የአረብኛ ቋንቋም ይታሰብበት እንላለን

­­ የአረብኛ ቋንቋም ይታሰብበት እንላለን

     በሀገራችን እየተከናወኑ ያሉ ለዉጦች አበረታች ከመሆናቸዉ አልፎ እየታዩ ያሉ ተግባራትም ሊመሰገኑ ይገባል የሚል እምነት አለን ። በቅርቡ በተለያዩ ክልሎች በትምህርት ቤቶች ደረጃ ሊሰጡ ይገባሉ በሚል የተለያዩ የሀገር ዉስጥ እና የዉጭ ቋንቋዎችን በትምህርት ቤቶች ደረጃ ለመስጠት ቅድመ ሁኔታዎችን እያመቻቹ እንደሆነ መገለጻቸዉ ይታወቃል። ይህም ሂደት እጅግ በጣም አበረታች መሆኑን በመግለጽ ለአፈጻጸሙ ስኬታማነት ትኩረት ይሰጠዉ እንላለን ።

     በተጨማሪነት ይሰጣሉ ተብለዉ ከተጠቀሱ ቋንቋዎች በተጓዳኝ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል የምንለዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ የተናጋሪ ቁጥር ካላቸዉ ቋንቋዎች አንዱ የሆነዉ የአረብኛ ቋንቋ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ግን በተጨማሪነት ይሰጣሉ ተብለዉ ከተጠቀሱ ቋንቋዎች ዉስጥ አለመካተቱ እጅጉን አሳስቦናል።

   በተለይ በሀገራችን ዉስጥ በርካታ የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከመኖራቸዉ አንጻር ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪም ሆነ የዉጭ ባለሙያዎች ሳያስፈልግ እንዲሁም ለባለሙያ ስልጠናም ከፍተኛ ወጪ በማይጠይቅ ሁናቴ በቀላል ወጭ ፕሮግራሙን በሀገር በሚገኙ ባለሙያዎች ለማከናወን የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል። 

   በሌላ መልኩ የጎረቤት ሀገሮቻችን ሁሉም በሚባል ደረጃ የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ መሆናቸዉም ታሳቢ ሊሆን እንደሚገባ በማሳወቅ ሲሆን በቅርቡ ከአባይ ግድብ ጋር በተያያዥነት የተፈጠረዉን ሁሉም በግልጽ የሚረዳዉ መሆኑን እያስታወስን በሀገራችንም የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ቁጥር ቀላል የማይባል በመሆኑና በርካታ የስራ እድልንም በሀገር ዉስጥ ሊፈጥር የሚችል ስለሆነ በትምህርት ቤቶች ደረጃ የአረብኛ ቋንቋ በተጨማሪነት ሊሰጥ ስለሚገባ የሚመለከታቸዉ አካላት ትኩረት ሰጥተዉ ለዉጤት ያበቁት ዘንድ ስንጠቁም ለተፈጻሚነቱም በመተማመን ጭምር ነዉ። 

ፈጣሪ ሀገራችንን በሰላም ይጠብቅልን

በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ    ሴፕተምበር 26 2020                                       

Leave a comment

All comments are moderated before being published