Deprecated: Non-static method JSite::getMenu() should not be called statically, assuming $this from incompatible context in /home/badrtube/public_html/badrethiopia.org/oldsite/templates/yoo_revista/warp/systems/joomla/layouts/com_content/article/default.php on line 13

Deprecated: Non-static method JApplication::getMenu() should not be called statically, assuming $this from incompatible context in /home/badrtube/public_html/badrethiopia.org/oldsite/includes/application.php on line 536

በረከተ-መርገም በ‹ኢቴቪ› ደጃፍ

Posted in Amharic Articles

Oct 30, 2012 | ነስሩዲን ዑስማን

በሁለተኛው ታሪካዊ የኢድ ተቃውሞ አንዳንድ ገፅታዎች ላይ ያተኮረ ምልከታ

በዋዜማው …

ዕለተ ሐሙስ ጥቅምት 15፣ 2005 ከቀኑ በ__ ሰአት፣ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የኢድ አል አድኃ (አረፋ) ትዕይንተ ተቃውሞ አፈጻጸም በህዝበ ሙስሊሙ የመብት ማስከበር እንቅስቃሴ የፌስቡክ አሚር አማካይነት ይፋ ተደረገ፡፡ ህዝቡ ተቃውሞውን የሚገልፅበት መንገድና የሚያስተጋባቸው መፈክሮች ተነገሩ፡፡ ‹‹…ተሰግዶ እንዳለቀ ለ5 ደቂቃ ቢጫ እናውለበልባለን፡፡ ከዚያም እነዚህን መፈክሮች ለእያንዳቸው 5 ደቂቃ እየሰጠን እንላለን፡ ምርጫው ሕገ ወጥ፣ ምርጫው የካድሬ፣ ምርጫው የአህባሽ፣ ዳግም ምርጫችን በመስጂዳችን፣ ያልመረጥነው አይመራንም ወዘተ.›› ...ከአሚሩ በተላለፉት የመፈክሮች ዝርዝር ውስጥ ‹‹ኢቲቪ ሌባ!››፣ ‹‹ኢቲቪ ውሸታም!››፣ ‹‹ዉሸት ሰለቸን!›› የሚሉ አልነበሩም፡፡…

በዕለቱ …

… የኢድ ሶላቱ ከመጀመሩ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ ይህ ፀሐፊ በነበረበት (ክቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ) አቅራቢያ አንድ የፌደራል ፖሊስ ባለማዕረግ የአዋቂ መዳፍ በሚያህል መጠን ተቆራርጠው የተዘጋጁ በግምት 1,500 የሚሆኑ ቢጫ ወረቀቶችን በሁለቱ እጆቹ ጠበቅ አድርጎ ይዞ ወደ መኪናው ሲያመራ ታየ፡፡ አንዱ ወንድማችን ለህዝብ ሊያድል ያመጣቸው፣ ግን ከመታደላቸው በፊት የተወረሱ ‹‹ቢጫ ወረቀቶች›› ነበሩ፡፡ ‹‹ተሰግዶ እንዳለቀ… ቢጫ እናውለበልባለን›› የሚለውን የአሚራችን መመሪያ መንግሥትም አንብቦት ኖሯል፡፡ ‹‹ለካ መንግሥታችን ቢጫ ካርድ ማየት አይፈልግም!›› የሚል ሐሳብ ሽው አለብኝ፡፡ ቢጫ ጨርቄን ቶሎ ኪሴ ከተትኋት ‹‹ሳላውለበልብ እንዳልወረስ!››

‹‹ሰላተል ጃሚያ!...›› ከተባለ በኋላ ከተቀመጥንበት ተነስተን ለሶላት እንደተዘጋጀን አሰጋጁ ሸኽ ጠሃ የሆነ ነገር ተናገረ፡፡ ድምፁ እንጂ ቃላቱ እኛ እነበርንበት ሥፍራ ጥርት ብሎ አልተሰማም፡፡ የሰውየውን ንግግር ንግግር ተከትሎ ከስታዲየሙ ውስጥ ከፍተኛ የተክቢራ ድምፅ ተስተጋባ፡፡ … ኋላ እንደሰማነው ተክቢራው አቶ ጠሃ ለተናገረው ንግግር የተሰጠ ምላሽ ነበር፡፡ አቶ ጠሃ ማሰገድ ሊጀምር ሲል፣ ‹‹የመጣነው ለሰላት ብቻ ነው፡፡ ሌላ ትርፍ ነገር አያስፈልግም!›› የሚል ማስጠንቀቂያ ይሁን ትዕዛዝ ብጤ አስተላልፎ ኖሮ፣ ስታዲየሙ ውስጥ ያለው ህዝብ ‹‹የሚሰማህ የለም!›› ብሎት ኖሯል ለካ በተክቢራ፡፡

