Deprecated: Non-static method JSite::getMenu() should not be called statically, assuming $this from incompatible context in /home/badrtube/public_html/badrethiopia.org/oldsite/templates/yoo_revista/warp/systems/joomla/layouts/com_content/article/default.php on line 13

Deprecated: Non-static method JApplication::getMenu() should not be called statically, assuming $this from incompatible context in /home/badrtube/public_html/badrethiopia.org/oldsite/includes/application.php on line 536

… እኔ መጅሊስ አልፈልግም!

Posted in Amharic Articles

Nov 3, 2012 | ነስሩዲን ዑስማን

… በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የተረጋጋ ህይወት እያወከ የሚገኘው የ‹‹አህባሽ አጀንዳ›› ከውጭ ኃይሎች፣ በዋነኝነትም ከጽዮናዊት እስራኤል የረዥም ጊዜ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅም የመነጨና በጂኦ-ፖለቲካዊ ካርታው ላይ ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አኳያ ለመንግሥታችን የቀረበ መርኃ-ግብር እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ለዚህ ዋናው ማሳያ፣ ይህ ባይሆን ኖሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ከጠቅላላው የአገሪቱ ህዝብ ከፊል ከሆነው ህዝበ-ሙስሊም ጋር የሚያላትም ፕሮጀክት ከመሬት ተነስቶ ሊፈጥር፣ በትጋት እና በፅናት ለመተግበር ሊሯሯጥ አይደክምም ነበር የሚል ነው፡፡ ይህ ፀሐፊ ይህንን አስተሳሰብ በፅኑ ይጋራል፡፡

… ‹‹የአህባሽ አጀንዳ›› ወይም መርኃ-ግብር ‹‹ሃይማኖታዊ›› ገፅታ ስላለው የኢትዮጵያ መንግሥት መርኃ-ግብሩን ለብቻው ሊፈፅመው አይችልም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ሕገ-መንግሥቱ በሃይማኖት ጣልቃ መግባት ስለማይፈቅድለት፡፡›› … ስለዚህም መንግሥት ‹‹የአህባሽን አጀንዳ›› ተፈፃሚ ለማድረግ የግድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባዔ (መጅሊስ) ያስፈልገዋል፡፡ መጅሊስ የሚባል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተጠሪ ተብዬ ተቋም ከነአካቴው ባይኖር ኖሮ፣ መንግሥት ‹‹የአህባሽ አጀንዳ››ን በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ ለመጫን የሚችልበት ተቋማዊ መዋቅር አይኖረውም ነበር፡፡ … እዚህ ላይ መንግሥት አህባሽን በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ መጫን የፈለገው ለአህባሽ የተለየ ፍቅር ስላለው፣ ወይም በአጠቃላይ ከሃይማኖታዊ ሰበብ አለመሆኑ በደማቁ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ መንግሥት የአህባሽ ተከታይ አይደለም፡፡ ከአህባሽ ጋር የተለየ ፍቅር ያለው ካለ በቅድሚያ የምትጠራው ጽዮናዊት እስራኤል ነች፡፡ እርሷስ ለምን አህባሽን ወደደች የሚለው ጥያቄ ርዕዮተ-ዓለማዊ እና ውስብስብ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚመዝ ስለሆነ ይህ ጽሑፍ እዚያ ውስጥ አይገባም፡፡…

