ለክቡር አምባሳደር ፍጹም አረጋ

 

 በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ


ከበድር ኢትዮጵያ

ለክቡር አምባሳደር ፍጹም አረጋ
ለኢትዮጵያ ፌድራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኤምባሲ
ዋሽንግተን ዲሲ 

ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉንም ባስደነቀ የለዉጥ ሂደት ላይ እንደምትገኝ ግልጽ ነዉ። ይህ ለዉጥ እዉን እንዲሆን በርካታ ሀገራችን ህዝቦች ዉድ ዋጋ ብሎም ብዙ መስዋእትነት የከፈሉለት መሆኑም ሊዘነጋ የሚችል አይደለም። እንደሚታወቀዉ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ለሰብአዊ መብታቸዉ እና ለእምነት ነጻነታቸዉ መከበር በግንባር ቀደምትነት በመቆም በሰላማዊ ትግል መርህ መሰረት ለመብት መከበር በአንድነት እና በጽናት እንዴት መቆም እንደሚቻል ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ማድረግ በመቻላቸዉ ድንቅ ምሳሌ ለመሆን በቅተዋል ።

ከለዉጡ ማግስት ጀምሮ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በሁሉም መስክ የለዉጡ አካልና አጋዥ በመሆን እንደ ዜጋ የሚጠበቅበትን ሁሉ በማድረግ የዜግነት ግዴታዉን እየተወጣ ይገኛል። ሀገራችንን ከመሩ መሪዎች በተለየ ሁናቴ በሁሉም ዜጎች በሚባል መልኩ ቅቡልነት ያገኙት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከህዝበ ሙስሊሙ ተወክለዉ የመብት ትግሉን በመምራታቸዉ ብቻ ያለአግባብ በወንጀል ተከሰዉ ብዙ ስቃይና እንግልት ያስተናገዱትን መሪዎቻችንን አቅርበዉ ለማወያየት በመቻላቸዉ እና የሙስሊሙን ችግር አጥንተዉ በማቅረብ ለመፍትሄዉ እንዲንቀሳቀሱ ዘጠኝ አባላት የሚገኙበት የተቋማዊ ለዉጥ የጋራ ኮሚቴ ማቋቋማቸዉን ስንመለከት የሙስሊሙ ህብረተሰብ ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቅርብ ይፈታል ብለን ትልቅ ተስፋ ሰንቀን ነበር።

ክቡር ጠ/ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የዲያስፖራዉን ማህበረሰብ ለማወያየት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በመጡ ጊዜም በሰዓቱ ይካሄድ በነበረዉ 18 ኛዉ የበድር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ጉባኤ ላይ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ከክቡር ኦቦ ለማ መገርሳ እና በወቅቱ ከነበሩት አምባሳደር ክቡር ካሳ ተክለብርሀን ጋር በመሆን ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ባደረጉት ዉይይት የተገነዘብነዉ ከአሁን ቀደም ከነበሩት መሪዎች በሙሉ የተለዩ እና አቃፊ መሆናቸዉን ነበር። ለዛም ከፍ ያለ ክብርና ምስጋና እናቀርባለን ። 

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከሰማናቸዉ ብዙ ፍትህን አንጋሽ ፤ አነቃቂ ንግግሮችን እንዲሁም ካየናቸዉ እንቅስቃሴዎች በመነሳትሙስሊሙ ህብረተሰብ ትልቅ ተስፋን ቢሰንቅ ሊያስመሰግነዉ እንጂ በጭራሽ ሊያስወቅሰዉ አይችልም። ሆኖም ግን እያደረ ቀረበ ስንለዉ እየራቀ፤ ሊደረግ ነዉ ስንል እየተሰረዘ ለዘመናት በጭቆና የሚንከባለለዉ መሰረታዊ መብታችንን ለማስከበር የመንግስታችን ፍላጎት እስከምን ድረስ ነዉ ብለን እንድንጠይቅ ተገደናል።

ለሀገራችን ሰላምና ለተጀመረዉ በይቅርታ ላይ የተመሰረተ ሽግግር እንዳይሰናከል በማሰብ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ወነጅሉና በሀሰት ምስክርነት ያለፈዉን ጨቋኝ ስርዐት ሲያገለግሉ የኖሩትን የመጅሊስ ሹማምንት የመፍትሄ አካል ማድረግ በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ የማይጠበቅ የነበረ ቢሆንም እጅግ ሰላም ወዳድና በሳል የሆኑት መሪዎቻችን ሀሳቡን ተቀብለዉ ንቀሳቀሱም ሌሎች ግን ችግሩን ከማባባስ ሊታቀቡ ያልቻሉት እና መንግስትም በቸልታ ሊመለከታቸዉ ለምን ቻለ ብለን እንድናስብ አድርጎናል። 

ክቡር አምባሳደር ከሀገራችን መሪዎች በተለይ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ጋር በመነጋገር የሙስሊሞች የዘወትር ጥያቄ ከሆኑት አንዱ የሆነዉ የሙስሊሙ የእምነት ቤት ሆኖ ለሙስሊሙ መብትና ጥቅም እንዲሰራ የሚጠበቅበት መጅሊስ መቼ ነዉ እዉን የሚሆነዉ? የመጅሊስ አመራሮች ወደ ፈጣሪያቸዉና ወደ ህዝብ ተመልሰዉ እራሳቸዉን ያርማሉ ተብሎ ሲጠበቅ ማንና ምንን ቢተማመኑ ነዉ የሙስሊሙን አንድነት በመፈታተን ለመዝለቅ የመረጡት እንድንል መገደዳችን በድር ኢትዮጵያ ዓለም የሙስሊሞች ድርጅት ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደናል። 

በመጨረሻም ክቡር አምባሳደር በጉዳያችን ላይ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር መምከር አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በተለያዩ ስቴቶች የሚገኙ የእህት ማህበራት አባሎቻችንም ሆነ በዲያስፖራ ለምንገኝ ብሎም ሀገራችን የሚገኙ ሙስሊም ማህበረሰብ የረጅም ዘመናት ጥያቄያችን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለዉጤት እንደሚበቃ ተስፋ ማድረግ ነዉ ።

አላህ ለፍትህ የሚቆሙትን ሁሉ እንዲረዳ እንማጸናለን 

በድር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት
ሰሜን አሜሪካ
አፕሪል 2 2019

Badr Ethiopia | Washington, DC, United States EIN: 90-0432681


 

Leave a comment

All comments are moderated before being published