የጋራ አቋም መግለጫ

የጋራ አቋም መግለጫ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ
እንደሚታወቀው በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዘርፈ ብዙ የሆነውን የማህበረሰባችንን ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ተደራጅተን ስንንቀሳቀስ ቆይተናል፡፡ በመካከላችን ማጎልበት የምንፈልገውን መንፈሳዊ ትስስር በሚያሳድጉ ስራዎች ላይ ከማተኮራችን በተጨማሪ በሀገርቤት ሙስሊሙን ማህበረሰብ በሚመለከቱ እና አጠቃላይ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የድርሻችንን ለመወጣት ስንጥር ቆይተናል፡፡ እነዚህን የመሰሉ ክንዋኔዎችን በተደራጀ መልኩ ለመስራት በምናደርገው ጥረት በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደቻልነው ሁሉ በረጅም ዓመታት ጉዟችን ውስጥ የአካሄድ ልዩነቶች እየተፈጠሩ ሂደታችን ሲገታ እና በመካከላችን ቅራኔዎች ሲፈጠሩ መቆየታቸውም አልቀረም፡፡ እነዚህን ክፍተቶች በግዜ ለማጥበብ የተደረጉ የውስጥ ጥረቶች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ባለመቻላቸው በማህበረሰባችን ጉዳይ ላይ ልናበረክት የምንችለውን አስተዋፅኦ ከማስተጓጎሉ በላይ አብሮ የመስራት ተነሳሽነትን ጎድቶ መንፈሳዊ ትስስሮችንም ወደማላላት እየተጠጋ የመጣበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ 
ይህን ችግር ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመፍታት በፈርስት ሂጅራ 30ኛው ዓመት ክብረ በዓል ጀምሮ በ18ኛው የበድር ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ጎን ለጎን በቀላሉ ሊቀረፉ ያልቻሉ የውስጥ ችግሮቻችንን ዋና ምክንያት በመለየት ዳግም እንዳይከሰቱም መፍትሄ ማግኘትን ታሳቢ ያደረገ ጥረት ተደርጓል፡፡ ይህ ጥረት በተለይም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ ኡስታዝ ነቢዩ አያሌው እና ኡስታዝ በድሩ ሁሴን አወያይነት በድር ኢትዮጵያ፣ ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን፣ ሠላም ፋውንዴሽን እና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊ ህብረትን ያካተተ የአራትዮሽ ውይይት እና ሽምግልና ተካሂዷል፡፡ ሂደቱም በጣም ጥልቀት የነበረውና በድርጅቶቹ መካከል ለተፈጠሩት ክፍተቶች ዋና ዋና መንስኤዎች በዝርዝር ተለይተው፣ በያንዳንዳቸው ላይ አጥጋቢ ውይይት ተካሂዶባቸው የችግሮቹ መንስኤዎች፣ የፈጠሩት ተፅእኖ እዲሁም ሊቀረፉ የሚችሉባቸው ስልቶች ላይ በጋራ ምክክር ተደርጓል፡፡ 
በዚሁ መሰረት የማህበረሰቡን ስነልቦና ለማደስና ማህበረሰቡ ያለውን ሀይል ወደፊት ሊሰሩ በሚገባቸው ስራዎች ላይ እንዲያውል ለማድረግ ያለፉ ቁርሾዎችና ክስተቶች ከዚህ በኋላ አጀንዳ ተደርገው እንዳይነሱ፤ ከዚህም ባለፈ በድርጅቶቹ መካከል ቅራኔ የሚፈጥሩ ከየትኛውም ወገን የሚቀርቡ አነረድነትን አፍራሽ ሀሳቦች በቅድሚያ በቀጥታ የሚመለከተው አካል በተጨማሪም ድርጅቶቹ በጋራ ሆነው የማስተካከል ኃላፊነት እንዲወስዱ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በድርጅቶቹ መካከል የተሻለ መተማመን ለመፍጠርም አሉታዊ ሀሳቦችና ተግባራት ሲታዩ ድርጅቶቹ አባላቶቻቸውን በመምከር በመካከላቸው ያለውን ትስስር በመተማመን ላይ ተመስርቶ እንዲጠናከር በሚያስችል መስመር እንዲጓዙ ሁሉም ወገን ስምምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ 
ስምምነቱን ዘላቂ ለማድረግ እንዲሁም የድርጅቶቹን አቅም ለማሳደግ በባለሙያዎች በሚዘጋጅ ጥናት ላይ በመመርኮዝ ድርጅቶቹን በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችሉ መዋቅራዊ ለውጦች እንዲደረጉም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በተበታተነ መልኩ ውጤታማ ስራ ለመስራት እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን በመቅረፍ ሁሉም ድርጅቶች በጋራ አዲስ ምዕራፍ ከፍተው አርአያ የሚሆኑ የማህበረሰብና የልማት ድርጅቶችን በሚመጥን ደረጃ እንዲንቀሳቀሱ በሚያስቸል ሁኔታ እንዲሰሩ የሚያመቻች አስተባባሪ አካልም በሁሉም ድርጅቶች ስምምነት በጋራ ተሰይሟል፡፡ 
በመጨረሻም በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን እና ድርጅቶቻቸውን አንድነት በመመኘት ይህንን እውን ለማድረግ ሲደክሙ ለቆዩ በዚህ በአሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰባችን አባላትን ማመስገን እንፈልጋለን፡፡ በተለይም የውስጥ ጥረቶቹ በሂደት እያደጉ መጥተው ፍሬ እንዲያፈሩ የማሳረጊያ ውይይቱ እና ድርድሩን በኃላፊነት ስሜት የመሩትን ኡስታዝ ኢንጂነር በድሩ ሁሴንን፣ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበክርን እና ኡስታዝ ነቢዩ አያሌውን እንደዚሁም በተለያዬ ጊዜ ይህንን እርቅ ዕውን ለማድረግ ጥረት ስታደርጉ የቆያችሁ ወገኖቻችንን ከልብ ማመስገን እንፈልጋለን፡፡ የሁሉም ወገኖች ፍላጎት የሆነውና ብዙ ጥረት የተደረገበት የዳግም አንድነት የመገንባት ስኬት ዘላቂ ሆኖ ለማህበረሰባችን እና ለሀገራችን ጠቃሚ ስራ እንዲሰራ የሁሉም ኮሚኒቲ አባላትና አመራሮች ርብርብ እንዲያደርጉ በአላህ ስም እንጠይቃለን።
አላህ ሱ.ወ. ወደ ቀጥተኛዉ መንገድ ይምራን 
በድር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት 
ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን 
ሠላም ፋውንዴሽን 
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊ ህብረት

ሰሜን አሜሪካ 
ኦገስት 1 2018

Leave a comment

All comments are moderated before being published