ከመጅሊስ ኡለማ ምክር ቤት የመርህና ስርዐት አርአያ መሆንን ይጠበቃል

Posted by Badr Ethiopia on

 ከመጅሊስ ኡለማ ምክር ቤት የመርህና ስርዐት አርአያ መሆንን ይጠበቃል

   የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የራሳችን የሆነ ተቋም እንዲኖረን ለረጅም ጊዜ ያላሰለሰ ጥረት እና መራር እንቅስቃሴ ባደረግንበት ወቅት ሁሉ በየጊዜያቱ በትግሉ ህይወት የከፋ የስደት ፤ እስር እና የአካል መጉደል እንዲሁም የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል አሁን ያለንበት ወሳኝ ወቅት በአላህ (ሱብሁዋነሁ ወተአላ) ፈቃድና በተከፈለዉ እልህ አስጨራሽ መስዋዕትነት ሳቢያ የትግል ፍሬዉ በተግባር ተተርጉሞ ለማየት ባንታደለም የተቋሙ ባለቤት ለመሆን በቅተናል።             

   ይህን የትግል ፍሬ ወደ መሬት ለማዉረድ ዘጠኝ አባላትን ባቀፈዉ የተቋማዊ ለዉጥ አጥኚ አካላት በተዘጋጀዉ የስምምነት ሰነድ መሰረት ተቋሙን መምራት እንዲያስችላቸዉ ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸቱ ይታወቃል። 

   በወቅቱ ሀላፊነት የተሰጣቸዉ የመጅሊሱ ሰባት የቦርድ ስራ አመራር እና ሀያ ስድስት የኡለማ አባላት በቀጣይ ስድስት ወራት ዉስጥ በወሳኝነት ተቋሙን ወደ ሚቀጥለዉ እርከን ለማሸጋገር የሚያስችሉ እና በቋሚነት የሚሰሩ የአመራር አካላትን በየደረጃዉ ማዋቀር ኋላፊነት ተጥሎባችዉ ነበር። ነገር ግን በሚያሳዝንና ከዲን አዋቂዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ በጥቂት ግለሰቦች ግፊት የአሏህ ፍራቻ ያደረባቸዉን ኡለሞች ቁጥር በማመናመን ቀሪዎቹን እጅ በመጠምዘዝ አግባብነት በሌለዉ መንገድ የስልጣን ዘመናቸዉን ከማራዘም አልፎ ሙስሊሙን ማህበረሰብ በልዩነት እንዲዘልቅ ምክንያት ሆነዋል።

    ከዚህ ቀደም የኡለማ ዘርፉ ከአሰራር ዉጪ የቦርድ ስራ አመራር ጸሀፊዉ ላይ እገዳ ለመጣል መሞከሩ በርካታ ተቃዉሞዎችን ማስተናገዱ ይታወሳል ።  አሁንም በጠቅላላ ጉባኤ የተወከሉትን የቦርድ አባላት መርህ በጣሰ መልኩ   ማክሰም መሞከር የወከላቸዉን ህዝብ ንቆ ስልጣንን ጠቅልሎ ከመያዝ ባሻገር ድርጅቱ መዋቅራዊ አመራር እንዳይከተል እክል መሆን እጅጉን አሳዝኗል።

   ሀገራችን ባለችበት ዉስብስብና መጠነ ሰፊ ችግሮች በሚስተናገዱበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ሙስሊሙን ማህበረሰብ ሀገራዊ ተሳትፎዉን እንዳያጎለብትና ሙስሊሙ ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዳይሆን ጫናዎችን መፍጠር ከራሱ ተቋም የማይጠበቅ ተግባር መሆኑንም ለመግለጽ እንወዳለን ።

   የመጅሊስ አመራር አካላት አደራ የሰጣቸዉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ መሆኑን ተረድተዉ ጉዳዩ ከመንገድ ከመዉጣቱ በፊት በአስቸኳይ ከሚመለከታቸዉ የክልልና መሰል ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሁሉ አቀፍ የዉይይት መድረክ በማዘጋጀት እንዲሁም ደንቡ በሚያዘዉ መሰረት በጠቅላላ ጉባኤዉ አማካይነት ምርጫ እንዲያካሄዱና ችግሮችን እንዲፈቱ እያሳሰብን ችግሩን ለመፍታት በሚደረገዉ ርብርብ በድር ኢትዮጵያም አስፈላጌዉን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን እንገልጻለን ። በመጨረሻም የሰላም ሚኒስትርም ጉዳዩ ሀገራዊ ከመሆኑ አንጻር ልዩ ትኩረት በመስጠት ችግሩን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ለዉጤት ያበቃዉ ዘንድ እንጠይቃለን።

አላህ (ሱብሁዋነሁ ወተአላ) ቀጥተኛዉን መንገድ ይምራን

በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ     ጃንዋሪ 29 2021                           


← Older Post Newer Post →