… ሶላቱ ተጀመረ፤ ሰገድን አላህ ይቀበለን፡፡ ሶላቱ እንደተፈፀመ ይህ ፀሐፊ የጫማውን ክሮች አስሮ ሳይጨርስ የተቃውሞው ሞተር የአላህን ታላቅነት፣ የፍጡራንን ከንቱነት በሚያወሳው ኃያል ቃል ተለኮሰ ‹‹አላሁ አክበር!›› ‹‹አላሁ አክበር!›› ‹‹አላሁ አክበር!›› … ከመወረስ የዳኑ ቢጫ ወረቀቶች እና ጨርቆች ይወለበለቡ ጀመር፡፡ በA-3 እና በA-4 ነጭ ወረቀቶች ላይ የተጻፉ በርካታ መፈክሮች ከቢጫ ወረቀቶቹ ጎን ከፍ ተደረጉ፡፡ በተክቢራ የተሟሟቀው ተቃውሞ ከአሚራችን በተላለፉት መፈክሮች ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ አንድ ወንድማችን በግማሽ ገጽ ወረቀት ላይ ቁልቁል ደርድሮ ከጻፋቸው መፈክሮች ውስጥ ከፍ ባለ ድምፅ ለማስተጋባት የሚመቸውን መርጦ ባለ በሌለ ኃይሉ ጮኸው፡፡ እሱ ‹‹ያልመረጥነው…›› ከማለቱ ‹‹አይመራንም!›› የሚሉ ድምፆች ተከተሉት፡፡ ‹‹ያልመረጥነው አይመራንም!›› አንድ አሥር ጊዜ እንደተስተጋባ የልጁ ድምፅ መሻከር ሲጀምር፣ ሌላ ወንድም በሌላ መፈክር ተረከበው፡፡ ‹‹ድምፃችን …›› ሲል በዚያ የነበረው ሁሉ ‹‹ይሰማ!›› በሚል ህብረ ድምፅ ተቀበለው፡፡ … ከአሚራችን የተላለፉት አብዛኞቹ መፈክሮች በነጭ ወረቀቶች ላይ በእጅና በኮምፒዩተር ተጽፈው በብዙዎቹ ሰልፈኞች ከፍ ተደርገው ይታዩ ነበር፡፡ ..ባለንበት ለተወሰኑ ደቂቃዎች መፈክሮችን እየተቀባበልን ካስተጋባን በኋላ፣ ፊታችንን ወደ ሰሜን አቅጣጫ በማዞር በቸርችል ጎዳና ላይ መፈክሮችን እያሰማን በዝግታ መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡ አሁን ‹ሪትም› ውስጥ ገብተናል፡፡…

… የብሔራዊ ቴአትር የትራፊክ መብራት እንደታለፈ፣ የሰልፈኛው ዓይኖች ከፊት ለፊት በስተግራ ከተገተረው ግራጫ ሕንፃ ላይ አረፉ፡፡ በዚያው ቅፅበት አዳዲስ መፈክሮች ተወለዱ፡፡ ከሰልፈኛው መካከል አንዱ ‹‹ኢቲቪ ሌባ!›› ሲል ጮኸ፡፡ ቁጣ እና እልህ የሚተናነቃቸው የብዙኃን ድምጾች በአዲስ ጉልበት አዳዲስ መፈክሮችን ያስተጋቡ ጀመር፡፡ ‹‹ኢቲቪ ሌባ!›› ፣ … ‹‹ኢቲቪ ዉሸታም!›› … ‹‹ዉሸት ሰለቸን!›› …ሰልፈኞቹ ወደ ሕንፃው በቀረቡ ቁጥር ድምጻቸው ከመዳከም ይልቅ ኃይል እየጨመረ ይስተጋባ ነበር፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢቲቪ ቅጥረ ግቢ ከሰው ቁመት ብዙም ከፍ ከማይል ግማሽ ግንብ፣ ግማሽ የብረት አጥር ባሻገር ወለል ብሎ ይታይ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ከሰው ቁመት በላይ በሆነ የደንጊያ አጥር ታሽጎ፣ ከአጥሩም ባሻገር ቤቢ ፊያት በሚያካክሉ ኮንክሪቶች ተከብቦ ወህኒ ቤት መስሏል፡፡ ‹‹ፈስ ያለበት…›› እንዲሉ፡፡ … ሰልፈኞቹ ከጣቢያው ደጃፍ ላይ ሁነው ያሰሙት የነበረው ድምፅ ከግቢው አጥር አልፎ በህንጻው አሥረኛ ፎቅ ላይ የሚገኝ ቢሮ ውስጥ ያለን ሰው ከመቀመጫው አስፈንጥሮ የሚያስነሳ ነበር፡፡ … በሺህዎች የሚቆጠር ህዝብ ከግቢው ደጃፍ ላይ ቆሞ ‹‹ኢቲቪ ሌባ!››፣ ‹‹ኢቲቪ ዉሸታም!››፣ ‹‹ዉሸት ሰለቸን!››፣ ‹‹ሕዝቡን አትዋሹ!›› … እያለ ሲጮህ፣ የጣቢያው ምስለኔዎች ከየቢሯቸው መስኮት አጮልቀው፣ አንዳንዶቹም ፊታቸውን በእጃቸው መዳፍ ከለል አድርገው ያያሉ፡፡

