ቤተ አምልኮዎችን መጠበቅ የእውነተኛ መቻቻል ማሳያ ነው

ከኡስታዝ አቡበከር አህመድ የተላለፈ መልዕክት

ቤተ አምልኮዎችን መጠበቅ የእውነተኛ መቻቻል ማሳያ ነው

በደቡብ ጎንደር እስቴ በመስጂዶች ላይ የተወሰደውን የማቃጠል እርምጃ ሁሉም በጋራ ሊያወግዘውና ሊያስቆመው የሚገባ ህገወጥና ኢ-ሞራላዊ ተግባር ነው፡፡ ቤተ እምነቶች የታፈሩ እና የተከበሩ የፈሪሃ አምላክ ምእመናን ማዘውተሪያ እንደመሆናቸው ለቤተ አምልኮዎች የምናሳየው ክብር ለአምላክ፣ ለምዕመኑ እና ለሰው ልጆች የምናሳየው ክብር ማሳያ ነው፡፡ በተቃራኒው ቤተ አምልኮዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች በቤቱ ላይ የሚሰነዘሩ ሳይሆኑ በምእመኑ እና በማምለክ ነፃነት በሚያምኑ የሰው ልጀች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ነው፡፡ ይህን ጥቃት ለማውገዝ የማምለክ ነፃነትን ከሚያምን ማንኛውም አካል የሚጠበቅ የመጀመሪያ ተግባር ነው፡፡

እንደሚታወሰው ከዚህ ቀደም በጅግጅጋ በቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰው ጥቃት የሁላችንም ትኩረት ስቦ ችግሩንም ለመፍታት ግንባር ቀደም ሚናውን የተጫወቱት በዚያው አካባቢ የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ አሁንም በደቡብ ጎንደር በደረሰው ጥቃት ተመሳሳዩ ሞራላዊ እና ኢትዮጵያዊ ምግባር የሚጠበቅ ቢሆንም የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች የተወሰነ ሙከራ በስተቀር ከህግ አስከባሪውም ሆነ ጉዳዩ ሊያሳስባቸው ከሚገባ ተቋማት የተሰጠው ትኩረት በሀገራችን እንዲመጣ ከሚፈለገው የአምልኮ ነፃነትና የመቻቻል መስተጋብር በተቃራኒው የሚሄድ ነገር እንዳይኖር ስጋት ውስጥ የሚከት ሆኖ የሚታየው፡፡ በመሆኑም የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆቹን መክሮና ገስፆ መስጂዶችን የመጠበቅና መልሶ የማቋቋም ስራውን በባለቤትነት እንዲይዝ እየጠየቅን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት መሰል ድርጊቶች ዳግም እንዳይፈፀሙ በድርጊቱ ፈፃሚዎችና አስተባባሪዎች ላይ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ ወስደው ስለተወሰደው ህጋዊ እርምጃም ለህዝብ እንዲያሳውቁ እንጠይቃለን፡፡

Leave a comment

All comments are moderated before being published