ይድረስ ለመጅሊሳችን ከበድር ኢትዮጵያ

ይድረስ ለመጅሊሳችን ከበድር ኢትዮጵያ

  የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለመብት ፤ ለእኩልነት፤ ለህገ መንግስት መከበር ያደረጉት እልህ አስጨራሽ መጠነ ሰፊ የትግል እንቅስቃሴ ባደረጉበት ወቅት ሁሉ እንግልት፤ እስር፤ የአካል ጉዳት ፤ ስደት እና የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸዉ ከታሪክም ሆነ ከቅርብ ጊዜ ትዝታ የምንገነዘበዉ ሀቅ ነዉ። በነዚህ መራር ሂደቶችም ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንግቦ ከመነሳት አልታቀበም ።

   በሀገራችን በተገኘዉ አንጻራዊ ለዉጥ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዘመናት የተጋረጡበትን ችግሮች ደረጃ በደረጃ አቅም በፈቀደ መልኩ መፍትሄ እንዲያገኙ ዘላቂ ትግል ማድረግ ሲገባን በራሳችን በኩል በተፈጠሩ ጥቃቅን የአመለካከት ልዩነቶች ሳቢያ አንድ ሆነን ባለመጓዝ በለዉጡ በአግባቡ ለመጠቀም አልቻልንም።            

   የመጅሊሱ አወቃቀር ለዉጤት ሲበቃ ከተቋሙ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ያላቸዉ ችግሮችም አብረዉ ይቀረፋሉ ብሎ የሚተማመነዉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በጉጉት ከሚጠብቃቸዉ መሰል ተግባራቶች የተቋሙ በአዋጅ መጽደቅና በየ እርከኑ የሚገኙ የአመራር አካላትን ምርጫ አፈጻጸም ተንጠልጥለዉ መገኘት የቀደምት ችግሮቹ ባሉበት እንዲቆዩ ምክንያት የሆናቸዉ መሆኑ ለመገንዘብ ያስችላል።      

   ከፍ ወደ አለ ድል ያሸጋግራሉ በሚል ተስፋ የተጣለባቸዉ ኡለማዎቻችን ከዉስጥ እና ከዉጭ አካላት ባለባቸዉ ጫና በጥቃቅን ጉዳዮች አለመግባባት ብሎም ተናበዉ አለመስራት በፈጠረዉ የአካሄድ ልዩነት በሀገር ዉስጥ እና ከሀገር ዉጭ የምንገኝ ሙስሊሞችን ያሳዘነ አቢይ ጉዳይ መሆኑም ለመግለጽ እንወዳለን ።

  የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም ካለበት ሰፊ ሀላፊነት እና ከተጣለበት የሙስሊሙ ማህበረሰብ አደራ አኳያ የተጋረጡ ችግሮችን በመለየት ከየእርከኑ ካሉ ተቋማት ብሎም የአመራር አካላት ጋር በሰከነ መንፈስ በዉይይት ችግሮቹን በመፍታት አንድነታችንን ማደስ የግድ ይላልና ቅድሚያ ተሰጥቶት ያሉትን ዉዥንብሮች የማጥራት ስራ እንዲሰራ በህዝበ ሙስሊሙ ስም እየጠየቅን በተገኙ እድሎችም ሳንጠቀም በሂደቶች ያለ አግባብ መጓተታቸዉ ሳቢያ ቢደናቀፉ ሁላችንም በአላህ (ሱወ) ዘንድ ተጠያቂ መሆናችንንም አንርሳ።         

     ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት የህዝበ ሙስሊሙ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴም በሁለንተናዊ መልኩ መጠበቅና የተቋማዊ ለዉጡ ለስኬት እስኪበቃም ድረስ የሚመለከታቸዉ አካላት ሁሉ ሀላፊነት እንዳለባቸዉ የሚታመን ሲሆን በተለይ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትም ሆነ ዘጠኙ የጋራ ኮሚቴ አባላት በመጅሊሱ አካባቢ ላሉ የአመራር አካላት በቂ ሙያዊ እገዛና ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል የሚል እምነትም አለን።

አላሁ አክበር

በድር ኢትዮጵያ     ሰሜን አሜሪካ    ጁን 7 2020                            

Leave a comment

All comments are moderated before being published