Deprecated: Non-static method JSite::getMenu() should not be called statically, assuming $this from incompatible context in /home/badrtube/public_html/badrethiopia.org/oldsite/templates/yoo_revista/warp/systems/joomla/layouts/com_content/article/default.php on line 13

Deprecated: Non-static method JApplication::getMenu() should not be called statically, assuming $this from incompatible context in /home/badrtube/public_html/badrethiopia.org/oldsite/includes/application.php on line 536

ኢህአዴግ በሰብአዊ ፍጡራን ላይ ‹‹ጅምላ ጭፍጨፋ›› ለማካሄድ ከመንደርደር ቆም ብሎ ያስብ!

Posted in Amharic Articles

Oct 22, 2012 | ጉዳዩ ያሳሰባቸው ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች | Article in Pdf
 1. በአሁኑ ወቅት አንድዬ የጋራ ተቋማችን የሆነውን ጠቅላይ ምክር ቤት በመጠቀም የ‹አሕባሽ›ን አስተሳሰብ በእኛ ላይ ለመጫን በምታደርጉት ጀብደኛ ጥረት ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ያነሳነውን ተቃውሞ በጠብ መንዣ ለመፍታት የምታደርጉት ሙከራ ኃላፊነት የጎደለውና ኢ ዴሞክራሲያዊ ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱንም አላስፈላጊ ወደሆነ ሁከት ሊያመራት የሚችል ነው፡፡ በአንድ በኩል የሰላም መኖር ለአገር ልማትና ዕድገት እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑ እየተናገራችሁ፣ በተቃራኒው የአገርን ሰላም ሊያደፈርስ በሚችል መልኩ አርባ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብን የእምነት መስመር በግድ የማስቀየር ጀብደኛ ሥራ ውስጥ መዘፈቃችሁ በጣም አሳፈሪ መሆኑን በግልፅ ልንነግራችሁ እንወዳለን፡፡
 2. እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የአገራችን ሰላም፣ ልማት እና ዕድገት ፀሮች አይደለንም፡፡ አገራችን አድጋ ሕዝቦቿም ከድህነት አረንቋ ወጥተው ማየትን አጥብቀን እንፈልጋለን፡፡ ይህ ፍላጎታችን ዕውን ይሆን ዘንድ የሚጠበቅብንን የዜግነት ድርሻ ለመወጣት የምናስቀምጠው አንዳችም ቅድመ ሁኔታ የለም፡፡
 1. ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለውንና ከሃይማኖታዊ እምነታችን የመነጨውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ከመንግሥት የሚጠበቅ ብልህነት ነው፡፡ ይህንን በማድረግ ፈንታ፣ በ1997 ምርጫ ማግሥት ቅንጅትን ለመሰነጣጠቅ በተጓዛችሁበት መንገድ ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ለመከፋፈል የምታደርጉት ጥረት፣ እውነት እውነት እንላችኋለን ‹‹ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ›› ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ መሆኑን በአጽንኦት ልናሳስባችሁ እንወዳለን፡፡ … እባካችሁ ይሄንን ነጥብ ከ‹ማን አህሎኝ›ነት እና ከግብዝነት ርቃችሁ በእርጋታ … በፍፁም ጥሞና አሰላስሉት፡፡ ሁለቱ እጅግ ለየቅል ናቸው፡፡ መንበረ ሥልጣን በመቆናጠጥ ዓላማ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች በህይወት መቆየትን አጥብቀው ከሚሹት የበለጠ፣ እኛ ሙስሊሞች እምነታችንን ጠብቀን መሞትን አንፈራም፡፡ እውነቱን ማወቅ የምትፈልጉ ከሆነ፣ ዛሬም ቢሆን ለእምነታቸው መሰዋትን የሚናፍቁ ጥቂት አይደሉም፡፡ የዚህ ምሥጢር ለእናንተ አይገባችሁም፡፡
