባር ይፋ እስካላደረገና ድርጊቱም ውሳኔውን የማስተላለፍ ስልጣንና ብቃት ባላቸው የኡለማዎች ምክር ቤት ወይም የዓሊሞች መንፈሳዊ ሸንጎ እስካልተረጋገጠ ድረስ ከእስልምና እንደወጣ አንቆጥረውም፤ ከዚህ ውጭ በሆነ አግባብ በግለሰቦች ወይም በስብስቦች (ጀመዐዎች) የሚተላለፉ የማክፈር ወይም የፍንገጣ (ተፍሲቅ) እንዲሁም ፈሊጥ አውጭነት (ተብዲዕ) ብይኖች ተቀባይነት እንደሌላቸውና እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የፈፀመ ወገን (ወገኖች) ሊገሰፁ እንደሚገባም ተስማምተናል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በኡለማዎች የተቀመጡና ከእስልምና ሊያወጡ የሚችሉ ሸሪዓዊ መርሆዎች (ዶዋቢጥ አትተክፊር) በተጠበቀበት ሁኔታ ክህደት ሲፈጸም በዝምታ የማይታለፍ መሆኑን፤ የኡለማዎች ምክር ቤትም እርምት እንዲደረግ ተገቢውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበት ተስማምተናል፡፡

5. በቁርኣንና በሀዲስ ለሠፈሩ ዕምነት ነክ (ዐቂዳ) አናቅፅና ድንጋጌዎች እንዲሁም ሕግ ነክ /አህካም/ ጉዳዮች በአራቱ የሸሪዓ ሕግ አረዳድ መስመሮች (መዛሂበል አርበዐ) ማለትም በሀነፍይ፣በሻፊዒይ፣በማሊክይና በሀንበልይ መዝሀቦች ወይም በብዙሀን ዓሊሞቻቸው (ጁምሁር) የተሰጡ ትንታኔዎችን በዋነኛነት የምንቀበል ሲሆን፣የነዚህ መዝሀቦችና የብዙሀን ዓሊሞቻቸው ሕግ ነክና ዕምነት ነክ አስተያየቶችና አቋሞች ለሕዝበ ሙስሊሙ አንድነት መሠረት መሆናቸውን በማረጋገጥ ሕዝባችንን በነዚህ መዝሀቦች አስተምህሮት አግባብ ለመምራትም ቃል እንገባለን፤

6. ቁርኣንና ሐዲስን መሰረት በማድረግ አራቱ መዝሀቦች ወይም በየዘመናቱ የተነሱ ዕውቅ ዓሊሞቻቸው በአንድ ድምፅና በስምምነት ያወገዙትን አዲስ ነገር /ቢድዐ/ ውድቅ እናደርጋለን፤መዝሀቦች ወይም ብቃታቸው በየመዝሀቦቹ የዒልም መመዘኛ የተረጋገጠላቸው ዓሊሞች በሀሳብ የተለያዩበትን ግን አንዱ ሌላውን ሊነቅፍና ሊያወግዝ እንደማይገባ ተስማምተናል፡፡ ሆኖም ቀርኣንና ሀዲስን መሰረት በማድረግ ለኃይማኖታዊ ታሪካችን፣እንዲሁም ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ ለመጡ ኃይማኖታዊ እሴቶቻችንና ባህላችን ይበልጥ ቀረብ ያሉትንና ከመረጃ አኳያም ጠንከር ያለ ዋቢ ያላቸውን እናበረታታለን፤

