በአማራ ክልል የተፈጸመ የመስጂድ ቃጠሎ

በአማራ ክልል የተፈጸመ የመስጂድ ቃጠሎ

        ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ላለፉት ዘመናት በነገስታቶችም ሆነ በመንግስታት ዘርፈ ብዙ ግፎች ሲፈፀምባቸዉ ችለዉ ኖረዋል። ሁሉም መሪዎች መጠኑ ቢለያይም ሙስሊሞችን በድሏል፤ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ እንዲገለሉ የተለያዩ ፖሊሲዎችን በማዉጣት አስተዳደራዊ መድሎ ፈጽሞባቸዋል። ሙስሊሙ በሀገሩ ባይተዋር ሆኖ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንዲታይ እና በሀገር ግንባታ ላይ ሚና እንዳይኖረዉ ደባ ተሰርቶበታል። መስጊዶችን ፤ የቁርአን መማሪያ ትምህርት ቤቶችን፤ እስላማዊ ኮሌጆችን እንዳይገነባ በይፋም በስዉርም ሲከለከል ቆይቷል። ጠንካራ የሆነ መሪ ተቋም እንዳይኖረዉም ተደርጓል።

   በኢትዮጵያ የተገነቡ መስጂዶች ባብዛኛዉ ግለሰቦች ገንዘብ አሰባስበዉ በሚገዙት መሬት ላይ የተሰሩ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ የግለሰቦችን ቤት በወፍቅ (በስጦታ) የተገኙ ሲሆን በዉስንነት የሚታወቁት ደግሞ በፈቃድ የተሰጡ ቢሆንም የህይወት መስዋዕትነት ተገብሮባቸዉ በትግል የተሰሩ መሆናቸዉ ምን ያህል አግላይ ስርዐት እንደነበር የሚያሳይ ነዉ።  አሁንም ድረስ ማምለኪያ መስጂድ እና መቀበሪያ ስፍራ የተነፈጉ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞችም አሉ። ሙስሊሙም ማህበረሰብ ይህ አይነቱ መድሎ እንዲቀር ከአጼዎች ዘመን ጀምሮ በሚችለዉ ነገር ሁሉ እየታገለ ዛሬ ላይ ተደርሷል።

    ሙስሊሙ ማህበረሰብ በቅርቡ የነበረዉን የግፈኛ አገዛዝን ለመደምሰስ እና የዜግነት መብቱ ይጠበቅለት ዘንድ እልህ አስጨራሽ የሆነ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ አድርጓል፤ለተገኘዉ ሀገራዊ ለዉጥም ፈር ቀዳጅ መሆኑን ማንም ሊክደዉ የማይችለዉ ሀቅ ነዉ ። ሆኖም ግን ምክንያት ለሆነለት አንጻራዊ ለዉጥ ሙስሊሙ ማህበረሰብ እዉቅና ሊቸረዉ ሲገባ በተቃራኒዉ በህልዉናዉ ላይ እንቅፋት በመፍጠር ብሎም በጽንፈኞች ተቋሞቹን በእሳት እያጋዩት ይገኛል። 

   ትላንት ጁምዓ ዴሰምበር 20/2019 በአማራ ክልል በጎጃም ሞጣ ከተማ በአንድ ምሽት ብቻ አራት መስጂዶች በኢስላም ጠል ጽንፈኞች በግፍ ተቃጥለዋል። የሙስሊም ቤቶችና የንግድ ተቋማት ጭምር እየተመረጡ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ስለሆነም እጅጉን ማዘናችንን እና የጽንፈኞችንም ተግባር አጥብቀን እንደምናወግዝ ለማሳወቅ እንወዳለን።

