የስም ለዉጡ እዉን ለምን አስፈለገ ?

የስም ለዉጡ እዉን ለምን አስፈለገ ?

     ለዘመናት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ችግር ሆኖ ከተጋረጡበት አንዱና ዋነኛዉ ጠንካራ የሆነ ተቋም አለመኖሩ ያስከተላቸዉ ዉስብስብ ችግሮች እንደሆኑ በመገንዘብ  በ 1966 እና በ 2004 የህዝበ ሙስሊሙ ሀገር አቀፍ ተቃዉሞ በጥቁቱ ማሳያዎች ናቸዉ። 

     በሀገሪቱ በተፈጠረዉ አንጻራዊ ለዉጥ በመንግስትም በኩል ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸዉ ብሎም  መስተካከል እንደሚገባቸዉ ከታመነባቸዉ ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) በመሆኑ አወቃቀሩን አስመልክቶ በአዲስ መልክ ለማደራጀት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ መልካም ፈቃድ ተጀምሮ በተዋቀረዉ የተቋማዊ ለዉጥ ኮሚቴ አማካይነት በቀረበዉ          ጥናታዊ ሰነድ መሰረት ተግባራዊ ለማድረግና ለዉጤት ለማብቃት ደፋ ቀና በሚባልበት በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ በማህበረሰቡ መካከል ክፍተቶችን መፍጠር አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አጠያያቂም ሆኖ አግኝተነዋል።

     በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገዉ ፕሮግራም ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በነጃሺ ስም በርዕሰ ከተማይቱ ታሪካዊና ዘመናዊነት ሊኖረው በሚገባ መልኩ ግንባታ እንደሚደረግ የገቡትን ቃል ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲቻል የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከአዲስ አበባ መጅሊስ ጋር በመሆን ስራዎቻቸዉን ጨርሰዉ ካርታ አዘጋጅተዉ ተረከቡኝ ባሉበት ወቅት ያዉም ለርክክቡና እና የመሰረት ድንጋይ ለመጣል ቀናት ሲቀረዉ ስም እንዲቀየርና የቦታዉ ባለቤትነትም ተቀይሮ ይዘጋጅ ማለት በርግጥም አስደንጋጭ ሆኖዋል።

የስም ለዉጥ ያስፈልጋል እንኳ ቢባል የሚመለከታቸዉ አካላት መክረዉበት፤ ለህዝብ አሳዉቀዉ እንጂ ሀገር አቀፍነት የያዘን ጉዳይ እና የቦታ ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የተዘጋጀለትን ተቋም በአንድ አካል ስሙ እንዲቀየር ያለምክንያት ሲጠየቅ እንዲጓተት ብሎም በወቅቱ እንዳይሳካ ከመፈለግ ዉጭ የተሻለ አማራጭ የሚያሳይ ነገር አይታይበትም፤ በሌላ መልኩ በሀገራችን ለሚገነባ ተቋም ስም ለመሰየም ለኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ከነጃሺ የተሻለ የሚወክለዉ ስምስ አለ ወይ?

      አፈጻጸሙ ጊዜ የሚሰጠዉ ጉዳይ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም በአስቸኳይ ራሱን በመፈተሽ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመሆን ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሄ መሻት እንጂ  ራሱ የችግሩ ተዋናይ መሆን አይጠበቅበትምና በዉይይት ችግሩን እንዲፈታ ትኩረት እንዲሰጠዉ እንወዳለን።

አላሁ አክበር

በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ       ሜይ 19 2020

 

 

 

Leave a comment

All comments are moderated before being published