* * *

የመንግሥት ሚዲያ የህዝበ ሙስሊሙን እንቅስቃሴ ዘግቦት አያውቅም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት በህዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄ አንጻር የሚሠራቸውን የራሱን ‹ድራማዎች› ሲዘግብ፣ እግረ መንገዱን ‹‹አንዳንድ/ጥቂት ድብቅ ዓላማ ያላቸው አክራሪዎች የሐሰት ወሬ በመንዛት … ህዝቡን በማሳሳት … ለፀረ ሰላም ተልዕኳቸው አሰልፈውት … ወዘተ.›› የሚሉ አርቲ ቡርቲ ወሬዎችን ያወራል፡፡ የኢድ አል አድኃ ዕለት ከሶላት በኋላ በቸርችል ጎዳና ላይ ይተም የነበረው ሰልፈኛ የኢቴቪን ሕንጻ ባየበት ቅፅበት ያስተጋባቸው መፈክሮች ጣቢያው ለሚነዛቸው የሐሰት ፕሮፖጋንዳዎች ከህዝብ የተሰጡ የቁጣ ምላሾች ነበሩ፡፡ እጅብ ብለው ቢጫ እያውለበለቡ የሚተሙት ሰልፈኞች እርስ በእርስ አይተዋወቁም፡፡ ሁላቸውም ግን ኢቴቪ ጋር ሲደርሱ ፍፁም ተመሳሳይ የቁጣና የእልህ ስሜት ይታይባቸው ነበር፡፡ የድምጻቸው መጉላት በጣቢያው ላይ ያደረባቸውን ከፍተኛ ጥላቻ በግልፅ ያንፀባርቃል፡፡ ያስተጋቧቸው መፈክሮች ከማንም ተፅፈው የተሰጡ አይደሉም፡፡ ይህ እውነታ የእንቅስቃሴው ባለቤት ህዝበ ሙስሊሙ ራሱ መሆኑን በግልፅ ያሳያል፡፡ ከጀርባም፣ ከፊትም፣ ከጎንም፣ ከአናትም ሌላ ማንም የለም፡፡ ህዝብ ከኢቲቪ ጋር ፊትለፊት ተገጣጠመ፤ ህዝብ የጋራ ስሜቱን፣ የጋራ ቁጣውን ገለፀ ‹‹ኢቲቪ ሌባ!›› … ‹‹ኢቲቪ ዉሸታም!›› … ‹‹ዉሸት ሰለቸን!›› … አለ፡፡

* * *

… በሺህዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ከደጃፉ ተኮልኩለው ፀረ ኢቴቪ መፈክሮች በሚያስተጋቡበት በዚያ ቅፅበት ኢቴቪ ውስጥ ምን እየተሠራ ነበር? … ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የዘንድሮዉን የኢድ አል አድኃ አከባበር የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሆኑ ሬዲዮ በቀጥታ አላስተላለፉትም፡፡ ቢያስተላልፉት ሶላቱ ሊጀመር ሲል ሸኽ ጠሃ ያደረገውን ተንኳሽ ንግግር ተከትሎ በስታዲየሙ ውስጥ የተስተጋባው የህዝበ ሙስሊሙ ተክቢራ በቀጥታ ከህዝብ ጆሮ ይደርስ ነበር፡፡ … ከሁለት ወር በፊት የዒድ አል ፊጥር ሶላት ተሰግዶ እንዳበቃ ሸኽ ጠሃ ኹጥባ (ሃይማኖታዊ ዲስኩር) ሊያደርግ ሲል በስታዲየም ውስጥ የነበረው ህዝብ በከፍተኛ የተክቢራ ድምፅ ንግግሩን አፈነበት፡፡ ሸኽየው ተበሳጭቶ ኹጥባውን በማቆም፣ ‹‹ምንድነው፣ ፖሊስ የለም እንዴ?!›› አለ፡፡ ማይክሮፎኑ አልተዘጋም ነበርና ይህ የሸኹ ንግግር ከስታዲየሙ አልፎ በኤፍ ኤም 97.1 ለአዲስ አበባና ለአካባቢዋ ህዝብ በግላጭ ተሰምቶ ነበር፡፡ … የኢድ አል አድኃ የሶላት ስነ ስርዓት በቀጥታ ያልተላለፈው አንድም እንዲህ ያለው ውርደት እንዳይደገም በመፍራት ይመስላል፡፡

… ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ኢቴቪ የጋዜጠኝነት ሙያ ስነ ምግባር በሚያዝዘው መሠረት በመሬት ላይ ስላለው ሐቅ ተጨባጭ መረጃ ለሕዝብ የሚያቀርብ ጣቢያ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ በሚጻረር መልኩ፣ የጣቢያው ዋነኛ ተግባር የኢህአዴግን ፕሮፖጋንዳ መለፈፍ ከሆነ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየም የኢድ ሶላቱ ልክ 2፡00 ሰአት ላይ ተጀምሮ 2፡07 ላይ ቢያበቃም፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜናውን ያስተላለፈው ከቀኑ 8፡00 ሰአት ላይ ነው፡፡ እስከዚያ ሰአት ድረስ ምን ሲሠራ እንደቆየ ኢዱን አስመልክቶ ያስተላለፈው ዜና ራሱ ይናገራል፡፡ …

በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደውን ሶላት አስመልክቶ ባቀረበው ዜና፣ ‹‹አንዳንድ ሰዎች በቅርቡ በነፃና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተካሄደውን የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ምርጫ በመቃወም ረብሻ ለማስነሳት ሙከራ አድርገዋል›› ብሏል፡፡ የህዝበ ሙስሊሙን ግዙፍ ትዕይንተ ተቃውሞ በዚህ መልኩ አድበስብሶ ሲያቀርብም፣ የተቃውሞውን ትክክለኛ ገፅታ ላለማሳየት በመሻት ከአንድ ጠርዝ ላይ ደርዘን የማይሞሉ ሰዎችን በጣም አቅርቦ (extreme close-up) በከፍተኛ ጥንቃቄ የተመረጠ ምስል አሳይቷል፡፡ [ሚያዝያ 30፣ 1997 ከ1.5 ሚሊዮን የሚልቁ የቅንጅት ደጋፊዎች ያደረጉትን ሰልፍ ኢቴቪ ሲዘግብ፣ ከጠቅላላው ህዝብ ይልቅ የተቆነፃፀሉና ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ የታለሙ ምስሎችን ብቻ ማሳየቱ ይታወሳል፡፡ የኢድ ዕለት የሠራውም ይህንኑ ነው፡፡] …

በዚሁ የኢድ ዘገባ ላይ ኢቴቪ ህዝቡ ከስታዲየም ወጥቶ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞውን በአደባባይ እያስተጋባ በነበረበት ቅፅበት ወደኋላ ቀረት ካሉ የአህባሽ ጀሌዎች አንድ ሁለቱን አነጋግሮ ምላሻቸውን አስደምጦናል፡፡ አንደኛው ‹አገር አማን ነው፤ ምንም ኮሽ ያለ ነገር የለም› ብሎ በአደባባይ ሲሸመጥጥ፣ ሌላኛው በበኩላቸው ‹‹የመጅሊስ ምርጫ በወረዳ ደረጃ ብቻ ነው የተካሄደው፤ የዋናው መጅሊስ ምርጫ ገና አልተካሄደም፤ ስለዚህ ህዝቡ ዝም ብሎ ከሚጮህ በትዕግስት ቢጠብቅ ይሻላል›› በማለት የወጣቱን ሽምጠጣ እዚያው በዜሮ አባዝተውታል፡፡

