ለጸጥታዉ ምክር ቤት ጥያቄ ቀረበ

Posted by Badr Ethiopia on

    የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተያዘለት መርሀ ግብር መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆን በድር ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም ያለዉ ሲሆን ይህንኑ በህብረተሰቡ ዘንድም በቂ እዉቀት እንዲኖር ለማስቻል ከግድቡ ጋር በተገናኘ መጠነ ሰፊ ስራ የሚሰሩ ወንድሞቻችንን በመጋበዝ በተለይ ክቡር አምባሳደር ፍጹም አረጋ በአሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር በተገኙበት ጀግናዉ መሀመድ አል አሩሲ እና ኡስታዝ ጀማል በሽር እንዲሁም ሌሎች አክቲቪስቶችን ባካተተ መልኩ ሰፊ ዉይይት መደረጉ ይታወሳል።

   በወቅቱ ከቀረቡ ወሳኝ ሀሳቦችም መካከል በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶዋቸዉ ፈጣን ምላሽ ያገኙ በአረብኛ ቋንቋ በቴሌቭዢን ፕሮግራም ስለ ህዳሴ ግድቡ መተላለፉና በዘርፉ የተሳተፉ አክቲቪስቶችን ማሰባሰብ የመሳሰሉ ተግባራት ተፈጻሚ መሆናቸዉ እጅጉን አስደስቶናል።   

   በአሁን ወቅት ከግድቡ ጋር ተያይዞ በቀጣናዉ ባሉ ሀገራት መካከል ያለዉን ብዥታ ለማጥበብ በተለይ የኢትዮጵያን አቋም በግልጽ ለማሳወቅ ሁሉም ዜጋ የራሱን ጥረት ማድረግ የሚጠበቅበት ሲሆን በድር ኢትዮጵያም ይህንኑ በተመለከተ ሰፋ ያለ ትንተና የያዘ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታዉ ምክር ቤት ለአምስቱ ቋሚ አባላት እና ለአስር ተመራጭ አባላት በጥቅሉ ለአስራ አምስቱም የጸጥታዉ ምክር ቤት አባላት፤ ለአዉሮፓ ህብረት ፤ ለአፍሪካ ህብረት እና ለእስላማዊ ትብብር ድርጅት በየኢሜይላቸዉ ስለ ህዳሴ ግድቡ ፍትሃዊ አፈጻጸም አስመልክቶ ደብዳቤ የተላከ ሲሆን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት አካላትም እንዲያዉቁት ተደርጓል።

   የግድቡ ዉሀ ሙሌት በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት መፈጸሙ ደግሞ የህልዉናችን ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ዜጋ በሚችለዉ አቅም ሁሉ የግድቡን ትክክለኛዉን ይዘትና ገጽታ ብሎም ፍትሃዊ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ለዓለም ማህበረሰብ በምናገኛቸዉ አጋጣሚዎች ሁሉ በመጠቀም ማሳወቅ እንደሚጠበቅበን ለመጠቆም እንወዳለን ።

አላህ (ሱብሀነሁ ወተአላ) መልካሙን ዜና ያሰማን  አሜን !

በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ     ጁን 29 2020                           


← Older Post Newer Post →