በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ

     ሙ ባ ረ ክ

     በሰሜን አሜሪካ እና  በመላዉ ዓለም ለምትገኙ ሙስሊሞች እንኳን ለ 1439 ኛዉ ለተከበረዉ የኢድ አልፊጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያልን የዘንድሮዉ ኢድ ለየት የሚያደርገዉ ያለ በቂ ምክንያት በፖለቲካ ሽፋን ለእስር ተዳርገዉ የነበሩ ብርቅዬ ዉድ ኮሚቴዎቻችን እና ከሰላማዊ እንቅስቃሴዉ ጋር በተያያዥነት ታስረዉ የነበሩ ከእስር ተፈተዉ ከሚወዳቸዉ ማህበረሰብ እና ከናፈቋቸዉ ቤተሰቦቻቸዉ ጋር መቀላቀላቸዉ ነዉ። በድጋሚ አልኸምዱሊላሂ እንላለን ።

      ከሰላማዊ የእምነት ነጻነት እና የመብት ጥያቄዉ ጋር በተያያዘ አሁንም በየ እስር ቤቱ እየማቀቁ ያሉ ወገኖቻችን ሁሉ እንዲፈቱ በዱዐ እንድናስታዉሳቸዉ ሆኖ በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆንልን በመመኘት የተራበና የታረዘን እያስታወስን በሀገራችንም ዘላቂነት ባለዉ መልኩ የተረጋጋ ሰላም እንዲመጣ በመመኘት እንዲሁም በሮመዳን ስንተገብራቸዉ የነበሩ መልካም ኢባዳዎች እና የይቅርታና የወንድማማችነት ጅማሮዎች ሂደታቸዉ ቀጣይነት እንዲኖራቸዉ በጽኑ እንሻለን።

   የአክሱም ሙስሊም ህብረተሰብ ለረጅም ዓመታት የመብት ጥያቄ ቢያቀርቡም ምንም ምላሽ ሳያገኙ በመመላለስ ብቻ እስከ ዛሬ የመስጂድም ሆነ የቀብር ቦታ አለመፈቀዱ በሀገሪቱ ታሪክ በጣም አሳዛኝ የሆነ ተጽእኖ ተፈጽሞባቸዋል። ይህንን ጉዳይ የፌዴራል መንግስትም ሆነ የክልል አስፈጻሚ አካላት በተቀናጀ መልኩ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸዉ እያሳሰብን በዉጭ የምንገኝ ሙስሊም ማህበረሰብም የማስፈጸም ግዴታ እንዳለብን አዉቀን የሚፈለግብን ሁሉ ለማድረግ ብሎም የድርሻችንን ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለብን ለማሳሰብ እንወዳለን። 

    በኢትዮጵያ ብሎም በመላዉ ዓለም ለሚገኙና ሰላም ፤ ፍትህ ፤ ደህንነት እና ነጻነትን ለተነፈጉ ሙስሊሞችና ሙስሊም ላልሆኑ ወገኖቻችን በሚያደርጉት የሰላማዊ ትግል ጉዞ ላይ እንደ ሁልጊዜዉም ከጎናቸዉ የምንቆም መሆናችንን እያበሰርን የዘንድሮ  ‘’ ኑ በአላህ መንገድ ላይ እንተጋገዝ ‘’  በሚለዉ መርህ በሰላም ፋዉንዴሽን አዘጋጅነት ከጁላይ 26 እስከ 29 በሚካሄደዉ በአይነቱ እጅግ ልዩና ታሪካዊ በሆነዉ 18 ኛዉ ዓመታዊ የበድር ኮንቬንሽን ከተጋባዥ እንግዶቻችን ዉድ የኮሚቴዉ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ፤ ታላቁ አሊማችን ሼህ ሙሀመድ ሀሚድን እና  ሌሎች ስመጥርና በዳዕዋቸዉ የብዙሀኑን ቀልብ የሳቡ ዳኢዎቻችን ጋር ለመታደም እንደምትገኙ ተስፋ በማድረግ በዓሉን በደስታ የምናሳልፈዉ እንዲሆንልን መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን።

    ተቀበለሏሁ ሚና ወሚንኩም ሷሊኸል አዕማል 

በድር ኢትዮጵያ                                                                                                                                        

ሰሜን አሜሪካ                                                                                                                                         

ጁን 14 2018   

                               

     በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ

የሰላም ጥሪ

   ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዲያስፖራ በምንገኝ ሙስሊም ማህበረሰብ መካከል ተከስተዉ የነበሩ ዉዥንብሮች የመጥራት ባህሪ ማሳየታቸዉና ይሰነዘሩ በነበሩ አሉባልታዎችና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ምትክም እርቅና አብሮ መስራት በሚሉ መልካም ቃላቶች ተቀይረዉ መገኘታቸዉና በሶሻል ሚዲያ ሲነገሩ መስማታችን ጅማሮዉን ከማድነቅ እና አልኸምዱሊላሂ ከማለት በስተቀር ሌላ ምላሽ ከቶ ሊኖረን አይችልም።

    በድር ኢትዮጵያ እንደ የእምነት ድርጅትነቱ ሰላምን መርህ አድርጎ ለኡማዉ ጠቀሜታ አብሮ ለመስራት የተቻለዉን ሁሉ ሲያደርግ እንደነበር እንረዳለን፤ በድርጅቶች መካከል ተፈጥረዉ የነበሩ አላስፈላጊ አካሄዶችን ግምት ዉስጥ በማስገባት እና በኡማዉ ላይ ሊደርሱ የሚችሉትን ፊትና ለማስቀረት በተለያዩ  አካላት በተዘጋጁ የተለያዩ ስብሰባዎች ላይ በድር ችግሮች እንዲፈቱ ካለዉ ጽኑ ፍላገት በመነጨ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቷል፤ ምንም እንኳን ሌሎች አካላት ባይገኙም።

     የበድር ድርጅት እና አመራሩ ኢስላማዊ አደብ በሌለዉ መንገድ በከንቱ ሲወነጀሉ ሌሎች በተለይ ጉዳዩን በአግባቡ የሚያዉቁ አካላት ምንም አለማለታቸዉ ቢያሳዝነንም የስም ማጥፋት ዘመቻን ጊዜ ይፍታዉ ከማለት በስተቀር የግለሰብም ሆነ የድርጅት ስም አንስቶ የተቸንበት ጊዜ አለመኖሩ ወንድማማችነትን እና ኡማዉን አንድ ለማድረግ የዓላማዉ ጉልህ ማስረጃ ነዉ ብለንም እናምናለን ።

    በሀገር ቤት የሙስሊሙ ህብረተሰብ ባደረገዉ ሰላማዊ የመብትና የእምነት ነጻነት ጥያቄ ለዉጤት ለማብቃትም ድርጅቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ በመንቀሳቀስ ጥረት አድርጓል። ከሰሞኑ ከበድር ኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመስራት የሰላም ጥሪ እንደቀረበ በሶሻል ሚዲያ እየተነገረ ነዉ። ሀሳቡ ምንጊዜም ስንመኘዉና ስንናፍቀዉ የነበረ ቢሆንም ከአንዳንድ ኸይር ፈላጊ ወንድሞች ይህን በተመለከተ ለማሸማገል ሀሳብ ከመኖሩ ዉጪ እንደ ድርጅት ለድርጅታችን የሰላም ጥሪን የሚመለከት በደብዳቤም ሆነ በኢሜይል የደረሰን ምንም ዓይነት ጥሪ አለመኖሩን ለአባላቶቻችንና ለሰላም ወዳድ ወገኖቻችን ግልጽ ለማድረግ እንወዳለን። ለእርቅና አብሮ ለመስራት በራችን እንደ ትናንቱ ዛሬም ክፍት መሆኑን ዳግም እየገለጽን በነበሩ ክፍተቶች ላይ ገለልተኛ በሆነ አካል አማካይነት ዉይይት ተደርጎ ለተፈጸሙ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች የማጥራት ሂደት ተከናዉኖ ዘላቂ መፍትሄ በመሻት ሁሉም የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ብሎም አብሮ ለመስራት እና ይቅር ለመባባል አላህ (.) በሚወደዉ መንገድ ተፈጻሚ እንዲሆን የበኩላችንን ለማለት እየወደድን የነበሩ ልዩነቶችን አስወግደን በጋራ ወደፊት ለሚጠበቅብን ሰፊ ተግባር እንድንዘጋጅ ጥሪያችንን እናቀርባለን። 

አላህ (.) ቀጥተኛዉን መንገድ ይምራን

                                              በድር ኢትዮጵያ                                                                                                                           ሰሜንአሜሪካ                                                                                                                                 ሰኔ 7 2018