‹‹በሰላም ተጠናቋል?!›› … ‹‹ምን እንዲፈጠር ተጠብቆ ኖሯል?›› …

... ኢቲቪ በተለያዩ የክልል ከተሞች የኢድ አል አድኃ አከባበርን ሲዘግብ፣ ሶላቱ በሰላም ስለመጠናቀቁ ከመናገር በስተቀር ከሶላት በኋላ ስለተካሄዱ የህዝበ ሙስሊሙ የተቃውሞ ትዕይንቶች አንድም ቃል አልተነፈሰም፡፡ ሶላቱ በሰላም ተሰግዶ መጠናቀቁ ሀሰት ባይሆንም፣ ከሶላቱ በፊትም ሆነ በኋላ የተካሄዱ ዐበይት ክንውኖችን መግደፍ ዜናውን ምሉዕ እንደማያደርገው በጋዜጠኝነት ሙያ፣ ይበልጡንም በዜና አጻጻፍ ላይ ያተኮሩ ጽሑፎች በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡ … በአንድ አንጋፋ ጋዜጠኛ የተጻፈ መጽሐፍ ስለ ዜና ምንነት ከሰጠው ድንጋጌ (definition) አኳያ በዕለተ ኢድ አል አድኃ በአዲስ አበባና በየክልሎቹ በተሰገደው ሶላት ዙርያ ለሚዘግብ ባለሙያ ጋዜጠኛ (professional journalist)፣ ዐብይ ዜና መሆን የነበረበት የህዝበ ሙስሊሙ ተቃውሞ እንጂ ስግደቱ አልነበረም፡፡ … እርግጥ፣ በአሁኑ ወቅት በየዕለቱ የጥፋት እሳት በሚነድባት ሶሪያ ወይም የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች በሚበዛባት ባግዳድ ‹‹የኢድ ሶላት በሰላም ተሰግዶ መጠናቀቅ›› ራሱን የቻለ ዐብይ ዜና ሊሆን ይችላል፡፡ …ኢትዮጵያ ግን ሶሪያ ወይም ባግዳድ አይደለችም፡፡ ራሱ መንግሥት ሁከት በመፍጠር ዓላማ ካልተንቀሳቀሰ በቀር የህዝበ ሙስሊሙ መብትን የማስከበር የተቃውሞ እንቅስቃሴ ፍፁም ሰላማዊ መሆኑ ከአገር ውስጥ አልፎ በዓለም ዙርያ በሰፊው ታውቋል፡፡ ከዚህ አኳያ ‹‹በሰላም ተጠናቋል›› ላይ ያተኮረው የኢቴቪ ዜና፣ ‹‹ምን እንዲፈጠር ተጠብቆ ኖሯል?›› የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ይጋብዘናል፡፡ …

‹‹ኢቴቪ ሌባ?!›› - ኢቴቪ ምን ሰረቀ?! …

ከአዲስ አበባ ውጪ በየክልሉ ከተሞች በተካሄዱ ስግደቶች ላይ ያተኮሩት ‹‹ዜናዎች›› በሙሉ ‹‹ስግደቱ በሰላም ተካሂዶ ተጠናቅቋል›› በሚል ጀምረው፣ ‹‹የዘንድሮውን ኢድ ለየት የሚያደርገው…›› በሚል ያረጀና ያፈጀ ቋንቋ (cliché) ለዛ ቢስ ፌዝ ቀላቅለው የሚያልቁ መሆናቸው አንድ ያልተነገረ ነገር፣ ያልተነገረ ሐቅ መኖሩን ጠቁሟል፡፡ ...ኢቴቪ ህዝብ እንዲሰማ ያልፈለገው ያንን ሐቅ ነው፡፡ የጋዜጠኝነት ምሁራን በዜና ዘገባ የአንድን ክስተት ዐብይ ገፅታ መግደፍ (omission) ሙያዊ ነውር ወይም ብልግና እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ይህ ተግባር ለህዝብ ሊነገርና ህዝብ ሊያውቀው የሚገባን ሐቅ (መረጃ) አፍኖ ማስቀረት ማለት ነው፡፡ በመርካቶ ቋንቋ ሲገለፅ ኢቴቪ የህዝብ መብት ከሆነው መረጃ ላይ ‹‹ፈርቅ ይዟል›› ማለት ነው፡፡ ከአንድ አገር ህዝብ መብት (ሐቅ) ላይ ‹‹ፈርቅ መያዝ›› ያው መስረቅ ማለት ነው ሌብነት ነው፡፡ …

… የዒድ አል አድኃ ዕለት ‹‹ኢቴቪ ሌባ!›› እያልን የጮህነው፣ ላለፉት አሥራአንድ ወራት ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እያካሄድን ባለነው መብታችንን የማስከበር እንቅስቃሴ ዙርያ ኢቴቪ ከእኛ እንደ ዜጋ የመሰማት (የመደመጥ) መብት፣ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ደግሞ ትክክለኛ መረጃ የማግኘት፣ ወይም የመቀበል መብት ላይ በዋጋ ሊተመን የማይችል ‹‹ፈርቅ›› ስለያዘብን ነው፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ የኢቴቪ ሌብነት ‹‹ፈርቅ ከመያዝ››ም እጅግ ይከፋል፡፡ ‹‹ፈርቅ›› የተወሰነውን ለባለመብቱ ሰጥቶ ጥቂት ወደራስ ማስቀረት ነው፡፡ ኢቴቪ (ባጠቃላይም የመንግሥት ሚዲያ) ባለፉት አሥራአንድ ወራት ከህዝበ ሙስሊሙ የመሰማት (የመደመጥ)፣ ሙስሊም ካልሆነው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ትክክለኛ መረጃን የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ላይ 1 ከመቶ ያህል እንኳ ሳያስተርፍ፣ ሙስሊሙን ‹‹አልሰማህም፤ አላሰማልህም››፣ ሙስሊም ያልሆነውን ወገን ደግሞ ‹‹አላሳይህም፤ አላሰማህም›› ሲለው ነው የከረመ፡፡ … ታዲያ ለኢቲቪ ‹‹ሌባ!›› መባል ቢያንሰው እንጂ ይበዛበታልን?! …

