ጥንቃቄ የሚያሻዉ ጦርነት

ጥንቃቄ የሚያሻዉ ጦርነት

     ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ የጦርነት ታሪኮችን ያሳለፈች ስትሆን በጦርነቱም የበርካታ ጀግኖች ዜጎቻችን ሀይወት ማለፉ የማይዘንጋ ነዉ። ጦርነቶች ሁሉም የራሳቸዉ ዓላማና ባህሪ ቢኖራቸዉም ከሚያደርሱት የኢኮኖሚ ዉድቀት እና የሰዉ ህይወትን መቅጠፍ ተዳምሮ በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ቀዉስ እንደሚፈጥር ይታወቃል።   

      በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በተከፈተዉ ጥቃት ሳቢያ እንደተቀሰቀሰ የሚነገረዉ ይኸዉ ጦርነት ልዩ የሚያደርገዉ በዝሆኖች ጥልም ሆነ ፍቅር የሚጎዳዉ ሳሩ ነዉ እንደሚባለዉ ሁሉ ሁለቱም የአንድ ሉዐላዊ ሀገር ዜጎች በመሆናቸዉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሊደርስ የሚችለዉ ጥቃት ህብረተሰቡን በከፍተኛ ሀሳብ ዉስጥ እንደተከተተዉ ይታወቃል።

   በድር ኢትዮጵያም በሀገራችን የተከሰተዉ ጦርነት በዚህ መልኩ መፈጸሙ እጅጉን እያሳሰበዉ በተለይ ሰዉ ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በተጋራጡበት በዚህ ወሳኝ ወቅት በተጨማሪነት ጦርነትን ማስተናገድ ችግሩን ምን ያህል ዉስብስብና የከፋ እንደሚያደርገዉ ከማንም የተሰወረ እንደማይሆን እናምናለን።   

   የሆነዉ ሆኖ ሁለቱም አካላት ህወሀትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ከምንም ነገር በላይ ለንጹሀን ዜጎች ደህንነት ብሎም በጦርነቱ በሁለቱም ወገን ህይወታቸዉን የሚያጡ አካላት የኛዉ ዜጎች በመሆናቸዉ አፈጻጸሙ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለመቋጨት ብሎም ራስን በመግዛት ለሀገር አንድነት እና ለዜጎች ክብር ሲባል ፈጣን መፍትሄ እንደሚሻም እንጠቁማለን።

   በመጨረሻም ህብረተሰቡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሚሰነዘሩ ሀሳቦች (ያልተረጋገጡ ወሬዎች) ሳይሸበር ሁኔታዉን በትዕግስት እንዲከታተልና ተአማኒነታቸዉንም ሊያረጋገጥ እንደሚገባ አበክረን እያሳሰብን በዋነኛነት ከሃላፊነት አንጻር በማዕከላዊ መንግስት በኩል ትልቅ የማስተዋል ጥበብ ይጠይቃልና የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ለሚወድመዉ ንብረትም ሆነ መስዋዕት ለሚሆኑ ዜጎች ከለላ ሊሆን እንደሚገባዉ እየገለጽን ማህበረሰባችንም የጦርነትን አስከፊነት ተገንዝቦ በያለበት በዱዐ (በጸሎት) እንዲበረታታና ሀገራችንን አላህ ሰላም ያደርጋት ዘንድ የበኩሉን እንዲወጣ እንጠይቃለን።

 አላህ (ሱብሁዋነሁ ወተአላ) ሀገራችንና ህዝቦቿን ይጠብቅልን አሜን !

በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ    ኖቨምበር 8 2020

Leave a comment

All comments are moderated before being published