የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ጥቅሙ ለሀገርም ጭምር ነዉ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ 

 በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመዉ የተቋማዊ ለዉጥ የጋራ ኮሚቴ ስራዉን አጠናቆ በመጪዉ ረቡዕ ሚያዝያ 23/2011 የጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያደርግ ማሳወቁን የሰማነዉ በታላቅ የተስፋ ስሜት ነዉ።  ትላላቅ የሀይማኖት ልሂቃኖች የሚሳተፉበት ይኸዉ ጉባኤ የሙስሊሙ ችግሮች ዋነኛ ምንጭ ሆኖ የቆየዉ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) አሁን ያለዉን ህገ ወጥ አስተዳደር አስወግዶ የሽግግር አስተዳደር ( ባለ አደራ ቦርድ ) መቋቋሙ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የእኔ የሚለዉ ፤ ድምጹን የሚያሰማለት ፤ ለመብቱ መከበር የሚቆምለት ድርጅት ባለቤት የሚሆንበት ጊዜ መቃረቡ ጠቋሚ ነዉ። 

       ለዚህ መልካም ተስፋ ለመብቃት የብዙ እህት ወንድሞቻችን ለመከራና ስቃይ ፤  ለእስር ፤ ስደትና መስዋዕትነት የከፈሉበት ዉጤት ሲሆን ጌታችን አላህ (ሱ.ወ ) ‘’ ከችግር በኋላ ስኬት ስለመኖሩ’’ በተከበረዉ ቃሉ ያረጋገጠልንን በማስታወስ ከሁሉም አድራጊዉ ፈጣሪ አላህ በመቀጠል ሀላፊነቱን ወስደዉ ያለመታከት ለሙስሊሙ ችግር ድምጽ በመሆን በእዉቀታቸዉና በጉልበታቸዉ የታገሉትና ለሀገር ሰላምና እድገት የእያንዳንዱን ዜጋ ሰብአዊ መብትና ነጻነት መከበር ወሳኝ መሆኑ ተረድተዉ የታገሉ የሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ምንዳችሁን ያብዛላችሁ እንላለን ።

        ሁሉንም እምነትና ህዝቦችን እኩል ለማየት እየሞከረ ያለዉን የዶ/ር አቢይ አህመድ አስተዳደርንም ከልብ ልናመሰግን እንወዳለን። በመቀጠልም በሀገሪቱ ያለዉ መላዉ ሙስሊም ማህበረሰብ የዉስጥ ችግሩ ተቀርፎለት በሀገር ግንባታ ፤ ሰላምና አንድነትን ለማስጠበቅ  በተገኘዉ ለዉጥና ተስፋ መጠናከር ከሌላዉ ወገኑ ጋር በመተባበር አመርቂ ስራ እንደሚሰራ እየተማመን በድር ኢትዮጵያ የሙስሊሞች ድርጅትም እህት ማህበራቱንና አባላቱን በማስተባበር በሃገር ግንባታዉ ላይ የሚደረገዉ አስተዋጽኦ የሚያጠናክር መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን ።

አላህ ሱወ ሀገራችንን የፍትህ የእኩልነት ምድር አድርጎ ያቆይልን !!

         በድር ኢትዮጵያ     ሰሜን አሜሪካ    ኤፕሪል 29 2019

Leave a comment

All comments are moderated before being published