የአርቲስት ሀጭሉ ሁንዴሳን ግድያ አስመልክቶ የሀዘን መግለጫ

Posted by Badr Ethiopia on

የአርቲስት ሀጭሉ ሁንዴሳን ግድያ አስመልክቶ የሀዘን መግለጫ

    በሀገራችን የሰላም ጭላንጭሎች በተገኙባቸዉ አጋጣሚዎች ሁሉ የተለያዩ መሰናክሎችን በመፍጠር ሰላምን ለማጨናገፍ ብሎም እንደ ሀገር ቆማ እንዳትቀጥል የሚደረጉ ጥረቶች መበራከት እጅግ በጣም ከማሳዘን አልፎ ሀገራችን የለዉጥ ጎዞ ተጠቃሚ እንዳትሆን እያደረጋት ይገኛል።

   በትላንትናዉ እለት በግፍ የተገደለዉ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳም  በሀገሪቱ ለህገመንግስታዊ መከበር ከታገሉ ጀግኖች አንዱ ነበር። በግጥምና በሙዚቃ ስራዉ የሚታወቀዉ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በሀገሪቱ በተደረገዉ የለዉጥ እንቅስቃሴ አሻራዉን ያሳረፈ ታላቅ ዜጋ ነበር።

   ሰዎች ሰብዐዊና ህገመንግስታዊ መብታቸዉን ተጠቅመዉ ሀሳባቸዉና አመለካከታቸውን በመግለጻቸዉ ብቻ በህልዉናቸዉ ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈጸም የትግል አማራጭ ዉጤት አይደለምና ቆም ብለዉ ሊያስቡ የሚገባ ሲሆን ይህንን መሰል አስነዋሪ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ሁሉ የስነምግባር ጉድለት የተጸናወታቸዉም ናቸዉ።

   ይህን መሰል ድርጊቶች በታዋቂ እና ለሀገር ብዙ ይጠቅማሉ በሚባሉ አካላት ላይ ሆን ተብሎ ያነጣጠረ መሆኑ ሀገሪቱን ወደ ብጥብጥ እንድታመራ በማድረግ በህልዉናዋም ላይ አደጋ ለመደቀን እንደሆነ ግልጽ ማሳያ ነዉ፤ በተለይ በዚህ ወሳኝ ወቅት ሀገራችን ከታላቁ ህዳሴ ግድቡ ጋር በተገናኘ አጣብቂኝ ዉስጥ ባለችበት ሰዓት ይህን መሰል ፈተና በህዝቧ ላይ መጫን ለሀገር ግድየለሽነትን ያሳያል። መንግስት በጉዳዩ ላይ ከምንጊዜዉም በላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ገዳዮችን በአስቸኳይ ለፍርድ ሊያቀርብ ግድ ይለዋል።

    ለሟች አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ቤተሰቦችና መላዉ የሀገሪቱ ህዝብ መጽናናትን እየተመኘን በመሪር ሀዘን ዉስጥ ያላችሁ የሀገራችን ህዝቦችም በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠዉን አደጋ በጋራ በድል በመሻገር በሰከነ መንፈስ ሀገራዊ ግዴታችንን እንወጣ ዘንድ አላህን (ሱብሀነሁ ወተአላ) እንማጸናለን ።  

በድር ኢትዮጵያ   ሰሜን አሜሪካ   ጁን 30 2020


← Older Post Newer Post →