የረጅም ጊዜ የትግል ዉጤት ለድል በቃ

        የረጅም ጊዜ የትግል ዉጤት ለድል በቃ

    በኢትዮጵያ እምነትን በነጻነት መተግበርና የእምነት ተቋሙም በሀገሪቱ  በአዋጅ ሙሉ እዉቅና እንዲያገኝ ለማስቻል የሙስሊሙ ማህበረሰብ  እጅግ ፈታኝ እና እልህ አስጨራሽ በሆነ መልኩ ከተፈራረቁበት የአጼዎች ነገስታት ጀምሮ በኡለማዎች፤ ምሁራን፤ ወጣቶች፤ ጀመዐዎች ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ቆይቷል። 

   በታሪካዊነቱ የሚዘከርለትና ሁሉን ሙስሊም ማህበረሰብ ባካተተ ሁናቴ ለተቃዉሞ ሰልፍ የበቃዉና ለትግሉ ጅማሮም መሰረት የጣለዉ በ1966 በንጉሱ አጼ ሀይለስላሴ ዘመን ታግለዉ ላታገሉ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን።

   የጭቆናዉ ደረጃ እርከኑን ስቶ እምነታችሁን እኔ ባበጀሁት ጎዳና ካልተጓዛችሁ ብሎ የሌላን እምነት በግድ ለመጫን በግልጽ አዋጅ ያወጀዉ የኢህአዲግ መንግስትን በይፋ ድምጹን አሰምቶ ተቃዉሞ ያሰማዉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ አንግቦ የተነሳዉ መሪ ቃል  “ድምጻችን ይሰማ “ የሚል ነበር።

   በአወልያ የተጀመረዉ ይኸዉ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ምንም እንኳን በመንግስት ማንአለብኝነት በአጭር ጊዜ ተጨናግፎ ይዘቱን በመቀየር የተከበሩ የህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች እና ከነሱ ጋር ተያያዥነት ያላቸዉን በጅምላ ለእንግልት እና ለሰቆቃ ፤ ለእስር ፤ ለስደት ብሎም ለህይወት መስዋዕትነት ቢዳርጋቸዉም ድርጅቱ የሰራዉ በደል በህዝብ ዘንድ ገንፍሎ በመዉጣቱ በመጨራሻ የራሱንም ህልዉና ለማስጠበቅ አላስቻለዉም። 

   በዛሬዉ እለት በመላዉ ሀገራችን የሰብዓዊ መብት ስኬት ችቦ በርቷል። ዘመን ተሻጋሪ ጥያቄ ሆኖ የቆየዉና የበርካታ ሙስሊም ማህበረሰብ የእምነት ጥያቄ የነበረዉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) በአዋጅ ህጋዊ ሰዉነት እንዲያገኝ ሲደረግ የነበረዉ ፍሬ ዛሬ ላይ ለዉጤት መብቃቱ አላህን (ሱ.ወ) እጅግ አድርገን እናመሰግናለን። በአዋጅ ቁጥር 1207/2012 ላይ የፓርላማ አባል ሆናችሁ የሙስሊሙን ማህበረሰብ አጀንዳ ለዉጤት ለማብቃት ላስቻላችሁ ታሪካዊ የመንግስት አካላት ሁሉ በኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ስም የከበረ ምስጋና እናቀርባለን።

   ዉጤቱ በተወሰኑ አካላት ብቻ የተገኘ ባለመሆኑ ሁሉን ዘርዝሮ መጥቀሱ የማያዛልቅ ቢሆንም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶ/ር አቢይ አህመድ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ቁልፍ ችግሮችን በመረዳት ከስራ ባልደረቦቻቸዉ ጋር በመሆን ሀገራዊ ለዉጡን ተከትሎ የተጫወቱት ሚና በሙስሊሙ ዘንድ የማይረሳ ታሪክ ማስመዝገብ ችለዋል። ከምንም በላይ አድናቂዎ   ነን ፤ ምስጋናችንም እጅግ በጣም የከበረ በመሆኑ በህዝበ ሙስሊሙ ስም እናቀርባለን።

