በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ

በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ

   ለረጅም ዘመናት በታሪክ እንደምንረዳዉ በኢትዮጵያ ህብረተሰቡ በጥሩ ማህበራዊ ሁኔታ በመቀራረብ ፤ በመተሳሰብ ፤ በመቻቻል እና በመሳሰሉ ሁኔታዎች ተሳስሮ በጋራ ይኖር እንደነበር በሰፊዉ ሲተረክ ይታወሳል። ይኸዉ ማህበራዊ ኑሮአቸዉንም ሀይማኖት ፤ ዘር ፤ ቋንቋ ፤ አካባቢና መሰል ጉዳዮች ሳይገድባቸዉ ህዝቦች አንድነታቸዉን ጠብቀዉ ኖረዋል፤ ምንም እንኳን በነበሩ መንግስታት በኩል ይደረጉ የነበሩ ልዩነቶች ፤ ጫናዎች ፤ጭቆናዎች እንደተጠበቁ ሆነዉ ማለታችን ነዉ።

   ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የተለያዩ የልዩነት ክስተቶች ቢንጸባረቁም ህዝቡ ግን ችግሮቹን ወደ ጎን በማድረግ ከሀይማኖት ዉጭ እንዲሆኑ ትግል ሲያደርግ ቢቆይም በአሁኑ ወቅት ግን ይዘቱን ቀይሮ የመጣዉ ለችግሮች ሁሉ መነሻዉ ሀይማኖት እንደሆነ የሚዘምሩ አካላት እየተበራከቱ ይገኛል።

   የታዋቂዉ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በግፍ መገደልን ተከትሎ በሀገሪቱ በተከሰተዉ አለመግባባትና ብጥብጥ የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ህይወት እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልኩ አልፏል። ለሟቾች ነብስ ይማር እያልን ለቤተሰቦቻቸዉና ለመላዉ ኢትዮጵያዉያን መጽናናትን እንመኛለን። በሌላ መልኩ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉ ንጹሀን ዜጎች እንዲሁም የወደመዉ የሀገር ንብረት ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር የጉዳዩ አስከፊነት ስፋቱን ይጠቁማል።

   መንግስት ባለበት ሀገር እንደዚህ አይነት ልቅ የሆነ ስርዐተ አልበኝነት ሲፈጠር መንግስት አለን ? ያስብላል። መንግስት ሆይ የታሰሩ አካላት ፈጣን ፍትህ እንዲያገኙና መፈታት ያለባቸዉ አካላትም ያለምንም መጉላላት በህግ የበላይነት መፍትሄ ሊቸራቸዉ ይገባልም እያልን በሌላ መልኩም የጥላቻ ንግግር የሚያስተጋቡ አካላትን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የማስቆም ሀላፊነቱን እንዲወጣ አደራ እንላለን። 

   ችግሩ የተከሰተበትን መንስኤ በማጥናት መፍትሄ መሻት ሲገባ አንዳንድ የግል ዓላማ ያላቸውና እስላም ጠል የሆኑ ጽንፈኛ አካላት የጉዳዩን አቅጣጫ ለማስቀየር የተለያዩ የዜና ማሰራጫ ዘዴዎችን በመጠቀም ጸረ ሰላም ብሎም ጸረ ኢስላም የሆነ ፕሮፓጋንዳቸዉን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ። በእምነት ተቃርኖ የማያዉቀዉ የሀገራችን አማኞች በእምነታቸዉ ከተመጣባቸዉ ሁሌም ቢሆን ወደ ኋላ የማይሉ እንደሆነ ስለሚያዉቁ በሌሎች ነገሮች ሁሉ ሞክረዉ አልሳካ ቢላቸዉ መጨረሻ ላይ ህዝቡን በእምነት ለማጋጨት ሌት ተቀን እየዳከሩ ይገኛሉ።

   በድር ኢትዮጵያ የማንኛዉም ቤተ እምነት ወይም ተቋም ሲደፈር በጽኑ ተቃዉሞዉን ያሰማል ። የእምነት ተቋማት ሊከበሩ ስለሚገባም ጭምር ነዉ። አንዱ ተቋም ከአንዱ አይበልጥም ፤ የትኛዉም ተቋም ከማንኛዉም አያንስም ፤ በእምነት ተቋምነታቸዉ ሁሉም እኩል ናቸዉ። ይህንን መገንዘብ የተሳናቸዉ የጽንፍ አራማጆች ግን በእምነቶች መካከል ጣልቃ በመግባት እኔ አዉቅልሀለሁ አባዜያቸዉን በመንዛ