    በተለይ በአማራ ክልል መሰል ጥቃቶች በተደጋጋሚ መከሰታቸዉ በሙስሊሙ ዘንድ አጠያያቂ ሆኗል። ከዚህ ቀደም እንደሚባለዉ ‘’ የፖለቲካ ፍጆታ ያላቸዉ አካላቶች ’’ በሚለዉ ሀረግ አሸብርቆ ሊታለፍ የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑና ሙስሊሙ ማህበረሰብም ከመቼዉም በተለየ መልኩ እየተቃጣበት ያለዉ የጥፋት ዘመቻ በትዕግስትና በዝምታ እንደማያልፈዉ ሁሉም አካል ሊገነዘበዉ ይገባል። እስከ አሁን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በርካታ መስጂዶች በግፍ ተቃጥለዋል፤ ምክንያት ተፈጥሮባቸዉ እንዲፈርሱ ተደርጓል፤ የቦንብ ጥቃት ደርሷል፤ ምዕመናን መስጂድ ዉስጥ እያሉ ተገድለዋል ፤ የአላህ (ሱወ) ቁርአን በሚያሳዝን ሁኔታ ተቃጥሏል፤ በድምሩ ሰላሳ አምስት መስጂዶች እንዲቃጠሉ ተደርጓል። ይህ ሁሉ ሲሆን ሙስሊሙ የወቅቱን ያገራችንን ሁኔታ ከግምት በማስገባት በደሉን ለመንግስት ከማሳወቅ በዘለለ ያደረገዉ አንዳችም ነገር አልነበረም።

    የሙስሊሙ ዝምታ ሽንፈት የመሰላቸዉ ሀይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ቡድኖች እና ጽንፈኛ ግለሰቦች በሙስሊሙ ላይ ሌት ተቀን የጥፋት እቅድ ሲያወጡና እቅዳቸዉ እንዲተገበር በተለያዩ ሚዲያዎች በይፋ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ሰንብተዋል። በተለይ ላለፉት ሰባት ወራቶች ሙስሊሙ ላይ ያነጣጠረ ሰበካ በየ ጉባኤዉ ላይ ሲሰጥ ተመልክተናል። በየ ቤተ እምነቱ ሁሉ ሳይቀር የተሰራጨ በሃሰት የተቀነባበረ ጸረ ኢስላም ቪዲዮ መታየቱንም ሁሉም የሚያዉቀዉ እዉነታ ነዉ። ይህንንም መንግስት እንዲያስቆም በተለያየ መልኩ ቢሞከርም ሳይሳካ ቀርቷል። ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለሀገሩ አንድነትና ጸጥታ ቅድሚያ ከመስጠት አኳያ ብሎም መስዋዕት ተከፍሎበት በተገኘዉ ሀገራዊ ለዉጥ ችግር ሆኖ እንዳይገኝ ከማሰብ እንጂ ለመብቱ ምን ማድረግ እንዳለበት ከማንም የሚጠይቀዉ አመራርም ሆነ ልመናዊ አካሄድ አይኖርም፤ በተግባር የተፈተነበት ጉዳይ ከመሆኑ አንጻር መብቱን ለማስከበር መቼም ብቁ ነዉ።

ጅራፍ ራሱን መቶ ራሱ ይጮሀል እንደሚባለዉ ሁሉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ይህን ያህል እየተፈጸመበት ያለዉን በደልና ግፍ እየቻለም ተበደልኩ ብሎ የሚጮኸዉ ሌላ አካል መሆኑ ከታሪክ የተረዳነዉ የረጅም ጊዜ ሂደት ነዉ። በእምነቶች መካከል ጣልቃ በመግባት የእኔ ሀሳብ ካልሆነ በሚል የማን አለብኝነት ክንዋኔ በህዝቦች መካክል ቅራኔና ልዩነቶችን ከማሳደጉ ዉጭ አንድ ርምጃ እንኳ መጓዝ የማይችል ህሳቤ እንደሆነ ሁሉም አካል በዉል ሊረዳዉ የሚገባ ሀቅ ነዉ።