… የመጅሊስ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከጥር ወር 2004 አንስቶ እያካሄዱ ባሉት መብትን የማስከበር እንቅስቃሴ ካነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥ ዋነኛው ነው፡፡ ከሦስቱ የህዝበ-ሙስሊሙ ጥያቄዎች የመጀመርያው፣ ‹‹ህዝበ-ሙስሊሙ በንቃት የሚሳተፍበት ነፃና ዴሞክራሲያዊ የመጅሊስ አመራሮች ምርጫ ይካሄድ!›› የሚል መሆኑ ይታወቃል፡፡ … ይህ ጥያቄ የመነጨው መንግሥት እና መጅሊስ በጋራ ሁነው የአህባሽን አስተምህሮ በህዝበ-ሙስሊሙ ላይ ለመጫን የጀመሩትን እንቅሰቃሴ ‹‹በቀላሉ ለማስቆም ያስችላል›› ተብሎ ስለታመነበት ይመስለኛል፡፡ … ይህ እምነት ‹‹ህዝበ-ሙስሊሙ ያለማንም ጣልቃ-ገብነት ነጻና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የመጅሊስ አመራሮችን ቢመርጥ አህባሾች በመጅሊሱ ውስጥ ቦታ አይኖራቸውም፤ አህባሻዊ ያልሆነ መጅሊስ ደግሞ አህባሽን በህዝበ-ሙስሊሙ ላይ ለመጫን ከመንግሥት ጎን አይሰለፍም›› በሚል እሳቤ ላይ የተመሠረተ ይመስላል፡፡

…መንግሥት ከውጭ ኃይሎች ጋር፣ ምናልባትም በሰጥቶ (ሰውቶ?) መቀበል መርኅ ላይ ተመሥርቶ ተፈፃሚ ሊያደርግ የጀመረውን መርኃ-ግብር በዚህ መልኩ ለማጨናገፍ መታሰቡ መንግሥትን ስጋት ውስጥ ሳይከተው የቀረ አይመስለኝም፡፡ ከዚህም በመነሳት ምናልባት መጅሊሱ ከቁጥጥሩ ውጪ ቢሆን ሌላ ተጠባባቂ አስፈፃሚ አካል እንዲያዘጋጅ ያነቃው ይመስለኛል፡፡ በመንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ በሚያስገርም ፍጥነት አምና የተቋቋመው ‹‹አህለልሱንና ወልጀመዓ ወሱፊ›› የተሰኘ ማኅበር የዚህ ተጠባባቂ፣ ኢስላማዊ መልክ ያለው አጋር ተቋም የመሻት ውጤት ይመስለኛል፡፡ …

… እዚህ ላይ ግን አንድ ቁልፍ ጥያቄ እናንሳ፡፡ ነገሩ ሁሉ ህዝበ-ሙስሊሙ በፈለገው መልኩ ሄዶ ፍፁም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተመረጡ የመጅሊስ አመራሮች የመንግሥትን መርኃ-ግብር (“የአህባሽ አጀንዳ”ን ወይም ‹‹የፀረ-ሰለፊ ዘመቻ››) ለማስፈፀም አሻፈረኝ ቢሉ፣ እነዚህ አመራሮች የተመረጡለት መጅሊስ ዕጣ ምንድን ነው የሚሆነው? እውን ይህ መጅሊስ በሁለት እግሩ መቆምም ሆነ ለህዝበ-ሙስሊሙ ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት ይችላልን? …በእኔ እምነት አይችልም፡፡

…በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ እንደሚሰማው የመንግሥት አጀንዳ ‹‹አክራሪነትን›› መዋጋት ቢሆን ኖሮ፣ በተባለው መንገድ የሚመረጡ የመጅሊስ አመራሮች የፀረ-አክራሪነቱን ትግል ከመንግሥት ጋር እጅና ጓንት ሆነው እንደሚያካሂዱት ብቻ ሳይሆን ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚችሉ በግሌ ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለኝም፡፡ ነገር ግን ‹‹አክራሪነት›› እና ‹‹ጽንፈኝነት›› የመርኃ-ግብሩ ‹‹የአህባሽ አጀንዳ›› የማስፈፀሚያ ቅመሞች (በኢህአዴግኛ “አቅጣጫዎች”) እንጂ ዋናው አጀንዳ አይደሉም፡፡ ዋናው አጀንዳ ሰፋ ያለ ርዕዮተ-ዓለማዊና ጂኦ-ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ‹የአህባሽ አጀንዳ› ነው፡፡ ከመንግሥት እና ከአህባሽ የፀዳ ምክር ቤት ደግሞ ይህንን አያስፈፅምም፡፡ ስለዚህም ከመንግሥት ጋር ይላተማል፡፡ ከመንግሥት ጋር ሲላተም ደግሞ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ስም አንዲት ሰባራ ሳንቲም ሳያንቀሳቅስ መንግሥት መላወሻ ያሳጣዋል፡፡ … ይህ ዕይታ በአጭሩ ለበጎም ሆነ ለክፉ መጅሊስ ከመንግሥት ጋር አዎንታዊ ግንኙነት ሊኖረው ግድ እንደሚለው ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ይህም በሌላ አነጋገር ከመንግሥት ጋር ተላትሞ ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት የሚችል መጅሊስ ዕውን ማድረግ አይቻልም ወደሚል መደምደሚያ ያደርሰናል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን በጥሞና ስንመረምረው ‹‹የአህባሽ አጀንዳ›› የደቀነብንን ችግር ዴሞክራሲያዊም ሆነ ኢ-ዴሞክራሲያዊ የመጅሊስ ምርጫ አይፈታውም የሚል ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን፡፡ … ታዲያ ምን ተሻለ? መፍትኄውስ ምንድን ነው? …

ኖሮ ካልጠቀመ፣ ቢሞት አይጎዳም፡፡ …

የመጅሊስ ህልውና የመንግሥትን ዕውቅና የሚያገኘውና መጅሊሱ በሁለት እግሩ መቆም የሚችለው [መቻል ከተባለ!] ጽዮናዊያን-ሠራሹን የአህባሽ መርኃ-ግብር ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ሲያስፈፅም ብቻ ከሆነ፣ መጅሊሰ የሚባለው ተቋም መኖሩ በራሱ ለህዝበ-ሙስሊሙ ከፍተኛ አደጋ ነው፡፡ … ይበልጡንም የአህባሽ ሥልጠና ከተጀመረበት ከሐምሌ ወር 2003 አንስቶ በተለያዩ መድረኮች ላይ ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ባለሥልጣናት አንደበት የተሰሙ መጅሊሱ እንዲጫወታቸው የሚፈለጉ ሚናዎችን በጥሞና ስናስተውል፣ ተቋሙ የህዝበ-ሙስሊሙን ሕገ-መንግሥታዊ መብቶችና ነፃነቶች የመሸርሸርያ መሣርያ እንዲሆን ብቻ እየተፈለገ እንደሆነ መረዳት አይከብደንም፡፡ … በዚህ ሂደት እኛም ሳናውቀውና ነገሩን በጥልቀት ሳንተነትነው ለዚህ የመንግሥት ፍላጎት ግብዓት የሚሆኑ ጥያቄዎችን ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ … ለምሳሌ ‹‹መጅሊሱ በአዋጅ ይቋቋምልን›› የሚል በህዝበ-ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴም ጭምር የተስተጋባ ጥያቄ አለ፡፡ …የጽዮናውያን ውልድ የሆነው የወቅቱ ሙሲባ ሳይመጣብን፣ በደጉ ጊዜ [ከሞላ ጎደል] ቢሆን ኖሮ ይህ ጥያቄ ተገቢ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ የመጅሊሱ ተቋማዊ ሰውነት ለዕኩይ ዓላማ ሊውል እየተፈለገ ባለበት በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ጥያቄ ‹‹የታሰቡልን›› ዕኩይ እቅዶች ሕጋዊ መሠረት እንዲኖራቸው ከመደገፍ የተለየ ትርጉም ያለው አይመስለኝም፡፡ …

‹‹በመንግሥት ውስጥ መንግሥት›› ትሻላችሁን?

