በበድር ስር እንድትሳተፉ ጥሪ ስለማቅረብ

በበድር ስር እንድትሳተፉ ጥሪ ስለማቅረብ

   በድር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት የዛሬ ሀያ ዓመት ኮምዩኒቲዎችን በአንድነት በስሩ አቅፎ ሲቋቋም አላማ አድርጎ የተነሳዉ  በዲያስፖራ የምንገኝ ሙስሊም ማህበረሰብ እምነታችንን ብሎም ባህላችንን በተገቢዉ ሁናቴ ለመተግበር እንድንችልና በሀገር ቤትም ሙስሊሙን ማህበረሰብ በሁለንተናዊ መልኩ አቅም በፈቀደ መጠን ለመደገፍ እንደሆነ ግልጽና የማያሻማ መሪ ሀሳብ ነበር።

   እስከ 2004 ድረስ በድርጅታችንም ሆነ በየኮምዩኒቲዎቻችን መካከል ይህ ነዉ የሚባል ችግሮች ሳይኖሩ  በድር ኢትዮጵያ በወቅቱ በስሩ በርካታ ኮምዩኒቲዎችን አቅፎ የተጓዘ ሲሆን በኮምዩኒቲዎችም ዘንድ እንደ ነበራቸዉ እንቅስቃሴና ተሳትፎም አንጻራዊ እድገት መፍጠሩ አይዘነጋም።

    በ2004 በሀገራችን በተደረገዉ ሀገመንግስታዊ ፤ የመብትና የእምነት ነጻነትን አስመልክቶ በተካሄደዉ    የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴን ተከትሎ በተለይ በዲያስፖራ በምንገኝ ሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ በተፈጠሩ የአመለካከት እና የአካሄድ ልዩነቶች ሳቢያ ክፍተቶች ተፈጥረዋል። በሂደቱም አንዳንድ ኮምዩኒቲዎችም ራሳቸዉን ከበድር ማግለላቸዉ ይታወቃል።

    ሀገራዊ ለዉጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ በኩል ያሉ ሁኔታዎች መሻሻል የሚታይባቸዉ ሲሆን ቀደም ሲል በመካከላችን ነበሩ ለተባሉ ችግሮችም በአብዛኛዉ በቂ መልስ ያገኙ በመሆኑ ልዩነቶችን በማጥበብ ይበልጥ ተጠናክረን ራሳችንን በማደራጀት ያሉብንን መጠነ ሰፊ ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ እንድንችል ከምን ጊዜም በላይ ተቀራርበን ልንሰራ ግድ እንደሚለን ወቅቱም ጠቋሚ እንደሆነ ይታመናል።

   ከዚሁ አንጻር ከበድር ራሳችሁን ያገለላችሁም ይሁን ያልታቀፋችሁ ኮምዩኒቲዎች በጋራ ድርጅታችንን ለማጠናከር በሚቻልበት መልኩ ተቀራርበን ለመስራት የሚያስችሉን በርካታ ጉዳዮች አሉና ወደ ድርጅታችን እንድትቀላቀሉ ጥሪ እያቀረብን ይህም በዲያስፖራ ሁሉ አቀፍ የሆነ ጠንካራ ድርጅት መኖሩ ጥሩ ተቋማዊ አቅም ከመፍጠሩ ባሻገር በሀገር ቤት ደረጃም ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን ያስችለናል። ይህንኑ ተገንዝባችሁ በበድር ኢትዮጵያ ድርጅት ስር እንድትታቀፉ እንደ ሁልጊዜዉም በአክብሮት ጥሪ በማቅረብ እንጠይቃለን ።      

 አላሁ አክበር

በድር ኢትዮጵያ       ሰሜን አሜሪካ     ጁን 28, 2020                                                             

Leave a comment

All comments are moderated before being published