የሀገራዊ ማንነት ህሳቤ የጋራ ጉዳይ ይሁን

የሀገራዊ ማንነት ህሳቤ የጋራ ጉዳይ ይሁን

   ሀገራችን  ኢትዮጵያ በምታራምደዉ መሰረታዊ የለዉጥ ሂደት ላይ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ የለዉጡን ፍሬ ተቋዳሽ እንዳይሆንና የአገሪቱም ሰላም እንዳይረጋጋ የሚያደረጉ ጥቂት ሃይሎች መኖራቸዉ ከማንም የተሰወረ አይደለም። በአሁኑ ወቅት እየተስተዋሉ ካሉ ተግዳሮች መካከል አንዱ በቤተ እምነቶችና በአማኞች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች ናቸዉ። በድር ኢትዮጵያም በየትኛዉም ሃይማኖት ቤተ እምነቶች እና አማኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በጽኑ ይቃወማል ፤ ያወግዛልም።ሀይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ትንኮሳዎችም በጊዜ ካልተገቱ የሀገርን ሰላም ከማወክ አልፈዉ ወዳልተፈለገ ብጥብጥ የሚያመሩ በመሆናቸዉ ጥቃት ፈጻሚዎችን አድኖ በመያዝ ለፍርድ ማቅረብና ችግሮቹ ዳግም እንዳይከሰቱ ከምንጫቸዉ ማድረቅ የመንግስትና የሁሉም ሰላም ወዳድ ዜጋ ሀላፊነት ነዉ።

     ሀገራችን እንድትረጋጋ በማይፈልጉ ሀይሎች እየተፈጠሩ ባሉ እኩይ ችግሮች ሳቢያ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ወገኖቻችን ቀያቸዉን ለቀዉ እንዲፈናቀሉ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ተካሂዷል፤ መስጂዶች እና ቤተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል። ይህ ተግባር ሁላችንንም ያሳዘነና በጋራ ያወገዝነዉ ተግባር ቢሆንም  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ጽንፈኞች በሀገር ደረጃ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች መንስኤዉና መፍትሄዉን ከመሻት ባሻገር ችግሮቹ ሥር እየሰደዱ እንዲመጡ በተለያዩ የቴሌቭዢን ጣቢያዎች ፤ በሶሻል ሚዲያና እንዲሁም እነሱ በሚመሯቸዉ የተለያዩ ድህረገጾች ላይ የክፍፍል ዘመቻ በተለይ በእስልምና እምነት ላይ በሰፊዉ እየተነዙ ይገኛሉ። የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት ሆኖ ሳለ ሀይማኖታዊ ይዘት እንዳለዉ በማስመሰል  ሙስሊም ክርስቲያን ሳንል ፤ በብሄር ሳንለያይ ተደጋግፈን ህይወትን ያስገበረ ዘርፈ ብዙ መስዋእትነት በጋራ ከፍለናል ጊዜዉም ሩቅ አይደለም። በተለይ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዚህ ለዉጥ መሳካት የከፈለዉ መስዋዕትነት ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም።

   ገዳማቶች ሲፈርሱ ፤ ቀሳዉስቶች ሲታሰሩ ከክርስቲያን እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ጎን በመቆም አደባባይ ወጥተን ከመጮህ አልፎ ጠበቃ ያቆምንበት ድምጻችን ይሰማ ብለን እንደ ንብ ሆ ብለን በተነሳንበትም ወቅት እነዚሁ ወገኖቻችን ድምጻችሁ ድምጻችን ነዉ ብለዉ ከጎናችን የቆሙበት ወቅት አኩሪ ታሪክ ተብለዉ ከሚመዘገቡ የአብሮነት ታሪካችን የራሱ ምእራፍ እንደሚኖረዉ ጥርጥር የለዉም ። የሰብዐዊ መብት መከበርና በደላችሁ በደላችን በማለት ይህንኑ ግብረሰናይ ድርጊት በሱማሌ ክልል ሆን ተብሎ በአፍራሾች እንዲቃጠሉና እንዲፈርሱ የተደረጉ አብያተ ክርስቲያናት ግንባታ የክልሉ መንግስትና የአካባቢዉ ሙስሊም ህብረተሰብ ያደረገዉ ርብርቦሽ የሚያሳየን ጠብ ጫሪዎች ወደ ፈለጉት ድቅድቅ ጨለማ ወደ ወረሰዉ መንደር ሳይሆን ብሩህ ተስፋ ወደ ሚታይበት መንደር ለመሆኑ ካላይ የተጠቀሱ ድርጊቶች በቂ መረጃዎች ናቸዉ።

    በመጨረሻም ለማስተላለፍ የምንፈልገዉ መልእክት የሌላዉን እምነትን ባነጣጠረ መልኩ የሚፈጸሙ የስም ማጥፋት ፤ የእምነት ተቋማትን መንካት፤ የሀይማኖት መሪዎችን ማብጠልጠል የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ መተላለፍ ሊያመጣ የሚችለዉን ጉዳትና የሚያስከፍለዉን መስዋእትነት በግልጽ መረዳት ያሻልና ጥንቃቄ ያሻል። ከመሰል እኩይ ተግባራትም እንዲቆጠቡ አበክረን ለማስታወስ እንወዳለን። 

   በዚህ አጋጣሚ እምነትን መተግበርም ሆነ የእምነት ቦታዎችንም ከጥፋት መታደግ የሚቻለዉ ሰላም ሲሰፍን ብቻ መሆኑን በመረዳት ተቆርቋሪ አካላት ፤ያገር ሽማግሌዎና የእምነት አባቶች ሰላም እንዲሰፍን ብሎም መረጋጋት እንዲፈጠር ከምን ጊዜዉም በበለጠ ጥረት እንዲያደርጉ በዚሁ አጋጣሚ ለመጠቆም እንወዳለን።    

 የሀገራችንና የህዝቦቿን ሰላም አላህ ይጠብቅልን  !!!

በድር ኢትዮጵያ       ሰሜን አሜሪካ        ሰፕተምበር  2, 2019

Leave a comment

All comments are moderated before being published