በአጠቃላይ የመጅሊሱ ሚና በመንግሥት በሚታሰበውና በታቀደው መልኩ የሚገለጥ ከሆነ፣ መጅሊሱ ‹‹በመንግሥት ውስጥ ያለ መንግሥት›› (A state within a state) ሆኖ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሕገ-መንግሥታዊ መብትና ነፃነቶች ከዚህ ተቋም ፈቃድ እንዲመነጩ የሚያደርግ ነው፡፡ በግልም ሆነ በጋራ ሃይማኖታዊ መጽሐፍ ጽፎ ማሳተም፣ የኢስላማዊ በጎ-አድራጎት ድርጅት ማቋቋም፣ መድረሳ መክፈት፣ መስጂድ መገንባት ወዘተ. የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች ሆነው ሳለ፣ ለመጅሊሱ በህዝበ ሙስሊሙ ጉዳዮች ላይ የፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣን በአዋጅ ማስሰጠት በእኔ ዕይታ በራስ ላይ እባብ መጠምጠም ነው፡፡

…አሁን ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ጥያቄው ‹‹ሕገ-መንግሥታዊ መብትህ/ሽ ከመጅሊሱ በጎ-ፈቃድ እንዲመነጭ ትፈልጋላችሁን?›› የሚል ነው፡፡ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እኔ ይህ በፍፁም እንዲሆን አልፈልግም፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት የተረጋገጡ (ወይም የተደነገጉ) መብቶችና ነፃነቶቼ በማንም /በመጅሊስም፤ በመንግሥትም/ ሳይሸራረፉ እንዲከበሩልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ኢስላማዊ መጽሐፍ ጽፌ ማተሚያ ቤት ከመሄዴ በፊት ለመጅሊስ ‹‹ሳንሱር›› ማስደረግ አልፈልግም፡፡ የአገሬ ሕገ-መንግሥት ይህንን አይፈቅድምና፡፡ … ህዝብን ከህዝብ ሊያጋጭ፣ በአጠቃላይ በወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል ነገር ጽፌ ካሳተምኩ የሕግ ተጠያቂነት ይኖርብኛል፡፡ ከዚህ ውጪ ስለፈለግሁት ነገር የማሰብ መብትና ነፃነት አለኝ፤ የመጻፍና የማሳተምም እንዲሁ፡፡ ቢሻኝ ስለ እስልምና፣ ቢሻኝ ስለክርስትና፣ ቢሻኝ ስለ ቡድሂዝም፣ ስለ ሒንዱይዝም፣ ስለ ሺንቶይዝም፣ … ስለፈለግሁት ሃይማኖት፣ እምነት ወይም ስለ ኢ-አማኒነት የመመርመር፣ መርምሬ ያወቅሁትንም ጽፌ ለወገኖቼ የማካፈል መብቴ በሕገ-መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ‹‹ሕገ-መንግሥቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው›› በሚባልበት አገር እኒህንና ሌሎችንም ማንኛቸውንም መብቶቼን ማንም ከአዋጅ በሚመነጭ ሥልጣን እንዲወስድብኝ አልፈቅድም፡፡ … መጅሊስ እንዲህ ዓይነት ሚና እንዲጫወት የሚፈለግ ከሆነ እኔ መጅሊስ እንዲኖረኝ አልፈልግም፡፡ … መንግሥት መጅሊሱን መቆጣጠር የሚሻው በዜግነቴ ያለኝን ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች በእጅ አዙር ሊነጥቀኝና ‹‹የመንግሥት ያለህ!›› ብዬ ስጮህ ደግሞ ‹‹በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አልገባም›› ብሎ ሊቀልድብኝ ከሆነ … እደግመዋለሁ … እኔ መጅሊስ አልፈልግም!! እንዲህ ዓይነት መጅሊስ ከሚኖረኝ … ከነጭራሹ መጅሊስ ራሱ ባይኖር እመርጣለሁ፡፡ …

About Us

WHAT WE DO

 • Da'awa
 • Unity
 • Advocancy
 • Development

Departments

 • Da'awa
 • Media
 • Finance
 • Convention
 • Community Relations
 • Badr Sisters
 • Youth
 • Ethiopian Relations
 • International Relations
 • Marriage