መፍትሄ ያጣዉ የንጹሀን ዜጎች እልቂት

መፍትሄ ያጣዉ የንጹሀን ዜጎች እልቂት

    በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የንጹሀን ዜጎች ህይወት ያለምንም ሰብአዊ ርህራሄ ዘግናኝ በሆነ መልኩ ሲቀጠፍ መስማት፤ ማየት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ መገንዘብ አቅቶን ነዉ ወይንስ አለመታደል ብለን እንለፈው? ሁሉም አካላት በራሳችዉ መሰል ድርጊቶችን ቢያወግዙም ሊታቀብ ያልቻለ ዘግናኝ ኢሰብአዊ ጥፋት በንጹሀን ዜጎች ላይ ቀጥሏል ።

   ንጹሀን ዜጎች በሀገራቸዉ ያለምንም ከልካይ በነጻነት መንቀሳቀስ ሲገባቸዉ ለመሸማቀቅ፤ ለመጨነቅ መዳረጋቸዉ ብሎም ፍትህን እየናፈቁ መንከራተትን ሁሉም ዜጋ ትኩረት ሰጥቶ ቆም ብሎ በማሰብ ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ በመስጠት ሊያስብበት የሚገባ ዋነኛዉ መፍትሄ የሚሻ ሀገራዊ ጉዳይ ነዉ። 

  በምዕራብ ወለጋ በጉሊሶ ወረዳ የተካሄደዉ የንጹሀን ዜጎች ጅምላ ጭፍጨፋ መልስ ያጣ ዘግናኝ ድርጊት በምን መልኩ ማዉገዝ እንደሚገባ እንኳ ለመግለጽ ይቸግራል። የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ በስልጣን ላይ ያለዉ የመንግስት አካል ለህዝቦች ልዕልና ካልቆሙ መገምገሚያቸዉስ ምን ይሆን? የሚለዉም ወሳኝ ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይገባል እንላለን።

   በድር ኢትዮጵያ ይህን መሰል ዘግናኝ የንጹሀን ዜጎች እልቂትን ሁሌም ሲያወግዝ ያለ ሲሆን መቼም ቢሆን በምንም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው ኢሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ በድር ኢትዮጵያ በጽኑ ያወግዛል። ከማንም በላይ መንግስት ሀላፊነት ያለበት በመሆኑ ለዜጎች መታደግ ተጠያቂነቱን ሊወስድ ይገባል፤ ዳግም ችግሮቹ እንዳይከሰቱም ዘላቂ መፍትሄ መሻትንም ይጠበቅበታል። 

   ዉድ ኢትዮጵያዉያን ችግሮቻችን ከመብዛታቸዉ አኳያ አይነታቸዉን እየቀያየሩ በመምጣት በተለይ በንጹሀን ዜጎች ህይወት ላይ ያንዣበበዉ አደጋ ሀገሪቱን ወዴት እየወሰዳት እንደሆነ በመገንዘብ ችግሮችን ከማባባስ እንዲሁም ከመደጋገም ይልቅ አማራጭ መፍትሄዎች ላይ ትኩረት እንድናደርግ ለማስገንዘብ እየወደድን በተለይ የመንግስት አካላት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ መሻት እና ጭፍጨፋዉን የፈጠሩ አካላትን በማደን ለህግ ማቅረብና ለህዝቡም ግልጽነት ባለዉ መልኩ ማሳወቅ እንደሚጠበቅበት ለመጠቆም እንወዳለን።

አላህ (ሱብሁዋነሁ ወተዋላ) ሀገራችንን ይጠብቅልን

በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ     ኖቨምበር 3 2020                      

Leave a comment

All comments are moderated before being published