በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ    

 ለዓላማ ስኬት በጽናት እንቁም

      በሀገራችን ኢትዮጵያ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አንግቦ የተነሳዉ እምነትን በነጻነት የመተግበርና ህገመንግስታዊ መብትን ሳይሸራረፍ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ በይፋ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል። በነዚህ ወቅቶችም በርካታ ፋይዳ ያላቸዉ ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም በአንጻሩ የተከፈለዉ መስዋእትነትም የትየለሌ ነዉ። ይህም የሚያሳየዉ በትግሉ ጉዞ ዉስጥ በህዝበ ሙስሊሙም ሆነ በመሪዎች ላይ በደረሰዉ የእስር፤ የመሰደድና የድብደባ ሰቆቃ በተፈራረቀበት ወቅትም እንኳ ቢሆን ከመርሁ ሳይዛነፍ ቆይቷል።

     በድር ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅትም ሰላማዊ እንቅስቃሴዉ ከመጀመሩ በፊትም ይሁን በኋላ አቅም በፈቀደ ሁናቴ የኡማዉ አካል በመሆን በአጋርነት ተሳትፎዋል ፤ ሰላማዊ መፍትሄ በመሻትም ሩቅ ርቀት ተጉዟል። በቅርቡ ከመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችን ‘’አቋምን በግልጽ ስለማሳወቅ በሚል የወጣዉ መግለጫም ይህንኑ የሚያስገነዝበን ሲሆን ድርጅታችንም በዚሁ በተቀየሰዉ መንገድ ሲጓዝ እንደነበር ለመግለጽ እንወዳለን።

     ህብረተሰቡም  ይህንኑ በግልጽ ተገንዝቦ ልዩነቶችን በማጥበብ እና አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር ከጅምሩ የተጠየቁ ሶስቱን መሰረታዊ የእምነት እና የመብት ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ በህዝባችን ላይ የተጋረጠዉን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ብሎም በእስር የሚማቅቁ ወንድሞቻችንን ለማስፈታት ጥረታችንን  መቀጠልና  በአዲስ መልክ በጋራ ርብርቦሽ በማድረግ የአቋም ጽናታችንን ዳግም መገንባት እንደሚጠበቅብን እናምናለን።

                                          የበድር ዳይሬክተሮች ቦርድ                                                                                                           ሰሜን አሜሪካ                                                                                                                       ኦገስት 16, 2017                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                           

     

 

 

                                                

Ustaz Abubeker Ahmed/ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ.

 

አቋምን በግልጽ ስለማሳወቅ

 

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ፣ በጣም አዛኝ በሆነው!

 

ከአምስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያዊው ህዝበ ሙስሊም 3 መሰረታዊ ጥያቄዎችን ማንሳቱ ይታወሳል፡፡ እነዚህ 3 መሰረታዊ ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች ብቻ መሆናቸው ከጅምሩ አንስቶ እስከአሁንም ድረስ በግልጽ የሚታወቅ ሲሆን ጥያቄዎቹም የሚከተሉት ናቸው፡-

 

1/ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን (መጅሊስን) የሚያስተዳድሩ ወኪሎችን በነጻነት ያለምንም ጣልቃ ገብነት እኛው የእምነቱ ተከታዮች እንምረጥ፤

 

2/ ብቸኛው ተቋማችን አወሊያ ከህዝበ ሙስሊሙ በሚመረጡ ምሁራን በቦርድ ይተዳደር፤

 

3/ የአህባሽ አስተሳሰብ በግድ አይጫንብን፤

 

