መጅሊሱን በማጠናከር ሂደት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል

Posted by Badr Ethiopia on

መጅሊሱን በማጠናከር ሂደት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል

     የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት (መጅሊስ) ራሱን ችሎና ተጠናክሮ የተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ ባለመገኘቱ የተነሳ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በተረጋጋ መንፈስ እምነቱን በሰላማዊ መንገድ እንዳይተገብር እና በሀገራዊ  ልማትና እድገት በጉልህ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳይሆን ችግር ሆኖ በመቆየቱ ሳቢያ አሉታዊ ተጽዕኖ በማህበረሰቡ ላይ ማሳደሩ ይታወቃል። 

     በሀገራችን እየተካሄደ ባለዉ ለዉጥም ሙስሊሙን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ያደረጉ አንጻራዊ በጎ ጅማሮዎች የሚታዩ ቢሆንም  ለዉጡን እንደ ዜጋ ከመጠቀም አኳያ ብዙ ርቀት መጓዝ አልተቻለም ። በተለይ በመጅሊሱ አካባቢ ባሉ የአመራር አካላት መካከል   በተፈጠረዉ አላስፈላጊ ክፍተቶች ሳቢያ ሙስሊሙን ማህበረሰብ በተፈለገዉ መጠን ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም። 

    የችግሩን ስፋት ከግምት ዉስጥ ያስገቡ በርካታ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ባለድርሻ አካላትም አቅማቸዉ በፈቀደ ሁሉ መጠነ ሰፊ ጥረቶችን እያከናወኑ እንደሆነም ይታወቃል። በተያያዥነት በሰላም ሚኒስትር በኩል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችም እጅጉን አበረታች መሆናችዉ የሚታወቅ ሲሆን በቀጣይ አስር ቀናት ዉስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ቀደም ሲል ሚያዝያ 23/2010 በጸደቀዉ የስምምነት ሰነድ መሰረት ምርጫ ተካሄዶ አፈጻጸሙም እስከታች የመዋቅር አካላት በማዉረድ ተግባራዊ እንዲሆን በሰላም ሚኒስትር በኩል አቅጣጫ እንደተቀመጠ ተሰምቷል።

    የተቀመጠዉ የመፍትሄ ሀሳብ የሚያበረታታ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት በመጅሊሱ አካባቢ እየታዩ የነበሩ የስራ ሂደቶች ሲገመገሙ ተስፋዉን በመጅሊስ አመራር አካላት ላይ ብቻ መጣሉ ተገቢ ስለማይሆን እየተከናወነ ያለዉ ሂደትም ዉጤት ላይ እስኪደረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ የተጀመረዉም እንቅስቃሴ ሳይቋጭ ዳግም መንገድ ላይ ተንጠልጥሎ እንዳይቀር ጠንከር ያለ ክትትል የሚያስፈልገዉ ሆኖ አግኝተነዋል ። ስለዚህ የሚመለከታቸዉ አካላት ሁሉ ያለመታከት ተከታትሎ የማስፈጸም ሂደት እንደተጠበቀ ሆኖ በሰላም ሚኒስትርም በኩል በተጀመረዉ መንገድና በተቀመጠዉ የስራ አቅጣጫ መሰረት ለዉጤት እንደሚያበቁት እምነታችን የጸና ነዉ። መላዉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ መጅሊስ በፍትሃዊነት እና በጠንካራ መሰረት ላይ እስኪዋቀር ድረስ በአንድነት እና በጽናት በመቆም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪያችንን እያቀረብን በድር ኢትዮጵያም ጉዳዩን በልዩ ትኩረትና በቅርበት እንደሚከታተለዉ ለመግለጽ እንወዳለን ።  

በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ    ፌብሩዋሪ 12 2021


← Older Post Newer Post →