Ramadan Mubarak

April 1, 2022

እንኳን ለረመዳን ወር በሰላም አደረሳችሁ!

 

﴾يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ ‎﴿

እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡ (183)

በድር ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት እንኳንም ለኸይረኛው የረመዳን ወር በሰላም አደረሳችሁ ፣በማለት መልካም ምኞቱን ይገልፃል።

ይህ ወር የጀሃነም በር ተዘግቶ የጀነት በር የሚከፈትበት ፣ ሸይጧን የሚታሰርበት ወር እንደመሆኑ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የሰጠንን መልካም እድል በመጠቀም ወደ አላህ የሚያቀራርቡንን መልካም ሥራዎች በመከወን አላህም ፆማችንን፣ዒባዳችንን፣ኸይር ሥራዎቻችንን እንዲቀበለን እንለምነዋለን።

አላህ ይህን ወር አገራችን ላይ እያንዣበቡ ያለውን አደጋ በቃ የሚልበት፣ በዲን እውቀት አንቱ የተባሉ መሻይኾቻችንም የመጅሊሱን ጉዳይ በጉጉት እየጠበቀ ያለው ሙስሊሙ ህብረተሰብ ቅስሙ እንዳይሰበር፣ በመካከላቸው፣ ያሉ ልዩነቶችን አጥበው ወደ አንድነት መጥተው የኡማውን ህልምና ምኞት እዉን ለማድረግ በዚህ የራህመት ወር ከአላህ በታች የቻሉትን በማድረግ ተግተው እንዲሰሩ በአክብሮት እንጠይቃለን ።

በዚህ አጋጣሚም በድር ኢትዮጵያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ፣ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው እየተከሰተ ባለው የኑሮ ውድነት ሳቢያ፣ እየተጨናነቁ ያሉ የህብረተሰብ አባላትን በመደገፍ አለኝታ እንሁናቸው ይላል።

ድርጅታችን በድር ኢትዮጵያ የዘንድሮውን አመታዊ ጉባኤውን July 15-25,2022 በአዲስ አበባ እንደሚያደርግ ከወራት በፊት በመገናኛ ብዙሃን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በበድር ታሪክም የዘንድሮውን ሃያ ሁለተኛ አመታዊ ጉባኤም ለየት የሚያደርገው ለመጀመሪያ ጊዜ በሃገራችን ላይ መደረጉ ሲሆን ይህን እድል የሰጠንን ጌታ እያመሰገን፣ጉባኤውን በጋራ የምንሳተፍበት ለየት ያለ ልምድና ግንዛቤ የምንቀስምበት እንዲያደርግልንም አላህን አጥብቀን እንለምነዋለን።

 

በድር ኢትዮጵያ ሰሜን አሜሪካ

Leave a comment

All comments are moderated before being published