‹‹ኢቲቪ ሌባ!›› = ‹‹ኢህአዴግ ሌባ!››፣ therefore ‹‹መንግሥት ሌባ!››

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኤጀንሲን ሙሉ በሙሉ ገዢው ፓርቲ (ኢህአዴግ) ነው የሚቆጣጠረው፡፡ በመሆኑም ከኤጀንሲው ጣቢያዎች የሚሰራጩ የአገር ውስጥ ዘገባዎች በሙሉ የኢህአዴግን ብሎም የኢህአዴግ መራሹን መንግሥት አቋም፣ አስተሳሰብና ማንነት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ መስታወቶች ናቸው፡፡ ኢቲቪ እና ኢህአዴግ አንድና ያው ናቸው፡፡ የኢቲቪ ቅጥፈት፣ የኢህአዴግ ቅጥፈት ነው፡፡ በኢቲቪ የሚሠራጭ ‹ፖለቲካዊ ድራማ› ደራሢውም፣ አርታዒውም፣ አዘጋጁም፣ ፕሮዲዩሰሩም ኢህአዴግ ነው፡፡ [እርግጥ ‹የሥራ ሂደት ባለቤት› ወዘተ. የሚል፣ ጋዜጠኛ ሲጠራበት ተሰምቶ የማይታወቅ ‹‹ቢፒአራዊ ማዕረግ›› ያላቸው ምስለኔዎች (ኅሊናቸውን ለመናኛ የወር ደመወዝ የሸጡ የጉልበት ሠራተኞች) አሉ፡፡] … ጁሙዓ ዕለት ከኢድ ሶላት በኋላ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና መሥሪያ ቤት ደጃፍ ላይ ተሰብስበን ‹‹ኢቲቪ ሌባ!››፣ ‹‹ኢቲቪ ውሸታም!›› ወዘተ. እያልን ለተራዘሙ ደቂቃዎች ያሰማነው መፈክር ‹‹ኢህአዴግ ሌባ!››፣ ‹‹ኢህአዴግ ውሸታም!›› ከማለት በምንም አይለይም፡፡ ኢህአዴግ መንግሥት እንደመሆኑም ‹‹ኢህአዴግ ሌባ!››፣ ‹‹ኢህአዴግ ውሸታም!›› ስንል፣ ‹‹መንግሥት ሌባ!››፣ ‹‹መንግሥት ዉሸታም!›› እያልን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡…

‹‹ኢቲቪ›› የመንግሥታችን ልክ! …

ኢቲቪ ማለት ኢህአዴግ፣ ኢህአዴግ ማለት መንግሥት ማለት ከሆነ፣ በቀመሩ መሠረት ኢቲቪ ማለት መንግሥት ማለት ነው ብለናል፡፡ ስለዚህም በኢቲቪ ‹‹ዘገባዎች›› የሚንፀባረቁ አቋሞች፣ አስተሳሰቦች እና ሐሳቦች የመንግሥት አቋሞች፣ አስተሳሰቦች እና ሐሳቦች ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ የኢቲቪን የዕለተ ኢድ አል አድኃ ዘገባ መነሻ በማድረግ በመንግሥት ላይ ሁለት መሠረታዊ ነውሮችን ነቅሰን ማውጣት እንችላለን፡፡ በኢቲቪ ዘገባ ላይ በግልፅ እንደተንፀባረቀው፣ መንግሥት ከጠቅላላ የአገሪቱ ህዝብ ግማሽ ያህል የሚሆነው ህዝበ ሙስሊም በመላው አገሪቱ ያደረገውን የተቃውሞ ትዕይንት ‹‹አላየሁም››፣ ያስተጋባውን የእሮሮ ድምፅም ‹‹አልሰማሁም›› ብሏል፡፡ … ህዝበ ሙስሊሙ በዕለቱ የተካሄደው ሰላማዊ ተቃውሞ ተዋናይ እንደመሆኑ በኢቲቪ ዘገባ የተንፀባረቀው የ‹‹አላየሁም››፣ ‹‹አልሰማሁም›› ክህደት ለመንግሥት የህዝበ ሙስሊሙን ከፍተኛ ትዝብት ከማትረፍ በቀር ምንም አያስገኝለትም፡፡ …

በሌላ በኩል፣ ዘገባው የዕለቱን ዐብይ ክስተት (የህዝበ ሙስሊሙን ተቃውሞ) መግደፉ፣ ሙስሊም ባልሆነው፣ ነገር ግን በአገሪቱ ውስጥ ስለተፈጠሩ ዐበይት ጉዳዮች መረጃ የማግኘት መብት ባለው ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይም ጭምር የተፈፀመ ሸፍጥ ነው፡፡ ስለመብቱ የጮኸን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝበ ሙስሊም ‹‹አልሰማሁህም››፣ ‹‹አላየሁህም›› ማለት እጅግ ነውር የሆነውን ያህል፣ በየቤቱ ስለአገሩ ጉዳይ በኢቲቪ ለሚከታተለው ህዝብ ስለ ዕለቱ ዐብይ ክስተት ምንም ዓይነት መረጃ አልሰጥህም ማለትም በዜጋው መረጃ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ላይ የሚፈፀም ሸፍጥ ነው፡፡

