በመጅሊሱ የቦርድ ጸሀፊ ላይ ደረጃዉን ያልጠበቀ እገዳ

በመጅሊሱ የቦርድ ጸሀፊ ላይ ደረጃዉን ያልጠበቀ እገዳ 

     በሀገራችን በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ለዘመናት ሲፈራረቁበት የነበሩ መጠነ ሰፊ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በሚደረገዉ ጥረት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ድምጻችን ይሰማ በሚል መሪ ቃል ባደረገዉ የህገመንግስት ፤ የመብትና የእምነት ነጻነት መከበርን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት የከፈለዉን መስዋዕትነት እና በሀገሪቱ የተከሰተዉን አንጻራዊ ለዉጥ ተከትሎ ከመሰረታዊ ጥያቄዎች በዉል የሚጠቀሱ ዉስን ተግባራት ተፈጻሚ ቢሆኑም የፌድራል መጅሊሱ ግን ለዉጥን ተቀብሎ ሙስሊሙን ማህበረሰብ የኢኮኖሚያዊ ፤ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችል  መልኩ ከፍ ወዳለ ደረጃና ቁመና ላይ ማሻገር ሲገባቸዉ ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ ከሽኩቻ የዘለለ ስራ አለመስራቱና ከአንድ የቦርድ አባል ጋር የደረሰበትን የሀሳብ ልዩነት በዉይይት የመፍታት አቅም አጥሮት በእገዳ ደብዳቤ ተወስኗል ።         

   ቀደም ሲል በነበረዉ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብም ሆነ ሚያዝያ 23 2011  በሸራተን አዲስ ሆቴል በተደረገዉ ሀገራዊ ስብሰባ ተቋሙን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተዘጋጀዉ ተቋማዊ የስምምነት ሰነድ መሰረትም ቢሆን ድርጅቱን በበላይነት የሚመራዉ ቦርድ ሆኖ ሳለ በሌላ መልኩ በማንኛቸዉም ተቋማት  አደረጃጀት መሰረት ቦርዱ የበላይ የድርጅቱ አስፈጻሚ አካል መሆኑ እየታወቀ በማን አለብኝነት በማንኛዉም መልኩ ተቀባይነት ባይኖረዉም የድርጅቱ የበላይ አካል የሆነዉ የፌድራል መጅሊስ ቦርድ ዋና ጸሀፊ የሆኑት አቶ ከማል ሀሩንን በኡለማ ምክር ቤት በተጻፈ ደብዳቤ አግጃለሁ ማለቱ ምን ተፈልጎ እንደሆነ ለመተንበይ አጠራጣሪ ጉዳይ ሆኗል።

   በአዲስ መልክ ከተዋቀሩ ጊዜያዊ ኮሚቴዎች አንዱ የሆነዉ የፌድራል መጅሊስ ቦርድ ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤ ሲሆን ሁሉም ጊዜያዊ ኮሚቴዎች በቀጣይ በስድስት ወራት ዉስጥ የምርጫ አፈጸጸምና መሰል ሂደቶችን ማመቻቸት እንዳለባቸዉ ቢታወቅም ከአንድ ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ዉስጥ ምርጫ አለማካሄዳቸዉ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በጠቅላላ ጉባኤዉ የተወከሉ አካላትን በተለያዩ ሰበብ አስባቦች አባላቱ በተመደቡበት የስራ ገበታ ላይ እንዳይገኙ ወይንም በፈቃዳቸዉ ለቀዉ እንዲሄዱ ከማመቻቸት አልፎ ሌሎች የተሰጠንን የህዝብ ሀላፊነት በቁርጠኝነት መወጣት አለብን በሚል በጽናት የቆዩትን ደግሞ በደብዳቤ በማገድ ድርጅቱ እንደተቋም ለመንቀሳቀስ በሚችልበት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ተዳርጓል።

   ከሁሉም በላይ እጅግ የሚገርመዉ ግን ሀገራችን ባለችበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ሙስሊሙን ማህበረሰብ የሚከፋፍል ብሎም በመንግስት ላይ እንዲነሳሳ የሚያደርግ ተግባር ለመፈጸም በሚያስችል ሁናቴ ሌላ የጦርነት አዋጅ ክተት በሚመሰል መልኩ ጊዜዉ የተመረጠበት ምክንያት መንግስት በራሱ ወሳኝ ጉዳይ ስለተጠመደ ትኩረቱን እኛ ላይ ስለማያደርግ እኛ የፈለግነዉን ለማድረግ ያመቻል በሚል የወሰዱት የተሳሳተ ግምት ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተለየ አቋም እንዳለዉ አስመስሎ ተጠያቂ ለማድረግ ታቅዶ የተሰራ ሥራ እንደሆነም ግልጽ ነዉ። በሌላ እይታ እንደምንረዳዉ ከሆነ ሀገራችን አሁን ካለችበት የጦርነት ፍልሚያ ወቅት የህብረተሰቡን ትኩረት ወደ ሌላ አቅጣጫ የመዉሰድ አጀንዳ ለመፍጠር ከመሞከር የዘለለ ሌላ ፋይዳም የለዉም ብለንም እናምናለን።    

    እንደ የእምነት ተቋምነቱ በሀገር ዉስጥ ጦርነትና መሰል ሁሉ አቀፍ ችግሮች ሲከሰቱ ህብረተሰቡን በማስተባበር ችግሮቹ ሊቀረፉ እና በሰዉ ህይወትና ብሎም ለሚወድመዉ ንብረት በማሰብ ዘላቂ መፍትሄ መሻት እንጂ በህብረተሰቡ መካከል አንድነትን የሚያሻክሩ እንቅስቃሴዎችን ለመፍጠር መጣር ህብረተሰቡን ለመለያየት ብሎም በመንግስት ላይ ጫናን ለመፍጠር ሆን ተብሎ ታቅዶ የተደረገ አጸያፊ ድርጊት ነዉ። ከተጠያቂነትም አያድንም።  

    የኡለማዎች ምክር ቤት የስራ ድርሻዉን ለይተዉ ሊያዉቁ እንደሚገባ ለመጠቆም እየወደድን እገዳዉ አግባብ ባለመሆኑ ይቅርታን ባዘለ መሻሪያ ደብዳቤ ሊያስተካክል ይገባል እያልን የፌድራል ቦርድ እና የኡለማዎች ምክር ቤት በጋራ ቁጭ ብለዉ ችግራቸዉን እንዲፈቱና ዉጤቱንም ለህብረተሰቡ በጋራ እንዲያሳዉቁ እያሳሰብን ሙስሊሙ ማህበረሰብም በሀገራችን እየተካሄደ ያለዉን ጦርነት ከግንዛቤ በማስገባት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ተጨማሪ ችግር እንዳይሆን በጥንቃቄ ለችግሩ መፍትሄ ለመሻት በጋራ መንቀሳቀስ እና የታገለለትን ዓላማ ለስኬት እስኪያበቃ ድረስ  ያለምንም መሸማቀቅ በሰላማዊ መንገድ መታገል እንዳለበት መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ እንደሆነ በማመን ነዉ።

አላህ (ሱብሁዋነሁ ወተአላ ) ሀገራችንና ህዝባችንን ይጠብቅልን አሜን !

በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ    ኖቨምበር 10 2020

Leave a comment

All comments are moderated before being published