በአማራ ክልል ዳግም ሙስሊም ተኮር የሽብር ጥቃት ተፈጸመ

Posted by Badr Ethiopia on

በአማራ ክልል ዳግም ሙስሊም ተኮር የሽብር ጥቃት

     በአማራ ክልል ከዚህ ቀደም በሙስሊሙ ማህበረሰብ እና በንብረቱ ላይ የተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችን አስመልክቶ በፌድራሉም ሆነ በክልሉ መንግስት ትኩረት ሳይሰጠዉ በመቅረቱ የተነሳ ተመሳሳይ የሆነ የሽብር ጥቃት ዳግም በክልሉ በደቡብ ጎንደር እስቴ ጃራ ገዱ ከተማ አሳዛኝ ጥቃት ሊፈጸም በቅቷል።  

     ሙስሊሙን ማህበረሰብ ተኮር ያደረገዉ ይኸው የሽብርን ጥቃት የአካባቢው የመንግስት አካላት ለመከላከልም ሆነ  ለመቆጣጠር  ያደርጉት ጥረት አናሳ ከመሆኑ አንጻር የጸጥታ ሀይላትም መልዕክቱ እንዲደርሳቸዉ ቢደረግም በወቅቱ አለመድረሳቸዉና በቦታዉ ዘግይተዉ ቢገኙም የዜጎችን ሰብአዊ መብት ለመታደግም ሆነ ለማስከበር የተደረገዉ እንቅስቃሴ ዘገምተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩንም ዉስብስብ አድርጎታል።

    በሀገራችን በንጹሀን ዜጎች ላይ ባህሪዉን በመቀያየር እየተፈጸመ ያለዉን በደል ከመላመዳችን የተነሳ በሚመስል መልኩ የሚሰጠዉ ትኩረትም ሆነ በጥቃት አድራሾች ላይ የሚወሰደዉ ርምጃ መላላት እንዳንዴም መፍትሄን በመንፈግ በቸልተኝነት ማለፉ የሚያስከፍለዉን ዋጋ መገመት የሚያስቸግር ሊሆን እንደሚችል ማሰብን ይጠይቃል።

    በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ በሚፈጸሙ ያላቋረጡ በደሎች ሳቢያ ሙስሊሙን ማህበረሰብ በብሶት ለማነሳሳት ብሎም እንደምክንያት በመጠቀም በሀገሪቱ ላይ ዉጥረት በመፍጠር ሰላሟን ለመፈታተን የሚደረገዉ ድብቅ አጀንዳም እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን በሌላ መልኩም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ተደራጅቶ ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር በነጻነት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ እንቅፋት ለመሆን የሚደረግ ጥረትም ጭምር ነዉ።  

   በሀገራችን በተለያዩ ክልሎች ተመሳሳይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ድርጊቱን የሚዘግቡት የመንግስት የመገናኛ ሚዲያዎችም ሆነ የመንግስት አካላት የደረሰዉን ጥቃት በመዘገብና ጥቃቱን ቢያወግዙም ነገር ግን በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች ትኩረት አለመስጠታቸዉ እጅጉን አነጋጋሪ ሲሆን በተለይ በሌሎች ክልሎች ለሚደርሱ መሰል ጥቃቶችን በቁጭት የሚያወግዘዉ የአማራ ክልል መስተዳደርም በክልሉ ጥቃት በሚፈጸምባቸዉ የሙስሊሙ ማህበረሰብም ሆነ የሚወድሙ ንብረቶችን አስመልክቶ አለማዉገዙና ጥፋተኞችን ለህግ አለማቅረቡ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች በክልሉ የተለያዩ መስፈርቶች ያለዉ አስመስሎታል። 

   የፌድራል መንግስትም ሆነ የክልል አመራር አካላት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረዉን የሽብር ጥቃቶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የማስቆም ግዴታ ያለባቸዉ መሆኑን እየገለጽን ዜጎች በሀገሪቷ ያለምንም አድልኦ ህገመንግስታዊ መብታቸዉ በእኩል የማስከበር ሀላፊነት አለበት።

   በአማራ ክልል ተመሳሳይ ሙስሊም ተኮር ጥቃቶች መፈጸማቸዉን እያወገዝን በየደረጃዉ ያሉ የመንግስት አካላት ይህን መሰል የሽብር ጥቃት ህግን ከማስከበር ተለይቶ የማይታይ ጥቃት በመሆኑ አስቀድመዉ ሊከላከሉ እንደሚገባ እያሳሰብን ከዚህ ቀደም በግዴለሽነት እንደታለፈዉ ሁሉ ዳግም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሊታገስ የሚችልበት ደረጃ ላይ ባለመሆኑ  የሽብር ጥቃቱን የፈጸሙ አካላት ተጣርቶ በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርቡና ለማህበረሰቡም እንዲገለጽ አበክረን እንጠይቃለን። 

አላህ (ሱብሁዋነሁ ወተአላ) ሀገራችንን በሰላም ይጠብቅልን !!!

በድር ኢትዮጵያ    ሰሜን አሜሪካ     ጃንዋሪ 26 2021                      


← Older Post Newer Post →