ኢ ድ    ሙ ባ ረ ክ

ኢ ድ    ሙ ባ ረ ክ

    በሰሜን አሜሪካ እና በመላዉ ዓለም ለምትገኙ ሙስሊሞች በሙሉ በድር ኢትዮጵያ እንኳን ለ 1440 ኛዉ የኢድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል አላህ (ሱ.ወ) በሰላም ፤ በደስታና በፍቅር አደረሳችሁ እያለ መልካም ምኞቱን በደስታ ይገልጻል።

   ባለፉት ዓመታት ዋነኛዉ ምኞታችን ዉድ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችን እና ከነሱ ጋር ተያያዥነት የነበራቸዉን አካላት በግፍ ለአስከፊዉ እስር በመዳረጋቸዉ ከእስር እንዲፈቱና ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር በሰላም እንዲቀላቀሉ ሁሉም በየፊናዉ የተቻለዉን ሁሉ ጥረት ሲያደርግ  ነበር የቆየዉ።

     ለፈጣሪያችን አላህ (ሱ.ወ) የላቀ ምስጋና ይገባዉና ያ ሁሉ አልፎ የህዝበ ሙስሊሙ የረጅም ጊዜ የመጅሊስ ጥያቄም ምላሽ አግኝቶ የእምነት ተቋሞቻችንን ህዝበ ሙስሊሙ በራሱ ለማስተዳደር በሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በሀገራችንም ዘላቂነት ያለዉ የተረጋጋ ሰላም እንዲመጣ እንዲሁም የተገኙ መልካም ድሎችን ጠብቆ ለማቆየት የሁሉም አካላት ድርሻ እና የተጠናከረ ጥረትን የሚሻ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ የግድ ይላል።

      መስጂዶቻችንን መጠበቅ እና መንከባከብ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ግዴታ እንደመሆኑ መጠን  ሁሉም ሙስሊም ማህበረሰብ ባለበት አካባቢ በንቃት መስጂዶችን እንዲጠብቅ እና ትኩረት እንዲሰጠዉ በማለት በድር ኢትዮጵያ ጥሪዉን ያስተላልፋል።በዘንድሮዉ ዓመት የሀጅ ፕሮግራም ለመፈጸም ከኢትዮጵያ የተጓዙ ሁጃጆችም ከአሁን ቀደም የነበሩ ችግሮች ተቀርፈዉ በተሻለ መልኩ ተስተናግደዉ በስኬት እንደሚመለሱ ተስፋ እናደርጋለን። ­­

    በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆንልን በመመኘት የተራበና የታረዘን እያስታወስን በምንችለዉ ሁሉ እንድንደርስላቸዉ ሲሆን በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸዉ ለተፈናቀሉና ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖቻችን በምንችለዉ አቅም ሁሉ በመርዳት እለቱን እንድናሳልፍ ሆኖ በዓለም ለሚገኙ ሙስሊም ማህበረሰብም በሙሉ በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ደስታችንን እንገልጻለን።

በድር ኢትዮጵያ      ሰሜን አሜሪካ      ኦገስት 10 2019

Leave a comment

All comments are moderated before being published