Deprecated: Non-static method JSite::getMenu() should not be called statically, assuming $this from incompatible context in /home/badrtube/public_html/badrethiopia.org/oldsite/templates/yoo_revista/warp/systems/joomla/layouts/com_content/article/default.php on line 13

Deprecated: Non-static method JApplication::getMenu() should not be called statically, assuming $this from incompatible context in /home/badrtube/public_html/badrethiopia.org/oldsite/includes/application.php on line 536

ዘመነ-ኢህአዴግ እና የሙስሊሞች ወቅታዊ ጥያቄ (ክፍል 1)

Posted in Amharic Articles

Oct 12, 2012 | ነስሩዲን ዑስማን | Article in Pdf

የዚህ ጽሑፌ መነሻ፣ ‹‹በኢህአዴግ ዘመን ምንም ከደርግ የተለየ መብት አላገኘንም፤ ተቀነሰብን እንጂ›› በሚል ርዕስ ተጽፎ በተለያዩ የፌስቡክ ግሩፖች ላይ ያነበብሁት ጽሑፍ ነው፡፡ ጽሑፉ በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ መንግሥት በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ እየፈፀመ ባለው ህገ መንግሥቱን የሚጻረር ተግባር በመብሸቅ የተጻፈ ይመስላል፡፡ ገዢው ፓርቲ በአሁኑ ወቅት እየሠራ ያለው ሥራ ህገ ውጥ ከመሆኑም በላይ፣ በተለይ አዘውትሮ ኢቲቪን ለሚያይ ሙስሊም በእርግጥም በጣም አብሻቂ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡

...ነገር ግን ከላይ ርዕሱ የተጠቀሰውን ጽሑፍ ከብሽቀት በራቀ ስሜት አንብቤው በይዘቱ ፈጽሞ ልስማማ አልቻልኩም፡፡ ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የአገሪቱን ህገ መንግሥት መሠረት አድርገው ያነሱት የመብት ጥያቄ፣ የተጠቀሰው ጽሑፍ በሚያንፀባርቃቸው (በእኔ እምነት የተሳሳቱ) አስተሳሰቦች ላይ የተመሠረተ ተደርጎ እንዳይወሰድ ስጋት ስለገባኝ ነው፡፡ በእኔ እምነት፣ አሥር ወራትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መብትን የማስከበር ትግል፣ ‹‹በኢህአዴግ ዘመን ምንም ከደርግ የተለየ መብት አላገኘንም፤ ተቀነሰብን እንጂ›› በሚል ከሐቅ የራቀ የጋራ አስተሳሰብና እምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡

ጥያቄዎቻችን ፈር እንዳይስቱ፣ በሐቅ ላይ ይመሥረቱ

ጽሑፉ በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ የዘውድ አገዛዝ እና በደርግ ሥርዓት የነበረውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሁኔታ በማውሳት በተለይ የደርግ ዘመንን ከዘመነ ኢህአዴግ ጋር ለማነፃፀር ይሞክራል፡፡ ጽሑፉ በዋነኛነት የደርግ ሥርዓትን ከኢህአዴግ ዘመን ጋር የሚያነፃፅር እንደመሆኑ፣ የእኔም ሒስ በዚህ የደርግ እና ኢሕአዴግ ንፅፅሩ ላይ ያተኩራል፡፡ ፀሐፊው የአፄውን ዘመን በርካታ አሉታዊ ገፅታዎች ጠቃቅሶ ወደ ደርግ ዘመን ሲሻገር እንዲህ ይላል፡

‹‹በመቀጠልም በትረ ስልጣኑን የጨበጠው የደርግ መንግስት ሙስሊሙ ያደረገውን መራራ ትግል በመገንዘብ እና አሱንም ከሙስሊሙ በኩል የንጉሱ አይነት ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥመው በመስጋት፤ የሃይማኖትን እኩልነት ያወጀ ሲሆን፣ ለመጀመርያ ጊዜም ለሙስሊሙ የዜግነት መብት፤ የመማር እና እንዲሁም የራሱን መጅሊስ የሚያቋቁምበት መብት አጎናፅፎታል፡፡››

