ሱልጣን ሀንፈሬ ዓሊሚራህ ወደ አኼራ ሄዱ

                          ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂኡን    

   ሱልጣን ሀንፈሬ በአሳይታ ከተማ ተወልደዉ በአዲስ አበባና በአሜሪካ ትምህርታቸዉን ሲከታተሉ ቆይተዉ በኋላም ወደ ሀገራቸዉ በመመለስ ከአባታቸዉ ጎን በመሆን አገራቸዉንና ወገናቸዉን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። አባታቸዉም “ እንኳን እኛ ግመሎቻችንም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያዉቃሉ’’ በማለት ሀገር ወዳድነታቸውን በዚህ መልኩ ገልጸዉታል። ወላጅ አባታቸዉ ሱልጣን አሊሚራህ ሲሞቱም ሱልጣኔነቱን ተረክበዉ ቆይተዋል።

   የ1966 ቱ ወታደራዊዉ መንግስትም ስልጣኑን ተረክቦ ሶሻሊዝምን ማራመድ በጀመረበት ወቅት ተቃዉሞአቸዉን ቀጥለዉ የአፋር ነጻ አዉጪ ግንባርን በማቋቋም እስከ 1983 ድረስ የትጥቅ ትግል ሲያካሄዱም ቆይተዋል። በወቅቱም የተደረገዉን የመንግስት ለዉጥ ተከትሎ ወደ አገራቸዉ ለመመለስ በቅተዋል።  

   ከ2001 እስከ 2006 በኩዌት የኢትዮጵያ መንግስት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን እያገለገሉ ሳለ  በጊዜው በስልጣን ላይ ከነበረዉ የኢህአዲግ መንግስትም ጋር አብረዉ መስራት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸዉ ድጋሚ ለስደት ተዳርገዋል።

    በሀገራችን ኢትዮጵያ የሙስሊሙ ማህበረሰብ የመብት እንቅስቃሴ “ድምጻችን ይሰማ ‘’ በሚል መርህ  በተነሳበት ወቅት እንቅስቃሴዉን በተመለከተ የነበረዉን የተዛባ ዜናን ለማረም በወቅቱ የበድር አመራሮች   በስደት ከሚኖሩበት ከዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ተገኝተዉ የበኩላቸዉን ትብብር እንዲያደርጉ በተጠየቁት መሰረት ተጽእኖ ፈጣሪነታቸዉን በመጠቀም ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ዉይይት ሳቢያ የትግል እንቅስቃሴዉ  በአልጀዚራ ጥሩ ሽፋን እንዲያገኝ አስችለዋል።

  እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ2010 የተከሰተዉን ለዉጥ ተከትሎ ዳግም ወደሀገር ተመልሰዉ እስከ ህይወታችዉ ፍጻሜ ድረስ አገራቸዉን በታማኝነት እና በቅነንት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በድር ኢትዮጵያ በእርሳቸዉ ዜና ህልፈት የተሰማዉን መሪር ሀዘን እየገለጸ ነፍሳቸዉን አላህ በጀነተል ፊርደዉስ እንዲያኖራት እየተማጸንን ለቤተሰቦቻቸዉና ለመላዉ ህዝብ መጽናናትን እንመኛለን ።

በድር ኢትዮጵያ     ሰሜን አሜሪካ     ሴፕተምበር 20  2020

 

Leave a comment

All comments are moderated before being published