 2. የሃይማኖት ነጻነታችን ቢከበር፣ የእምነት ተቋሞቻችን በምናውቃቸው፣ በምናከብራቸውና ከመካከላችን በምንመርጣቸው ብቁ እና ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች ቢመሩ፣ ይህ ሁኔታ እኛ ለአገራችን ሰላም፣ ልማትና ዕድገት የምንጫወተውን አወንታዊ ሚና ይበልጥ ያጠናክረዋል እንጂ ከቶውንም አያቀጭጨውም፡፡ በአንጻሩ፣ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት “የተረጋገጠው” የሃይማኖት ነጻነታችን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ሲሸራረፍ፣ የእምነት ተቋሞቻችን በማናውቃቸው፣ በማናከብራቸው፣ ባልመረጥናቸው እና ‹እህ› ብለን እንድንሰማቸው የሚጋብዝ አንዳችም መሠረት በሌላቸው ‹‹ሹሞች›› መዳፍ ስር እንዲወድቁ ሲደረግ፣ ይህ ሁኔታ መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ መግባቱን ብቻ ሳይሆን፣ ለእኛ ያለውን ንቀትም የሚያንፀባርቅ ነው ብለን ለማመን ስለሚያስገድደን በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ያድርብናል፡፡ በእርግጥም በአሁኑ ሰአት የከፋ ቅሬታ አድሮብናል፡፡
 3. የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በእኛ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ስም የሚንቀሳቀስ፣ በእኛ ስም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እና ሐብት የሚያንቀሳቅስ ሆኖ ሳለ፣ ላለፉት አሥራስምንት ዓመታት ኃላፊዎቹ መላ ህዝቡ በግልፅ በሚያውቀው መልኩ በኢህአዴግ መራሹ መንግሥት መሾማቸውና ሹማምንቱም ለእኛ ተጠያቂነት የሌላቸው መሆኑ ለጥቂት ግለሰቦች ሰፊ የሙስና በር ከመክፈቱና ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ከመንግሥት ጋር ከማቃቃሩ በስተቀር የሚያስገኘው የረባ ጥቅም ይኖራል ብለን አናምንም፡፡
 4. እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለአገራችን ሰላም፣ ልማት እና ዕድገት ፀር የሆነ ማንኛውንም አሉታዊ እንቅስቃሴ አጥብቀን እንደምንቃወምና በፅናት እንደምንታገለው ለማንም መንገር አያስፈልገንም፡፡ በአገራችን እውነተኛ የሃይማኖት መቻቻል እንዲሰፍንም አጥብቀን እንሻለን፡፡ የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታዊ በዓላታቸውንና የእምነት ሥርዓታቸውን ሰላም በሰፈነበት መንፈሳዊ ድባብ ቢያከብሩና ቢተገብሩ ደስ ይለናል እንጂ ፈጽሞ አያስከፋንም፡፡ የማንንም ክፉ አንመኝም፡፡ ለእኛ የምንወደውን ለሌሎችም እንወድዳለን፡፡ ለእኛ የምንመኘውን የሃይማኖት፣ የእምነትና የአስተሳሰብ ብሎም የተቋም ነፃነት ለሌሎችም እንመኛለን፡፡ ነገር ግን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ‹‹አልሃምዱሊላሂ ታቦታችን በሰላም ገባ›› ይሉት አባባል የሃይማኖት መቻቻል መገለጫ ነው ብለን አናምንም፡፡ ክርስቲያን ወገኖቻችን ‹‹እግዚሃር ይመስገን የዒድ ሶላታችንን በድምቀት ሰገድን›› እንዲሉም አንጠብቅም፡፡ እንዲህ ማለት ወይም አለማለት ከሃይማኖት መቻቻል ጋር ምንም ዝምድና የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት መቻቻል መኖሩም ሆነ አለመኖሩ ይህን በማለት ወይ ባለማለት አይገለፅም፡፡ እባካችሁ ግልብ ፕሮፖጋንዳ ከመንዛት ይልቅ በዘላቂነት ለአገር የሚበጀውን ነገር በጥልቀት አስቡ፡፡