ሙስሊሙን ማህበረሰብ ለማሸማቀቅ በሚያስችል ደረጃ የችግሩ አካል ለማድረግ ብዙ ለፍተዋል። ሆኖም ግን አይሳካላቸዉም ። ሙስሊሙ ማህበረሰብ የማንም አካል ተቀጥላ ሆኖም አያዉቅም ፤ መብቱን ለማስከበር ደግሞ ማንም ሊነግረዉ አይችልም በቂ ተሞክሮም አለዉ።

   በሀገሪቱ የመጣዉን አንጻራዊ ለዉጥ ያልተዋጠላቸዉ ለዉጡን  ለመቀልበስና ዳግም ላይመለስ ያከተመዉን የአጼዎችን ስርአት ለማንገስ ለሚድሁ ያለን ምክረ ሀሳብ ሀገራችን በተያያዘችዉ የለዉጥ ጎዳና የሚያራምዳት እንጂ ለነዉጥ የሚዳርጋትን ስለማትሻ ከእኩይ ተግባራችሁ እንድትቆጠቡ እያልን የሰላም ሰባኪ በመምሰል በህዝቡ መካከል አሉባልታ የሚነዙና ጽንፈኝነትን የሚያራምዱ አካላት ከሚያስቡት ባልታሰበ መልኩ በተቃራኒዉ ብዙ አላስፈላጊ ዋጋ ሊያስከፍላቸዉ ይችላልና ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት ለህዝቦቿ አንድነት እንዲሁም ለሰላም ሲባል ቆም ብላችሁ እንድታስቡ መልካም መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን። 

   በአማራ ክልል በሞጣ የሚገኙ አራት መስጂዶችን አቃጥሎ የሙስሊም ማህበረሰብ ድርጅቶችን በመለየት በማዉደምና ንብረታቸዉን በመዝረፍ እሳት እየሞቁ ይጨፍሩ የነበሩትን የስነ ምግባር ሞራል የጎደላቸዉን ኢስላም ጠል ጽንፈኞችን ለመገሰጽ እንኳ የሞራል ብቃት ያጡ አካላት አሁን በሀገሪቱ በተከሰተዉ ብጥብጥ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በሞተበትና ንብረቱ የወደመበት ሆኖ ሳለ የግል ድብቅ አጀንዳቸዉን ለማሳካት በበሬ ወለደ ትርክታቸዉ የእምነት ጥቃት አድርጎ ክፍፍልን መዝራት ፍጹም ተቀባይነት የሌለዉ እኩይ ተግባር ነዉ።

   ስለዚህ እየተካሄደ ያለዉ አላስፈላጊ ቅስቀሳ ህዝቡን ከማበጣበጥ ፤ ሀገር ከማፈራረስ እና በህዝቦች መካከል ሊፈታ የማይችል ጠባሳ ከማኖር ውጭ እንደ ሀገር እና ህዝብ የማያስተሳስር ለሰላምና ፍትህ ያልቆመ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እንደ እምነትም ቢሆን በየትኛዉም የእምነት አስተምህሮት የማይደገፍ አጸያፊ ተግባር መሆኑን በመረዳት ሁሉም ሊገነዘበዉ የሚገባና ማንኛዉም አካል  ከዚህ መሰል ሂደት ጥፋትን እንጂ ትርፋማነትን ማሰብ እንደማይገባ በቅጡ መገንዘብ ያሻል።

       በመጨረሻም ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የምናስተላልፈዉ መልእክት ኢስላም ሰላም እንደመሆኑ መጠን ለሰላም መከፈል የሚገባዉ ዋጋም እንደተጠበቀ ሆኖ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክሮ መገኘት እና በጽንፈኞች ለሚሰነዘሩብን የዉሸት ፕሮፓጋንዳ ለኛ አዲስ ባለመሆኑ ትኩረት ባለመስጠት የሚቃጣብንን በጥበብ በሰከነ መንፈስ እንደ ሀገር በማሰብ የመመከት ሀይል ማዳበር ለሰላም ዘብ መቆም ግድ ይላል እንላለን።   

ሀገራችንን ፈጣሪ  አላህ (ሱ.ወ) በሰላም ይጠብቅልን  !!!                                 

በድር ኢትዮጵያ       ሰሜን አሜሪካ       ጁላይ 24 , 2020                              

Leave a comment

All comments are moderated before being published