    በዲያስፖራ የምንገኝ ሙስሊም ማህበረሰብ እጅግ በጣም ካዘንባቸዉ ጉዳዮች በዋነኛነት መንግስት ባለበት ሀገር የእምነት ተቋም አቃጥለዉ በጭፈራ ደስታቸዉን የሚገልጹ የሞራል ስብዕና የሌላቸዉ አካላትን ማየቱ ሲሆን በሌላ መልኩ የሚመለከታቸዉ አካላት ሁሉ በጉዳዩ አሉበት ለማለት በሚያስችለን የህሳቤ ደረጃ ላይ ደርሰናል። ምክንያቱም በተቃጠሉ መስጂዶች ጉዳይ እስከዛሬ ድረስ የክልል አመራሮችም ሆኑ የፌደራል መንግስት ምንም አይነት የክትትልም ሆነ የማጣራት ዘመቻ አለማከናወናቸዉ ተዛማጅነት ባላቸዉ መልኩ ተጨማሪ ጥፋቶች እንዲተገበሩ ምክንያት በመሆናቸዉ ነዉ።           

     በሱማሌ ክልል የተቃጠሉ አብያተ ቤተክርስቲያናት በየትኛዉም አካል ጥቃቱ የተፈጸመ እንኳ ቢሆንም የፌድራል መንግስት በጉዳዩ የገባ ሲሆን ሙስሊሙ ህብረተሰብና የክልሉ መንግስትም በክልላቸዉ ለተፈጸመዉ ሁኔታ ተጠያቂነታቸዉን አምነዉ ይቅርታ ጠይቆ መልሶ እንደገነባዉ ሁሉ ከአማራ ክልላዊ መንግስትም ተመሳሳይ ርምጃ እንጠብቃለን።                                                        

   በሌላ መልኩ በሌሎች የእምነት ተቋማት እና የእምነት መሪዎች በኩልም ሙስሊም ጠል የሆኑ ቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ በተለያየ መልኩ ሶሺያል ሚዲያን ጨምሮ ሲሰራጭ እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነዉ። ትላንት ሙስሊሙ ህብረተሰብ የታገለለትን መብቱን የማስከበር ሰላማዊ እንቅስቃሴ ዳግም በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት የሚያመላክቱ በርካታ ተግባራቶች ስለሚታዩ ዓላማችን እምነታችንን በተፈለገዉ መልኩ መተግበር ብሎም መብታችንን እስከ ጥግ ማስከበር ነዉና ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥቃቅን ልዩነቶችን በመተዉ በዋነኛነት እየተፈጸመብን ያለዉን ጥቃት ለመከላከል በቁርጠኝነት ተደራጅተን መብቶቻችንን ሀገ መንግስቱ በሚፈቅድልን መሰረት ተግባራዊ ለማድረግ እንጣር እያልን ሙስሊሙን ማህበረሰብ ታርጌት ያደረገ ጥቃት ፈጻሚዎችም ከእኩይ ተግባራቸዉ እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ እንወዳለን።

    በመጨረሻም በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎችን ጨምሮ መስጂዶች በመቃጠላቸዉ አዘኔታን እየገለጽን የተቃጠሉ መስጂዶችን ለመገንባት ሙስሊሙ ማህበርረሰብ ጠንካራ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ሆኖ በሌሎች መስጂዶች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ዳግም እንዳይፈጸም በየ አካባቢዉ የሚገኙ ሙስሊም ማህበረሰብም ጥበቃዉን በማጠናከር ተቋማቱን እንዲንከባከብ በዚሁ አጋጣሚ ለመጠቆም እየወደድን ጉዳዩ ወደ ከፋ ደረጃ ከመሸጋገሪሩ በፊትም የፌደራል መንግስት እና የክልል መንግስታት በጋራ በመሆን ልዩ ትኩረት ሰጥተዉ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሹ አበክረን እናሳስባለን።  

አላሁ አክበር !

       በድር ኢትዮጵያ                ሰሜን አሜሪካ     ዴሰምበር 21 2019

Leave a comment

All comments are moderated before being published