 5. እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፣ በየትኛውም የሃይማኖት ወይም የእምነት ማኅበረሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት የሚንፀባረቅን የጽንፈኝነት አዝማሚያ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ በእኛ እምነት የሃይማኖት ጽንፈኝነት የሚመነጨው ከሃይማኖት እውቀት ማነስ፣ ወይም በእውቀት ላይ ካልተመሠረተ ስሜታዊ ቀናዒነት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መድኃኒቱ የአገሪቱ ዜጎች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 27 ድንጋጌዎችን ፋይዳ በጥልቀት ተገንዝበው በአግባቡ እንዲጠቀሙባቸው ማበረታታት ነው ብለን በጽኑ እናምናለን፡፡ … በአንጻሩ ‹አሕባሽ› የተባለ ሌላ ራሱን የቻለ በሽታ ከሊባኖስ አስመጥቶ አንድ አገር ሙሉ ህዝብ ላይ ለመጫን ጥርስን ነክሶ መውተርተር ያልነበሩ ጽንፈኞችን ከመፍጠር በስተቀር ለአገሪቱ ምንም የሚያስገኘው ትርፍ የለም፤ አይኖርምም፡፡ ዜጎች ያለማንም አስገዳጅነት በነፃ ምርጫቸው የ‹አህባሽ›ን አስተሳሰብ ተቀብለው ቢያራምዱ ይህ ህገ መንግሥታዊ መብታቸው በመሆኑ ቅሬታ የለንም፡፡ ነገር ግን አንድዬ የጋራ ተቋማችን የምንለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የአህባሽ አስተምህሮ ማስፋፊያ ተቋም መሆኑን አሜን ብለን እንድንቀበል የሚያሳየን ምንም ዓይነት ሕግም ሆነ አመክንዮ (Logic) የለም፡፡
 6. የሁሉም ሃይማኖቶች ተከታይ የሆኑ የአገራችን ዜጎች ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 27 በተረጋገጡ የሃይማኖት፣ የእምነት እና የአስተሳሰብ ነጻነቶቻቸው በመጠቀም እምነታቸውን በዕውቀት ላይ ለመመሥረት ያደረጉት ጥረት ግልብ ቀናዒነትን በማስወገድ ረገድ መልካም ውጤት እንዳስመዘገበ በቅጡ ያስተዋላችሁ አይመስልም፡፡ ክርስትና እና ኢስላም ሁለቱም አብራሃማዊ እምነቶች እንደመሆናቸው በርካታ ስነ መለኮታዊ እሴቶችን ይጋራሉ፡፡ የዚያኑ ያህልም ጥቂት መሠረታዊ አስተምህሯዊ ተቃርኖዎች አሏቸው፡፡ በኢትዮጵያ ከ1400 ዓመታት በላይ አብረው የኖሩት የእነዚህ ታላላቅ ሃይማኖት ተከታዮች በጋራ እሴቶቻቸውና በአስተምህሯዊ ተቃርኖዎቻቸው ዙርያ ቅዱሳን መጻሕፍቱን እያጣቀሱ በአደባባይ ለመወያየትና ለመከራከር የበቁት ካለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ ይህ በእኛ አመለካከት የማኅበረሰባዊ እድገት ምልክት ነው፡፡ … ምንም እንኳ ጅማሮው በታየባቸው በ1980ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ስሜታዊ ነውጦች (emotional frustrations) የነበሩ ቢሆንም፣ እንዲህ ባለ የሠለጠነ አካሄድ እውነተኛ የመቻቻል መንፈስ እንደሚዳብር ፈፅሞ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ እምነትን የሚመለከቱ የተቃርኖ ሐሳቦችን ማድመጥና እውቀትን መሠረት አድርጎ መተቸት የቻለ ማኅበረሰብ በተዘዋዋሪ ዴሞክራሲያዊ ባህልን እያዳበረ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ … ለስሜት በቀረበው የእምነት ጉዳይ ላይ ተቃራኒ ሐሳብን ለመሸከም ጫንቃው የፈረጠመ ማኅበረሰብ፣ በዓለማዊው ጉዳይ ዙርያ የተለያዩ ሐሳቦችን በሰከነ አዕምሮ ለመመዘን ከፍተኛ ብቃት ይኖረዋል፡፡ ስለዚህም ስነ ምግባርን በተከተለ መልኩ የተነጻጻሪ ሃይማኖቶች ስነ መለኮታዊ እና አስተምህሮ ተኮር ውይይቶች በመጽሐፍ መልክም ይሁን በሲዲ፣ አልያም ሕዝብ በተሰበሰበበት መድረክ ላይ መካሄዳቸው ሊበረታታ እንጂ ሊወገዝ አይገባም፡፡ … ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት እንዲህ ያለውን የሠለጠነ አካሄድ እየለመደ ብዙ እርምጃዎች ወደፊት የተራመደውን ኅብረተሰባችንን ወደ ኋላ ለመጎተት መራኮት፣ ህዝብን ‹‹አክራሪ››፣ ‹‹ጽንፈኛ›› ወዘተ. በሚሉ ታፔላዎች ማሸማቀቅ 90 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባትን ታላቅ አገር ከሚመራ መንግሥት የሚጠበቀውን ብስለት አያሳይም፡፡…