7. በየዘመናቱ የነበሩ ዓሊሞቻችን በርካታ ጉዳዮችን ፈትሸው መፍትሄ ያበጁላቸዉ እንደመሆናቸው ኃይማኖታዊ ትንታኔ ለሚሹ ጉዳዮች ከቁርኣንና ሱንና፤ ከነቢዩ አስሀባዎች ብይኖች እንዲሁም በአራቱ መዝሀቦች ዓሊሞች ከተደራጁ ኪታቦች መፍትሄ የምናገኝ መሆኑን እናምናለን፡፡ በተጨማሪም ኢስላም ሁሉንም የሕይወት ዘርፎች የሚመለከቱ፣እንዲሁም ለሁሉም ዘመናትና ቦታዎች የሚበጁ ህግጋትን፣ትምህርቶችንና መመሪያዎችን በውስጡ የያዘ ኃይማኖት እንደመሆኑና ተልዕኮውም ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ስኬትን ማጎናፀፍ ከመሆኑ አኳያ ጥንት ያልነበሩ አዳዲስ ነገሮች በየዘመኑ መከሰታቸው የማይቀር በመሆኑ የምርምር (ኢጅቲሀድ) በር ምንጊዜም ክፍት እንደሆነ እያፀናን ልዩ ምርምሮች መካሄድ ያለባቸውም የጥንት ዓሊሞችን መሠረታዊ የትንታኔ ስልት (ኡሱል አል ፊቅህ ወቀዋዒድ አል ፊቅሂያ) በተከተለ መልኩና ለምርምር ብቁ በሆኑ ሊቃውንት ብቻ መሆኑን እናሰምርበታለን፡፡ በዚሁ አግባብ የተደራጁ የምርምር ውጤቶችንም የፈትዋዎቻችንና ያስተምህሮዎቻችን ግብአቶች እናደርጋለን፡፡

8. የእውቀትና የሥነ ምግባር ይዞታቸው አስተማማኝ ካልሆኑ ግለሰቦች የሚመነጩ፣እንዲሁም የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘቡ ፈተዋዎች በህዝባችን ላይ የሚያስከትሉትን መንፈሳዊና ዓለማዊ ጉዳት ለመከላከል ሲባል የሕዝባችንን ታሪካዊ፣ባህላዊና ሥነልቦናዊ ሥሪት ያገናዘበና በብቁ ዓሊሞች ብቻ የሚሰጥ የፈትዋ ሥርዓት መዘርጋት ግዴታችን መሆኑን ተቀብለናል፡፡ እውን ይሆን ዘንድም ተገቢውን ሁሉ ጥረትና ትብብር እናደርጋለን፡፡

9. ማንኛውም ሙስሊም ወይም ስብስብ/ጀመዓ/ የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ካለበት ኃላፊነት እና በዚህም አቅጣጫ ሊወጣው ከሚገባው ግዴታ ጋር በማይጋጭ መልኩና ሥርዓት በኢስላም ታሪክ ውስጥ አፈንጋጭ ተብለው ከተፈረጁት መስመሮች ውጭ ትክክል ነው ብሎ የመረጠውን አተያይ (ተያር) ለመማር፣ ለማስተማር ወይም ለመተግበር ያለውን ነጻነት እናከብራለን፡፡ በተለያዩ የፊቅህ መዝሀቦች መካከል የሚስተዋለው የአተያይና የብይን ብሎም የአፈጻጸም ፊቅሀዊ ልዩነት በሸሪዓው ተቀባይነት ያለውና ለመለያየትም ምክንያት ሊሆን የማይገባ መሆኑን እናምናለን፤ስለዚህም በየትኛውም ጉዳይ የየትኛውንም መዝሀብ ብይን የተከተለ ሙስሊም ድርጊቱ ከሕገ-ሸሪዓ አኳያ ተቀባይነት ያለው መሆኑን እናምናለን፤

10. በኃይማኖት ጉዳዮች ዙሪያ የሀገራችን ህዝበ ሙስሊም ተውሂዱን አጠንክሮ ፣ ለሺርክ ከሚዳርጉ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ታቅቦ መኖር ኃይማኖታዊ ግዴታው መሆኑን ይበልጥ እንዲያውቅና እንዲተገብር ማስተማርና ማብቃት የዓሊሞች የነፍስ ወከፍና የጋራ ኃላፊነት መሆኑን እናጸናለን፡፡ በአቂዳ ዙሪያ የተነሱ የተለያዩ አስተሳሰቦችን እናቅፋለን፤ በዚህ ረገድ ግለሰባዊና ስብስባዊ መብቶችን የማክበር አቅጣጫን እንከተላለን፡፡ አንዱ ወገን ሌላውን ማክፈርም ተገቢ መንገድ እንዳልሆነ ተስማምተናል፡፡ መጅሊስም ሆነ የኡለማ ምክር ቤት ልዩነት ባላቸው የአቂዳ ጉዳዮች የአንድ ወገንን እሳቤ ብቻ እንደማያስተናግዱም ተስማምተናል፡፡


