መልካም ተግባር በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል

መልካም ተግባር በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል

   በሀገራችን ለረጅም ዘመናት መልስ ካጡ ጉዳዮች በከፊል ለዉጤት እየበቁ ወይንም ምላሽ እያገኙ መሄዳቸዉ አበረታች ተግባር በመሆናቸዉ ሊበረታቱ ይገባል እንላለን። በተለይ የሙስሊሙ ማህበረሰብ መሰረታዊ ጥያቄ ሆነዉ አስተዋሽ ተነፍጎአቸዉ ሲንከባለሉ የነበሩት ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎች ዋነኛዎቹ ናቸዉ።

   በ2007 እኤአ የበድር ልዑካን ቡድን በበርካታ ጉዳዮች ጥናታዊ ጽሁፍ አዘጋጅቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ለሚመለከታቸዉ የመንግስት ከፍተኛ አካላት ሲያቀርብ የፋይናንስ ተቋማትን በተመለከተ  “ ከሙስሊም ባህል አኳያ የተቀረጹ የፋይናንስ ተቋማትም አስፈላጊ በመሆናቸዉ ማደራጀት እና ከወለድ ነጻ የሆኑ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ቢቋቋሙ ከሁሉም በላይ ወለድ ዉስጥ ላለመግባት ከኢንቨስትመንት የታቀቡ ዜሆችን በልማት ለማሳተፍ አይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል ፤ ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገዉ ጥረትንም ያግዛሉ ። በዚህ ዘርፍ ለመስራት ለሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶችን እንዲያበረታታ’’ በሚል መጠየቁ ይታወቃል።

   ሆኖም ጉዳዩ ትኩረትን አግኝቶ የነበረና ለረጅም ጊዜ ለስኬታማነቱ ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩ በዘርፉ የሙያዉ ባለቤቶች እና ሙስሊሙ ማህበረሰብ ያላሰለሰ ጥረት በዛሬዉ እለት ለስኬት የበቃዉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ተግባራዊ በመሆኑ እጅግ ደስ ብሎናል እናንተም እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን።    

    ዘምዘም ባንክ በሀገራችን የመጀመሪያዉ  ከወለድ ነጻ ባንክ ሆኖ መመስረቱ እጅጉን አስደስቶናል። ለበርካታ ዓመታት በቁርጠኝነት ታግለዉ እዉን በማድረጋቸዉ ያሳያችሁት ጽናት ለወደፊቱ  የስራ ጊዜያችሁ ጥንካሬ ጠቋሚ ነዉና መልካሙን ሁሉ እንዲገጥማችሁ ከልብ እንመኛለን። ጅማሮው አስደሳች በመሆኑም  ሌሎችም ተመሳሳይ ባንኮች በቅርቡ አስፈላጊዉን መስፈርት አጠናቀዉ ወደ ስራ እንደሚገቡም እንተማመናለን።

     በሌላ መልኩ በዚሁ እለት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሚያስተላልፋቸዉ ዝግጅቶች የአረብኛ ቋንቋን ከሰኞ እስከ አርብ በየቀኑ ለአንድ ሰዓት በቋሚነት እንደሚያስተላልፍ ማስተዋወቁና የሙከራ ስርጭቱን በዛሬዉ እለት መጀመሩን ይፋ አድርጓል። እንደተገለጸዉም ለሀገር እድገት ፤ ለስራ እድል እንዲሁም ለመልካም ግንኙነት እጅጉን ጠቃሚ ነዉ ። በቀጣይ ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግም በትምህርት ቤቶች ደረጃ እንደሚሰጥ በሚጠበቀዉ የአረብኛ ቋንቋም ሳቢያ ለወደፊቱ ፕሮግራሙ በተሻለ መልኩ ይታገዛል ብለን እናምናለን።

    በድር ኢትዮጵያም ለተጠቀሱት ስኬቶች የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም ተወዝፈዉ ከተቀመጡብን በርካታ ችግሮች አንጻር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን በማመን ለሀገራችን ብሎም ለህዝባችን ሁለንተናዊ እድገት ብዙ መስራት ይጠበቅብናልና ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን በማስወገድ አንድነታችንን በመጠበቅ ሳንዘናጋ ለበለጠ ድል እንዘጋጅ እንላለን።       

አላህ (ሱብሁዋነሁ ወተአላ) ሀገራችንን ይጠብቅልን

Leave a comment

All comments are moderated before being published