 7. አልፎ አልፎ ከስነ መለኮታዊ ውይይትና ትምህርት አቀራረብ ስነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ የሚቀርቡ፣ ዘለፋ የታከለባቸው፣ ትንታኔ፣ አስተያየት፣ ሐሳብና መረጃን በአፀፋ ትንታኔ፣ አስተያየት፣ ሐሳብና መረጃ አስደግፎ ከመሞገት ይልቅ፣ በግለሰቦች አልያም ቡድኖች ላይ የተነጣጠሩ መረን ለቀቅ ውግዘቶችን ለህዝብ የሚያቀርቡ ሰባኪያን አይጠፉ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያሉ አቀራረቦች ሃይማኖትን ከኳስ ጨዋታ ለይቶ ካለማየት፣ በጥቅሉም ከግልብ ‹‹የማሊያ ፍቅር›› የሚመነጩ ይመስሉናል፡፡ ዒላማ የሚያደርጉትም የ‹ቲፎዞ›ን ስሜት በማነቃቃት፣ የባላንጣ ቡድን ተጨዋቾችና ደጋፊዎችን በማብሸቅ ላይ ነው፡፡ በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ የማይጠፉትን እነዚህን ወገኖች በማስተማር ወደ ትክክለኛና የሠለጠነ መስመር ማምጣት የመንግሥት፣ የሁሉም ሃይማኖቶች በሳልና ተሰሚ ምሁራን እንዲሁም የመላው ማኅበረሰብ የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ …
 8. ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 27 በሠፈሩ ድንጋጌዎች አጠቃቀም ዙርያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ያልሠራቸው በርካታ ከግንዛቤ መዳበር ጋር የተያያዙ ሥራዎች አሉ፡፡ በተቃራኒው ኅብረተሰቡ ባለፉት 21 ዓመታት በራሱ ጥረት እየተንገታገተ በሃይማኖቱ ዙርያ ከዛሬ 21 ዓመታት በፊት ያልነበረውን ጥልቅ እና ሠፊ ግንዛቤ አዳብሯል፡፡ የተለያዩ እምነቶች ተከታይ የሆነው ህዝብም ከ21 ዓመታት በፊት ከነበረው በብዙ እጥፍ በበለጠ እርስ በእርስ የመተዋወቅ ዕድል አግኝቷል፡፡ ሙስሊሙ ስለ ክርስትና፣ ክርስቲያኑም ስለ ኢስላም ብዙ፣ እጅግ ብዙ አውቀዋል፡፡ ይህ መተዋወቅ የመቀራረብ፣ የመከባበር ብሎም በሰላም እና በፍቅር አብሮ የመኖር ዋነኛ መሠረት መሆኑ በጥብቅ የሚታመነውን ያህል፣ አንዳንድ በማሊያ ፍቅር የታወሩ ወገኖችን ሊያስከፋቸው እንደሚችል የሚካድ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰአት መንግሥት በእኒህ በማሊያ ፍቅር የታወሩ ወገኖችና ከውጭም ለኢስላም ቀና አመለካከት በሌላቸው ኃይሎች ተገፋፍቶ ይመስላል፣ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የህገ መንግሥቱ አንቀፅ 27 ባጎናፀፈው መብቱ ተጠቅሞ ሃይማኖቱን በቅጡ ለማወቅና ለመረዳት፣ ባወቀውም ልክ ለመተግበር የሚያደርገውን ጥረት በአሉታዊ መልኩ ለመተርጎም ሲተጋ ይታያል፡፡ በቀደሙት ሥርዓቶች የሃይማኖቱን መማሪያ መጻህፍት እንኳ ለማግኘት ሲቸገር የኖረው የኢትዮጵያ ሙስሊም፣ ዛሬ የህገ መንግሥቱ አንቀፅ 27 ባጎናፀፈው መብቱ ተጠቅሞ ባደረገው የግልና የወል ጥረት የሃይማኖት እውቀቱን አዳብሮ ያወቀውን መተግበር ሲጀምር ‹‹አክራሪ›› እና ‹‹ጽንፈኛ›› የሚል ታፔላ እየተለጠፈበት ይገኛል፡፡ በማኅበረሰብ ደረጃ አቅሙን አስተባብሮም ሆነ ከውጭ የሙስሊም አገራት ለምኖ ነባር ደሳሳ የጭቃ ስሪት መስጊዶቹን በጡብ ሲያድስም ሆነ በመኖሪያው አቅራቢያ ያልነበረውን አዲስ መስጊድ ሲገነባ፣ ይህ የህገ መንግሥቱ ፍሬ እንደመሆኑ በአወንታዊነት ሊታይ፣ ሊሞገስና ሊወደስ ሲገባ፣ በተቃራኒው ልክ በአጼያዊው ሥርዓት ዘመን ይታሰብ እንደነበረው የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ኢትዮጵያዊነት በመገዳደር ሙስሊሙ ‹‹የውጭ ኃይሎች ቅጥረኛ›› ወዘተ. እየተባለ ይብጠለጠላል፡፡ በእኛ እምነት ይህ ግልፅ የሆነ የኋልዮሽ ጉዞ ነው፡፡ …

ጥራትና ልዕልና የተገባው ኃያሉ ፈጣሪያችን አላህ ቅኑን መንገድ ያመላክተን፤ ኢትዮጵያንና ህዝቧንም ከክፉ ይጠብቅ፡፡ አሚን፡፡

* * * * * *

About Us

WHAT WE DO

 • Da'awa
 • Unity
 • Advocancy
 • Development

Departments

 • Da'awa
 • Media
 • Finance
 • Convention
 • Community Relations
 • Badr Sisters
 • Youth
 • Ethiopian Relations
 • International Relations
 • Marriage