ምንም እንኳን ህዝበ ሙስሊሙ ‹‹መፍትሄ ያፈላልጉልኛል›› በሚል ዓላማ ከአገር ቤትም ከውጭም በፊርማው በወከላቸው ኮሚቴዎች አማካኝነት እነዚህን ጥያቄዎች ወደመንግስት ቢያቀርብም በመርህ ደረጃ የተሰጠው መልስ ግን አፈጻጸሙን በሚመለከት ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ ሂደቱ ሊራዘም ችሏል፡፡ እኛ የህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎችም ህዝባችን እንድናደርስለት የወከለንን ጥያቄ በተገቢው መልኩ ለሚመለከተው አካል ለማድረስ በተለያዩ እርከኖች ከሚገኙ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በተደጋጋሚ ውይይት ያደረግን ሲሆን የጥያቄዎቹን ተገቢነት እና ግዝፈትም በሚገባ አስረድተናል፡፡ ከመንግስት የተሰጠንን ምላሽ ግልጽ በሆነ መልኩ ለህዝቡ ይፋ በማድረግ ህዝባችን የጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት ሞክረናል፡፡ በመርህ ደረጃ የተሰጠውን ምላሽ ተግባራዊ አፈጻጸም አስመልክቶ ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸው ስጋቶች አግባብ በመሆናቸውም ግልጽና ተገቢ በሆነ መልኩ ይፈጸም ዘንድ የበኩላችንን ጥረት ስናደርግም ቆይተናል፡፡ 

 

ይህንኑ ጥረታችንን ተከትሎ ባለፉት ዓመታት በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአንድነት የአፈጻጸም ችግሩን በመቃወም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃውሟችንን ስናሰማ የቆየን ሲሆን በሂደቱም ከፊል የኮሚቴ አባላቱን ጨምሮ በርካታ ምሁራን፣ ዑለሞችና ወጣቶች ለስደትና ለእስር ተዳርገዋል፡፡ አሁንም በስደት እና በእስር የሚገኙ በርካቶች ናቸው፡፡ 

 

ይህንን ሰላማዊ የመብት ጥያቄ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዓላማውን ተቀብለው ሲደግፉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ይህን መሰል ግዙፍ ህዝባዊ እንቅስቃሴ የተራዘመ ሂደት ውስጥ ሲያልፍ ለተለያዩ አተረጓጎሞች መጋለጡ የማይቀር ነበርና የሙስሊሙ የመብት ጥያቄም ለአተረጓጎም ልዩነቶች የተጋለጠበት አንዳንድ ሂደት መፈጠሩ አልቀረም፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ መንገዶች ጥያቄዎችን ማቅረባቸው የማይቀር እንደመሆኑ መጠን በተራዘሙ ሂደቶች ሰበብነት የራሳቸውን ልዩ ባህርያትና አካሄድ የሚያዳብሩበት ሁኔታ መፈጠሩ የሚጠበቅ እና ያለ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳው የመብት ጥያቄ ሃይማኖታዊ ህገመንግስታዊ መብቶችን የመጠየቅ ፍጹም ሰላማዊ አካሄድ ሲሆን ይህ ባህሪውም ዛሬም ድረስ እንደተጠበቀ ይገኛል፡፡

 

የህዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄ የራሱ የሆኑ ልዩ ባህርያት ያሉት፣ ሂደቱም በራሱ በእንቅስቃሴው መርህ የሚቃኝ እንጂ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በሚሰጠው ስያሜ የሚገለጽ አይደለም፡፡ በመሆኑም እስካሁን ድረስ የቀጠለውን ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ከፖለቲካ ጋር በማዛመድ ሌላ መልክ ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶች እንቅስቃሴውን የማይወክሉ እና ከእንቅስቃሴው መርህም ውጭ የሆኑ አካሄዶች መሆናቸውን አበክረን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ በተለይም አሁን ላይ ትግሉን የተለያዩ ቡድኖች ለራሳቸው እምነት፣ አስተሳሰብም ሆነ የፖለቲካ ፍልስፍና የተመቸ እንዲሆን በማድረግ ለዓላማቸው ለመጠቀም እና ከተነሳበት መሰረት ውጭ ለማስኬድ የሚያደርጉት ጥረት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፡፡

 

የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች ከጅምራቸው አንስቶም በህግ አግባብ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ወደሚመለከተው አካል የቀረቡ ህገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄዎች ሲሆኑ ቅኝታቸውም በአገራዊነት እና ሰላማዊነት መንፈስ የታጀበ ከመሆን የራቀበት አንዳችም ወቅት አልነበረም፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄውን በይፋ ማቅረብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እርስ በእርስ ይግባባበት የነበረው ብቸኛ ቋንቋም ሰላማዊነት፣ ህጋዊነት እና አገራዊነት ነበር፡፡ ይህ የትግሉ ባህሪ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን በመርህም በተግባርም ተፈትኖ መልኩን ያልቀየረ፣ ከሰላማዊነትም በጭራሽ ያላፈነገጠ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ለዚህ መርህ አክባሪነት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ እንቅስቃሴው ሃይማኖታዊ መብትን ለማስከበር ያለመ ሰላማዊና ህጋዊ እንቅስቃሴ ብቻ እና ብቻ በመሆኑ ነው፡፡

 

ይህንን እውነታ ዳግም ለማስታወስ የፈለግነው ሰላማዊው የመብት እንቅስቃሴ ዛሬ ላይ በተለያዩ አካላት፣ ለተለያዩ የፖለቲካ ዓላማዎች በተለያየ ስያሜ ሲቀርብ በማየታችን ሲሆን ይህን መሰሉ አካሄድም የተነሳንበትን ዓላማ የሚቃረን በመሆኑ በዝምታ ለመመልከት አልፈቀድንም፡፡ ካሁን ቀደም በተለያዩ ጊዜያት አስፈላጊ መርሆችን በተለያዩ አማራጮች ለህዝብ እንዲደርሱ እናደርግ ነበር፡፡ ይህ አካሄድ ግን እስር ቤት የመግባቱ ነገር ሲፈጠር የግንዛቤ ማስተካከያዎችን እንደልብ ለማሰራጨት እድሉ ባለመገኘቱ በተወሰነ ሁኔታ የተስተጓጎለበት ሂደት መፈጠሩ አልቀረም፡፡ በዚህ ክፍተት ስለ ህዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄ ሊፈጠር የሚችለውን የአመለካከት ክፍተት ለማጥበብ ግን ዛሬም ላይ መርሁን የማሳወቅ ግዴታ ስላለብን ይህንን ማስታወሻ መስጠት ለጊዜው አስፈላጊ ሆኗል፡፡ 

 

ዛሬም ቢሆን ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸው ተቋማችንን መጅሊስን እና ሌሎችም ተቋሞቻችንን የሚመለከቱ የመብት ጥያቄዎች ፍጹም ተገቢ መሆናቸውን እና ተቋማቱም መሰረታዊ ለውጥ የሚሹ መሆናቸውን በጽኑ እናምናለን፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ሁሉም በእኩል የሚስተናገድባቸው፣ ከሙስናና ከብልሹ አሰራር የጸዱ፣ በሚያምናቸውና በመረጣቸው መሪዎች የሚተዳደሩ ተቋማት ባለቤት ለመሆን አሁንም ድረስ ህዝባችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ይጠይቃል፡፡ በመብት ጥያቄው የተነሳ በርካቶች ለእስር እና ለስደት ቢዳረጉም የእንቅስቃሴው መርህ ግን ዛሬም እንደተጠበቀ የሚጸና ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የእንቅስቃሴው መርህ ከህዝባችን ሰላማዊነት፣ አገራዊነት እና ህግ አክባሪነት ባህሪ የተቀዳ በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ለመርሁ ተገዥ የሆነ የመብት እንቅስቃሴ በየጊዜው በሚፈጠሩ ችግሮች እና ፍላጎቶች የማይለወጥ መሆኑን ከእስር የተፈታን የኮሚቴ አባላትም ሆነ በእስር ያሉትም ጭምር በጋራ ለማስረገጥ እንወዳለን፡፡ 

 

በዚህ አጋጣሚ እንደአንድ የእምነቱ እና የአገሩ ጉዳይ አጥብቆ እንደሚያሳስበው አካል ተቋማችን መጅሊስ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የትግልና የመስዋእትነት ታሪክ የሚመጥን ክብር እና ሞገስ የተላበሰ ተቋም እንዲሆን ጥረት ታደርጉ ዘንድ ለዑለማዎቻችን፣ ለአገር ሽማግሌዎች እና ለምሁራኖቻችን አጥብቀን አደራ የምንል ሲሆን እኛም በበኩላችን የሚጠበቅብን ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡      

 

አላሁ አክበር!

 

 

ነሐሴ 7/2009