ክብርና ምስጋና ለጀግናዉ ሰራዊታችን ይሁን

Posted by Badr Ethiopia on

  ክብርና ምስጋና ለጀግናዉ ሰራዊታችን ይሁን   

    ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ጦርነቶችን አድርጋለች ። በሁሉም ጦርነቶችም በፈጣሪ ሀይል ለዉጤት መብቃትዋና ዓለምን ባስደመመ መልኩ የታሪክ ባለቤትም አድርጓታል። ባለፉት ሶስት ሳምንታት ዉስጥ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሀት መካከል በተካሄደዉ የሀገር ዉስጥ ጦርነት ጅማሮዉን ያደረገዉ ጥቃቱ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያነጣጠረ ስለነበር ከሁሉም ልዩ የሚያደርገዉ የጦርነት ባህሪ ያለዉ ቢሆንም የሀገራችን ጀግናዉ መከላከያ ሰራዊት ጥቃቱን በመቋቋም በድል ብስራት ቀይረዉታል። በጦርነቱ ለተጎዱና ህይወታቸዉ መስዋዕት ለሆኑ ጀግኖች ሁሉ ክብር ይገባቸዋል እያልን ለቤተሰቦቻቸዉም መጽናናትን እንመኛለን።      

   የጦርነቱን መጀመር ተከትሎ በድር ኢትዮጵያ በሚፈለገዉ ደረጃ የተጣሩ መረጃዎችን ከሁሉም አቅጣጫዎች ባለማግኘቱ የተነሳ ጠቅለል ባለ መልኩ የጦርነት አስከፊነትና የሰላማዊ ንጹሀን ዜጎች ሁኔታን እንደሚያሳስበዉ በመግለጽ በወቅቱ መግለጫ ማዉጣቱ ይታወቃል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ባለዉ የተጣራ መረጃ መሰረት የጦርነቱ አጀማመር እና መንግስት ህግን የማስከበር ዘመቻ በሚል ባካሄደዉ ጦርነት በተለይ ንጹሀን ዜጎችን ለመታደግ የተወሰደዉን ርምጃ ግምት ዉስጥ በማስገባት ብሎም ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ዉስጥ በመጠናቀቁ በድር ኢትዮጵያ የተሰማዉን ታላቅ ደስታ ለመግለጽ እንወዳለን።

   በሀገራችን ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅ በነጻነት ለመንቀሳቀስ እና ሰብአዊ መብታቸዉን ለመተግበር የሚያስችላቸዉ ስርዐት ተነፍገዉ ሀገ መንግስቱን በሚጻረር መልኩ ሰዎች በተለያዩ መልኮች ስቃዮችን ሲያስተናግዱ ፤ ሲፈናቀሉ፤ ሲሰደዱ፤ ጭካኔያዊ ግድያ ሲፈጸምባቸዉ ከማስተናገድ የበለጠ የከፋ ነገር የለም። ለረጅም ጊዜ ከተፈራረቁብን የአጼዎቹ መንግስታት ሁሉ ባልተናነሰ መልኩ ባለፉት 27 ዓመታት ዉስጥ የሙስሊሙ ማህበረሰብ  መጠነ ሰፊ ችግሮችን ያስተናገደ መሆኑ የትላንት ታሪካችን በመሆኑ መዘርዘሩ አስፈላጊ አይሆንም ። በቅርቡ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበዉን ሪፖርት ግምት ዉስጥ በማስገባት በማይካድራ እና መሰል አካባቢዎች በንጹሀን ዜጎች ላይ የተፈጸመዉ አሰቃቂ ግድያም እጅጉን ያሳዘነንና በጽኑም የምናወግዘዉ እኩይ ተግባር ነዉ ።      

   ዉድ የሀገራችን ህዝቦች ሆይ ሰብዐዊነት ለአንድ አካል ብቻ የሚቸር ሆኖ ለሌላዉ የሚነፈግ አይደልምና እስከዛሬ ያስተናገድናቸዉን የመከራ ጊዜያትን ተሻግረን አሁን በምንገኝበት ሰዐት ያለፉትን ቁርሾ በመርሳት በቀጣይ የህይወት ዘመናችን ሀገራዊ እና ቤተሰብአዊ ትስስራችንን አጠናክረን ከችግር፤ ከረሀብ  እና ከመሰረታዊ ተቋማት ችግሮች የምንላቀቅበትን በጋራ በማለም ጠንክረን ለመስራት እንድንዘጋጅ በማለት አደራ እያልን በንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃትን የፈጸሙ አካላት መንግስት ተከታትሎ ወንጀለኞችን በህግ አግባብነት ባለዉ መልኩ ለፍርድ ሊያቀርባቸዉ እንደሚገባ ለመጠቆም እየወደድን በተለይ በጦርነቱ ለተጎዱም ሆነ ለተሰደዱ ዜጎች መንግስት በፍጥነት የማቋቋም ሂደቱን እንደሚያፋጥን በመተማመን ጭምር ነዉ።    

  በኮቬድ 19 ወቅት ያደረግነዉ ድጋፍ በቀጥታ ለህብረተሰቡ ለማድረስ እንደተቻለዉ ሁሉ አሁንም ያንን ፈልግ ተከትለን ለተጎዱ የሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ቤተሰቦች ፤ በአማራ እና በትግራይ ክልል በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖቻችን በቀጥታ ተደራሽነት ባለዉ መልኩ እርዳታ በማድረግ የበኩላችንን የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት እንድንችል በየኮምዩኒቲዎቻችን እንደሌላዉ ጊዜ ሁሉ የተለመደዉን ትብብራችሁን በአፋጣኝ ታደርጉ ዘንድ በማክበር እናሳዉቃለን ።

አላህ (ሱብሁዋነሁ ወተአላ ) ሀገራችንና ህዝባችንን ይጠብቅልን አሜን !

በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ    ዴሰምበር 1  2020                                              


← Older Post Newer Post →