የአክሱም ሙስሊሞች ህገ መንግስታዊ ጥያቄ !!!

የአክሱም ሙስሊሞች ህገ መንግስታዊ ጥያቄ !!!

እምነት የግለሰቦች ስጦታ አይደለም ፤ በነሱ ፍላጎትም አይመራም

   የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለበርካታ ዘመናት በአጼዎች አገዛዝ ለግፍ ተዳርገዋል። አንዱ ከአንዱ ምንም በማይሻልበት መልኩም ተፈራርቀዉበታል። በነዚሁ በርካታ ዓመታት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዉጥን በመናፈቅ ችሉ ለመኖር ቢጥርም ሰብዐዊ መብቱን ነፍገዉ ፤ በትዉልድ ሀገሩ እንደ ዉጭ ዜጋ ተቆጥሮ ፤ ሁለንተናዊ ክብሩ ተደፍሮ የግፍ ጫንቃዉ በላዩ ላይ ተጭኖ ከትዉልድ ትዉልድ ተሸጋግሮዋል። በነዚህ ዘመናትም መብቱን ለማስከበር የተቻለዉን ሁሉ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም በተለይ ከ1966 ዓ ል ጀምሮ በተደረገዉ ያልተቋረጠ እንቅስቃሴ መጠነኛ ዉጤት በደርግ አገዛዝ ወቅት ቢታይም ዘላቂነትን ግን ሊያገኝ አልቻለም ።  

    የኢህአዲግ መንግስትም እንደ አመጣጡ ለመብት፤ ለህገመንግስት መከበርና ለእምነት ነፃነት እታገላለሁ ብሎ ባወጀዉ መሰረት በህብረተሰቡ ዘንድ ያለፉትን የጭቆና ጊዜያትን በማሰብ የተሻለ ሊሆን ይችላል ከሚል እሳቤ በትእግስት ቢጠብቅም መልኩን ቀይሮ ከማጡ ወደ ድጡ ሆነ። ለመጀመሪያ ጊዜ መላዉ የሀገሪቱን ሙስሊም ማህበረሰብ ባደራጀና ባሳተፈ መልኩ የመፍትሄ አፈላአልጊ ኮሚቴን በማዋቀር ሰላማዊ የመብት እንቅስቃሴ ላለፉት ሰባት ዓመታት በቆራጥነት ሰፊ ትግል አካሂዷል። ዉጤቱም በመላ አገራዊ ለዉጥ ፈርቀዳጅ በመሆን መሰረታዊ አሻራ ጥሎ ማለፉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነዉ።

    ሀገራዊ ለዉጡን ተከትሎ ህዝባችን ለረጅም ጊዜ ያጣቸዉን የህገ መንግስት መከበር ፤ የመብት ረገጣ ፤ እምነትን በነጻነት ማክበርና የመሳሰሉ ሂደቶች ፍሬያቸዉ አብቦ ለማየት በሚጓጓበት በዚህ ወሳኝ ጊዜ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የአክሱም ሙስሊሞች የረጅም ጊዜ ጥያቄን አስመልክቶ ሲናገሩ የትግራይ ሙስሊም እስከዛሬ መስጂድ አልነበረዉም አሁን ለምን ? የትግራይ ክልል ሙስሊሞች ከእምነታቸዉ ይልቅ ትግሬነታቸዉን አብልጠዉ መቀበል እንዳለባቸዉ መናገራቸዉ ሙስሊሙን ህብረተሰብ መናቅ ብቻ ሳይሆን በሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ወቅት ሙስሊሙ ማህበረሰብ የከፈለዉን መስዋእትነት ዋጋ እንደ ማሳጣት ይመስለናል ። ለመሆኑ የትግራይ ሙስሊም በትግል ወቅት መስዋእት አልሆነምን? መቀሌና አዲግራት ከፍታ ቦታዎች ላይ የተንጣለሉት መስቀሎችስ ድሮ ነበሩን? በሌላ መልኩ ለእድገት የሚታገሉ ከሆነ ትላንት ላልነበረዉ እድገት አሁን መሯሯጣቸዉ ምን ይሉት ይሆን? 

   በህይወታችን ትልቅ ቦታ የሚሰጠዉ “ እምነትን ” እንደ ተራ ነገር በመቁጠር ፤ ድሮ መስጂድ አልነበራቸዉምና አሁን ለምን አስፈለገ ? ወይንም ከእምነታቸዉ ይልቅ ለብሔራቸዉ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብሎ ማለት ከመሪዎች የሚጠበቅ አይደለም፤ በሌላ መልኩ  “እምነት የግለሰቦች ስጦታ አይደለም ፤ በነሱ ፍላጎትም አይመራም” እያልን ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከመቼዉም ይበልጥ በመደራጀት መብቱን ለማስከበር የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆን እንዳለበት እየጠቆምን በሚተላለፉ ሰበካዎች ሳይታለል አንድነቱን አጠናክሮ መጓዝ እንዳለበት አበክረን እናሳዉቃለን ።

አላሁ አክበር

      በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ     ኦክቶበር 30 2019                       

Leave a comment

All comments are moderated before being published