11. የዓሊሞቻችን ብቃትና ደረጃ ለመመዘን የሚያስችል ግልጽና ጠንካራ መስፈርት እንዲደራጅና ምዘናውም በቁርአን፣በሀዲስ፣ በተውሂድ፣ በፊቅህ፣ በአረብኛ ሰዋሰው፣ በአሱለል ፊቅህና በላጋ እውቀት ላይ በተመሰረተ አግባብ እንዲከናወን ተስማምተናል፡፡ እንደ ግለሰቡ የሥራ ድርሻም መስፈርቱ ከላይ ከተጠቀሱት ዘርፎች ሙሉ በሙሉ፣ አብዛኛውን ወይም ከፊሉን የሚያካትትበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚገባ ተስማምተናል፡፡

12. ማንኛውም ግለሰብ ወይም ስብስብ የአመለካከት ወይም የአስተያየት ልዩነቶች ባሉባቸው ጥያቄዎችና ነጥቦች ዙሪያ ተገቢ ምሁራዊ ትንተናና ግንዛቤን ከማስጨበጥ እንዲሁም የእውቀት ክፍተትን ከመሙላት በዘለለ ሁናቴ ቡድነኝነትን መሰረት ያደረጉ፣ ስድብና ውግዘትን የቀላቀሉ መግለጫዎችን፣ፍረጃዎችንና ከፋፋይ ወገንተኛነትን የሚያራምዱ ቅስቀሳዎችን ከማድረግ፣በዚሁ አፍራሽ መንገድም ጽሁፎችን ከመበተን እንዲቆጠብ ማስተማርና መምከር የዓሊሞች ኃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን አምነን ተቀብለናል፡፡

13. በዓሊሞች፣ በዳዒዎችና በሀገር ሽማግሌዎች ላይ መልካም ስምን የማጥፋት፣ ከኃይማኖት ክልል የማስወጣት (ተክፊር) አቋም የሚወስዱ፣ የቆየ የመዝሀብ ልዩነት (ኺላፍ) እንዳለባቸው በሚታወቁ ጉዳዮች ላይ አል ሙኸተለፉ ፊሂ ላ ዩንከር (ብዝሀ ሀሳብ የተነሳበት ጉዳይ አይወገዝም) የሚለውን ነባር መርህ በተደጋጋሚ የሚጥሱ ግለሰቦች ወይም ወገኖች ወደፊት በሚቋቋመው አካታች የኡለማ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ወይም መንፈሳዊ ሸንጎ ቀርበው ጉዳያቸው እንዲታይና አስፈላጊው ፍትሀዊ ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው ለማድረግ ተስማምተናል፡፡ አፈጻጸሙ በእስልምና የጸደቀውን የማሰብ ነጻነት በማይቃረንና ሰፊውን ሙስሊም ማህበረሰብ የማስተማርን አላማ በሚያሳካ መልኩ እንዲሆን አስፈላጊው ሁሉ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡

14. በሀገራችን የእስልምና ቅብብሎሽ ውስጥ ወሳኝ ሚና ሲጫወቱ የኖሩ የሀገራችን ዑለማዎችንና ሸሆችን ውለታ ምንጊዜም አንዘነጋም፤ መልካም ሥራቸውንና አርአያቸውን ለመከተል እንተጋለን፤ ታሪካቸውን እናስታውሳለን፤ በበጎ እናስባቸዋለን፤ ለአዲሱ ትውልድም ይህንኑ በፅናት እናስተምራለን፡፡ ለእነኝህ የሀገራችን ዓሊሞች መፍለቂያ የሆኑትና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለብዙ ክፍለ ዘመናት ህብረተሰቡን ሲያገለግሉ የቆዩ ኢስላማዊ የትምህርት ተቋማት ዛሬም እንደጥንቱ የእውቀት ማዕድ ሆነው እንዲቀጥሉ ለማስቻል በትጋት እንሰራለን፡፡ ለዚህም የፌዴራልና የክልል እስልምና ጉዳይ ምክር ቤቶች፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች የየበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ማስቻል የወቅቱ ኃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን ተስማምተንበታል፡፡

ይቀጥላል.....

Leave a comment

All comments are moderated before being published