… ኢቲቪ/መንግሥት ላለፉት አሥራአንድ ወራት ፍፁም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን የህዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ ትክክለኛ ስዕል ሙስሊም ላልሆነው የአገሪቱ ዜጎች አለማቅረቡ ብቻ አይደለም የሚያሳዝነው፡፡ ይበልጥ የሚያሳዝነው ትክክለኛውን መረጃ የማግኘት መብት ያለው ዜጋ፣ ሆን ተብሎ ገሸሽ በተደረገው የህዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄ ምትክ፣ በየጊዜው ያፈጠጡ የሐሰት ፕሮፖጋንዳዎች የሚንነዙለት መሆኑ ነው፡፡ 90 ሚሊዮን ሕዝብ የሚያሥተዳድር መንግሥት የከፊሉን (ህዝበ ሙስሊም) ጥያቄ ገሸሽ ከማድረጉ እና የሌላኛውን ከፊል (ሙስሊም ያልሆነውን) ዜጋ ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት ከመርገጡ ባሻገር፣ በተለይ ሙስሊም ላልሆነው ወገን ሆን ብሎ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ መመገቡ፣ በዚህም የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የአገሪቱ ሙስሊምና ሙስሊም ያልሆነው ዜጋ እርስ በእርሱ በጥርጣሬ እንዲተያይ ማለሙ እጅግ አሳዛኝ፤ እጅግ በጣምም አሳፋሪ ነው፡፡

በአሁኑ ሰአት ሙስሊም ካልሆኑ ኢትዮጵያዊያን መካከል ትክክለኛ መረጃ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመነፈጋቸው፣ በህዝበ ሙስሊሙ የመብት እንቅስቃሴ ዙርያ የመንግሥት ሚዲያ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሰለባ የሆኑ ዜጎች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ የዚያኑ ያህልም በተለያዩ መንገዶች እውነቱን በውል የተረዱ ሙስሊም ያልሆኑ የአገራችን ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ዕድሜ ለኢንተርኔት ቴክኖሎጂ፣ የህዝበ ሙስሊሙን የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ ሙሉ ስዕል የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች በየዕለቱ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገፆች ላይ ይታተማሉ፡፡ ድምፁ የታፈነበት፣ እውነቱ የተካደበት ኢትዮጵያዊው ሙስሊም በእነዚህ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ያላቸው ሚዲያዎች አማካይነት ድምፁን ማሰማት በመቻሉ፣ አገር ውስጥም ሆነ ባህር ማዶ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መብትን የማስከበር ሰላማዊ ትግሉን ትክክለኛ ገፅታና መንፈስ በውል ተረድተዋል፤ እየተረዱም ነው፡፡ … ከእውነት ይልቅ ቅጥፈትን፣ ከሐቅ ይልቅ ክህደትን፣ ለህዝብ ትክክለኛ መረጃ ከመስጠት ይልቅ መንፈግን ዋነኛ መርኅ አድርጎ በመንግሥት ሚዲያ በየጊዜው የሚነዛው እያንዳንዱ ፕሮፖጋንዳ የኢህአዴግን አገር የማስተዳደር የተወላገደ ቀመር እያጋለጠ ይገኛል፡፡ … አገርን ያህል ነገር፣ 90 ሚሊዮን ያህልን ህዝብ ለማስተዳደር ውሸትን ዋነኛ ቀመር አድርጎ ከመጠቀም የበለጠ ምን የሚያሳፍር፣ ምንስ የሚያሳዝን ነገር አለ?!፡፡ …
ለፕሮፖጋንዳም ለውንጀላም ያልተመቹ መረጃዎች …

