የበድር ኢትዮጵያ የጉባኤ የአቋም መግለጫ

በድር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት በ2018 በሰላም ፋዉንዴሽን ኮምዩኒቲ አዘጋጅነት ከጁላይ 26 እስከ 29 በተካሄደዉ 18 ኛዉ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዶክተር አቢይ አህመድ ፤ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር የክቡር ዶክትሬት አቶ ለማ መገርሳ እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እና ኢንጂነር በድሩ ሁሴን ሌሎችም ዉድና የተከበሩ ኡስታዞቻችን በተሳተፉበት በዚሁ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ የተሰጡ ትምህርቶች እና የተላለፉ የመፍትሄ ሀሳቦችን ግምት ዉስጥ በማስገባት በጉባኤዉ ማጠቃለያ የሚከተለዉን ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በጋራ አዉጥተናል።

1. ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አቢይ አህመድ አሊ እና አመራራቸዉ በሚተገብሩት ፈጣን የለዉጥ ሂደት ሀገራችን ወደ ተሻለ ሰላምና እድገት ጎዳና በማምራት ላይ የምትገኝ በመሆኗ በማህበራሰባችን ዉስጥ የፈጠረዉን ከፍተኛ ተነሳሽነት በቀጣይነት እንዲዘልቅ በነፍሰ ወከፍ ማድረግ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችን እንዲሁም ከክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አቢይ አህመድ የለዉጥ ሂደት ጎን መቆማችንን እናረጋግጠለን፤

2. የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች የእምነት ነጻነትና ህገ መንስታዊ የመብት ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የህዝበ ሙስሊሙን መሰረታዊ ጥያቄዎችን አንግበዉ ከተነሱበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እያደረጉት ያለዉ እልህ አስጨራሽ ሰላማዊ የትግል ተጋድሎ እና ያስመዘገቡት ዉጤት እንዲሁም በቀጣይ ሊመጣ የሚችለዉን በጎ ተግባር ተዳምሮ ሲመዘን ላበረከቱት አስተዋጾ እና ለከፈሉት መስዋእትነት ምስጋናችን የላቀ መሆኑና ምን ጊዜም ከጎናቸዉ መሆናችንን ዳግም እናረጋግጣለን ፤

3. በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አቢይ አህመድ በተመራዉ ስብሰባ በሀገራችን በህዝበ ሙስሊሙ መካከል ያለዉን ልዩነት ለመፍታት እንዲቻል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ የተደረሰበትን የዉሳኔ ሀሳብ በሙሉ ልብ በመቀበል ለስኬቱ የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን ፤

4. በሀገራችን በጸደቀዉ ህገ መንግስት በሚፈቅደዉ መሰረት የእምነት ነጻነት መከበርን በሚያበስረዉ አንቃጽ ተንተርሶ በአክሱም የሚገኙ ሙስሊም ማህበረሰቦች ለዘመናት ያጋጠማቸዉን ኢፍትሀዊ በደል ተቀርፎ ህገ መንግስታዊ መብታቸዉ ለማስከበር የመስጂዶችና የመቃብር ቦታ ጥያቄያቸዉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለዉጤት እንዲበቁ በጽኑ የምንደግፋቸዉ መሆኑን እናረጋግጣለን ፤

5. የሙስሊሙን ማህበረሰብ ያሳተፈ ብሎም ወጥነት ያለዉ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሀገሪቱ ለመተግበር እንዲቻል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያሳድግ በሚችል መልኩ እስላማዊ ባንክ ሊኖር እንደሚገባና በመንግስት በኩልም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተፈጻሚ እንዲሆን የማመቻቸቱ ስራ ሊታሰብበት እንደሚገባ እየጠቆምን ከሙስሊሙ ማህበርሰብ መሰራታዊ ጥያቄዎቻችን ዉስጥ አንዱ እንደመሆኑ መጠን በሙሉ ተስፋ እንደሚፈቀድ በመተማመን ዳግም ጥያቄያችንን ከፍ አድርገን በማንሳት እናረጋግጣለን፤

6. በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ ሙስሊም ማህበረሰብ ራሳችንን ከምንጊዜዉም በተሻለ ደረጃ በማጠናከር አቅማችን በፈቀደዉ መጠን ሁሉ በሀገር ቤት የሚደረገዉን የለዉጥ እንቅስቃሴ እንደግፋለን ፤

7. በድር ኢትዮጵያ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር በዲያስፖራ የምንገኝ ኢትዮጵያዉያንን ማቀራረብ፤ ማደራጀት ብሎም ኮምዩኒቲዎች የራሳቸዉ የሆነ ተቋም እንዲኖራቸዉ በማስቻል በኩል ሊጫወት የሚገባዉን ሚና ካሳለፍናቸዉ ጊዜያት በተሻለ ደረጃ ለማሳደግና መሰረታዊ ለዉጥ ለማምጣት በኮምዩኒቲዎች ላይ ሀይላችንን አስተባብረን መስራት ፤

8. ከእኛነታችን መገለጫዎች አንዱ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለሌላው ሙስሊም ወንድም መሆኑን በተግባር ማሳየት ስለሚጠበቅብን ያለፉትን ልዩነቶች በይቅርታ በማለፍ እንደጊዜው በፍቅር ተዳምረን መጓዝ ስለሚጠበቅብን በአላህ ፈቃድ አንድነታችንን ጠብቀን ለዉጤት ለማብቃት ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን ፤

9. በሴቶች እና በወጣቶች በኩል ያላቸዉን ብቃት በእግባቡ ለመጠቀም እንዲቻል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከፍ ወደ አለ ደረጃ ለማሸጋገር ይሰራበታል።

በድር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት 
ጁላይ 29 , 2018 ሰላም ፋዉንዴሽን , ቨርጂኒያ

Leave a comment

All comments are moderated before being published