  ዉድ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በጽናት ታግላችሁ በማታገል ያሳያችሁት ጨዋነት፤ ሀገር ወዳድነት ብሎም በሳል አመራር የሀገራችን ሙስሊም ማህበረሰብም ሆነ ታሪክ መቼም አይረሳችሁም። አላህ (ሱ.ወ) ጄነትን ይወፍቃችሁ፤ በጣም እናመሰግናለን። የከፈላችሁት መስዋእትነት ዉጤቱ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ መብት ከማስከበር አልፎ ለታላቁ ሀገራዊ ለዉጥ ምሰሶ በመሆናችሁ ኮራንባችሁ። ዘጠኙ የጋራ ተቋማዊ ለዉጡ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የህግ ባለሙያዎች ስራችሁ ለዉጤት በቅቷል እና የልፋታችሁን ዋጋ በማየታችን እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን። 

  ለመፍትሄ አፈላላጊ ኮሜቴ አባላት የጀርባ አጥንት ሆናችሁ ከጎናቸዉ ለተሰለፋችሁ ፤ በሀሳብ፤ በቁሳቁስ እንዲሁም በተለያዩ የትግል እንቅስቃሴዎች ዉስጥ አሻራችሁን ላሳረፋችሁ የኢትዮጵያ ህዝበ ሙስሊም በሙሉ የድምራችን የትግል ዉጤት ነዉና እናንተም እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን።

   በድር ኢትዮጵያ የሙስሊሞች የትግል እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊትም የልዑካን ቡድን በመላክ ለመንግስት ካቀረባቸዉ መሰረታዊ ጥያቄዎች መካከል ከወለድ ነጻ ባንክ እና ተቋሙ (መጅሊስ) በአዋጅ መካተት የመሳሰሉ ጥቂቶቹ ሲሆኑ ከሰላማዊ የትግሉ እንቅስቃሴ ጅማሮም አንስቶ የአቅሙን ሲያደርግ ቆይቷል ፤ ለኮምዩኒቲዎች እና ለበድር አባላቶችም እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን።   

   በዲያስፖራ የሚገኙ ሙስሊም ማህበረሰብ በተቃዉሞ ሰልፍ ፤ በሀሳብ ፤ በቁሳቁስ እና በተለያዩ መልኮች ያደረጉት ድጋፍ ለሰላማዊ ትግሉ ትልቅ ስንቅ ከመሆኑ ባሻገር በሀገራዊ ለዉጡም የነበራቸዉ ተሳትፎ መቼም የሚዘነጋ አይደለም። በቀጣይ በተቋም ግንባታዎቻችን ላይም የላቀ ተሳትፎ እንደሚኖራቸዉ በመተማመን ነዉ። ለእናንተም ያለን ምስጋና የላቀ ነዉ።

   ዉድ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ሆይ ምንም እንኳን አሁን የተገኘዉ ለዉጥ ለዘመናት ስንመኘዉ የነበረ ቢሆንም እንደ ሀገር ብዙ የሚቀሩን ፖለቲካዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ ፤ ማህበራዊ እና ተቋማዊ ጉዳዮች እንዳሉ በመገንዘብ እምነታችን እንደሚያስተምረን ሁሉ ከምንም ነገር በላይ ለአንድነታችን ትልቅ ቦታ በመስጠት ከምንጊዜዉም በተሻለ መልኩ ተጋግዘን መጓዝ እንደሚገባን አደራ በማለት ለማስታወስ  እንወዳለን።

   በመጨረሻም ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተዉ በሀገሪቱ የለዉጥ ሂደት ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን እምነታችንን  በነጻነት ለመተግበር የሚያስችሉንን በርካታ ስራዎች ይጠብቁናልና ቅደም ተከተላቸዉን ጠብቀን ለማስፈጸም አቅማችንን በጋራ አዋህደን ለተግባር እንዘጋጅ በማለት አላህ (ሱ.ወ) እንዲረዳን በመማጸን ጭምር ነዉ።

አላሁ አክበር                                                                            

በድር ኢትዮጵያ   ሰሜን አሜሪካ     ጁን 11 2020                

 

 

 

 

Leave a comment

All comments are moderated before being published