ህዝበ ሙስሊሙ ላለፉት አሥራ አንድ ወራት አንዳችም ከመንግሥት ዓይንና ጆሮ የተሰወረ እንቅስቃሴ አላደረገም፡፡ የህዝበ ሙስሊሙ የመብት እንቅስቃሴ ህዝባዊ መልክ ከያዘበት ከጥር ወር 2004 አንስቶ በአወሊያም ሆነ በሌሎች መስጊዶች የተካሄዱትን ህዝባዊ ስብሰባዎች፣ የአንድነትና የሶደቃ ፕሮግራሞች እንዲሁም በየመድረኮቹ የተደረጉትን ንግግሮች፣ የተስተጋቡትን መፈክሮች በሙሉ መንግሥት በዓይኑ አይቷቸዋል፤ በጆሮው ሰምቷቸዋል፤ በፊልምም ቀርጿቸዋል፡፡ መንግሥት ነጋ በጠባ በኢቲቪ፣ በአዲስ ዘመን እና በሌሎቹም የፕሮፖጋንዳ መሣሪያዎቹ እንደሚለፍፈው፣ የህዝበ ሙስሊሙ እንቅስቃሴ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ቢኖረው፣ ከአክራሪነት፣ ከጽንፈኝነት ወይም ከአሸባሪነት ጋር የሚያያዝ ቢሆን ኖሮ መንግሥት በደኅንነቶቹ አማካይነት የሰበሰባቸውን ምስሎችና ድምጾች ዋቢ በማድረግ በኢቲቪ አስደማሚ ዶኩመንታሪ በሰራና እኛንም ‹‹ጥቂት ድብቅ ተልዕኮ ባላቸው ቡድኖች›› ከመታለል በታደገን ነበር፡፡ …

… ነገር ግን መንግሥት ይህንን እንኳንስ ለኢትዮጵያ ህዝብ በቴሌቪዥን ሊያቀርብ ቀርቶ፣ በፍፁም ሰላማዊነትና በአርቆ አስተዋይነታቸው የተመሰከረላቸው የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በሽብርተኝነት በከሰሰበት የፍትኅ መድረክ ላይ እንኳ ሊያቀርብ አልቻለም፤ ወይም አልፈለገም፡፡ ለምን? … ምክንያቱ ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ድምጾችም ሆኑ ምስሎች መንግሥት ወህኒ ቤት በወረወራቸው የኮሚቴው አባላትም ሆነ በሌሎቹ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የመሠረተውን የሽብርተኝነት ክስ መሠረተ ቢስነት ያጋልጡ እንደሁ እንጂ፣ የክሱን እውነትነት አያረጋግጡም፡፡ እነዚህ ድምጾችም ሆኑ ምስሎች በኢቲቪ የማይታዩትም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ መንግሥት በየጊዜው ለህዝብ የሚነዛውን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሚጻረሩ እንጂ የሚደግፉ ግብዓቶች ሊሆኑለት አልቻሉም፡፡ እነዚህ ድምጾችና ምስሎች በኢቲቪ ቢቀርቡ በመብት እንቅስቃሴው ላይ በንቃት የማይሳተፈው ሙስሊምም ሆነ ሙስሊም ያልሆነው የአገሪቱ ዜጋ በመብት ጥያቄ እንቅስቃሴው ዙርያ ከሚነዛው ፕሮፖጋንዳ የተለየ አዎንታዊ አስተሳሰብ ስለሚይዙ፣ ኢሕአዴግ በእጁ የሚገኙ የእንቅስቃሴውን ፍትኃዊነት እና የአካሄዱን ሰላማዊነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች አፍኖ፣ በህዝብ ላይ የፈጠራ ወሬ መንዛቱን ቀጥሏል፡፡ እንዲህም በማድረግ ሕገ መንግሥቱን፣ በተለይም የሕገ መንግሥቱን አንቀፅ 29 ሙሉ በሙሉ የሚደረማምስ የመረጃ አሻጥር መሥራቱን፣ ‹‹የመረጃ ፈርቅ›› መያዙንም ገፍቶበታል፡፡

‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› ፖለቲካዊ ጥበብ ስለመሆኑ አላውቅም፡፡ ለእኔ እንደሚገባኝ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› በስህተት ላይ ስህተት፣ በጥፋት ላይ ጥፋት ከመደረብ ውጪ ምንም የማያስገኝ፣ የትም የማያደርስ የፈሪ መንገድ ነው፡፡ … ንፁኃን ዜጎችን ገድሎ ‹‹አክራሪዎች ተገደሉ›› ብሎ ማቅራራት፣ አልፎም ጥቅመኛ ጀሌዎችን በማስተወን በህዝብ ላይ ‹የቴሌቪዥን ድራማ› መሥራት፣ ህዝብ መብቴን ብሎ ሲጠይቅ ‹‹አንዳንድ አክራሪዎች›› … እያሉ ሾላ በድፍን ህዝብን ማደናገር፣ ህዝብንም ማጭበርበር ሌላ ስም የለውም ሌብነት ነው፡፡ … ‹‹ኢቲቪ ሌባ!›› ማለት ይኸው ነው - ወገን፡፡

* * * * * * *

About Us

WHAT WE DO

 • Da'awa
 • Unity
 • Advocancy
 • Development

Departments

 • Da'awa
 • Media
 • Finance
 • Convention
 • Community Relations
 • Badr Sisters
 • Youth
 • Ethiopian Relations
 • International Relations
 • Marriage