ደርግ ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አጎናፀፋቸው ተብለው የተጠቀሱት ትሩፋቶች ማናፀሪያቸው የአፄው ዘውዳዊ ሥርዓት ሲሆን፣ ሙስሊሞች በአፄው ዘመን ያልነበሯቸውን የ‹‹እኩልነት፣ የዜግነት፣ የመማር፣ መጅሊስ የማቋቋም…›› መብቶች ማግኘታቸው ተጠቅሷል፡፡ ፀሐፊው ባይጠቅሳቸውም በዘመነ ደርግ ሦስት የሙስሊም ሃይማኖታዊ በዓላት ብሔራዊ በዓል እንዲሆኑ መታወጁንም አስታውሰን እንቀጥል፡፡

ደርግ ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አጎናፀፈ ተብለው የተጠቀሱት እኒህ መብቶች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንደመሆናቸው፣ የደርግ ሥርዓት ችሮታ ማሳያ ተደርገው ከሚጠቀሱ ይልቅ የአፄያዊው ሥርዓት ቅጥ ያጣ አድሏዊነት እና የመሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ረገጣ መገለጫ ተደርገው ቢጠቀሱ ይበልጥ ተገቢ ነበር፡፡ በደርግ ሥርዓት የሃይማኖቶች እኩልነት ተከብሯል ከተባለ የዚህ ዐብይ መገለጫ በረዥሙ አፄያዊ ሥርዓት ሰፍኖ የቆየው የአንድ ሃይማኖት የበላይነት (ብሔራዊ ሃይማኖትነት) ማብቃቱ ነው፡፡ ከሃይማኖት አኳያ በደርግ ሥርዓት የመጣው መሠረታዊ ለውጥ ይህ ሲኾን፣ በተለይ እስልምናን እና ሙስሊሞችን ዒላማ ያደረጉ አያሌ ተቀፅላ መድሎዎችን ያስቀረ በመሆኑ ከህዝባዊው አብዮት ፍሬዎች ውስጥ በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ ነገር ግን ይህ መሠረታዊ ለውጥ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል እንጂ በሙስሊሞች ትግል ብቻ የመጣ አይደለም፡፡ እንደ ባሌ ሙስሊም ገበሬዎች ሁሉ፣ የጎጃም ክርስቲያን ገበሬዎችም በዘውዳዊው ሥርዓት ላይ አምፀዋል፡፡ እርግጥ ነው በዘውዳዊው ሥርዓት ውድቀት ዋዜማ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ‹‹የሃይማኖት እኩልነት ይከበር!›› የሚል መፈክር አንግበው ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ …

ሕዝባዊው አብዮት የፈጠረለትን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ወደ ሥልጣን የወጣው ደርግ መንግሥታዊ ሃይማኖትን ያስቀረው ፀሐፊው እንደጠቀሱት፣ ‹‹ሙስሊሙ ያደረገውን መራራ ትግል በመገንዘብ እና እሱንም ከሙስሊሙ በኩል የንጉሡ ዓይነት ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥመው በመስጋት›› አይመስለኝም፡፡ የአጼውን ሥርዓት ውድቀት ያፋጠነው የተማሪዎች እንቅስቃሴ በእጅጉ ግራ ዘመም (ማርክሳዊ ሌኒናዊ) ከመሆኑ በመነጨ ይመስላል፣ ደርግ ሥልጣን ሲጨብጥ ሶሻሊዝምን አገሪቱ የምትከተለው ርዕዮተ ዓለም አድርጎ አውጇል፡፡ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ሃይማኖትን ‹‹የደሃው ኅብረተሰብ ማደንዘዣ›› አድርጎ ስለሚያይ፣ የመንግሥታዊ ሃይማኖት ማብቃት ‹‹የሙስሊሞች መራራ ትግል ውጤት ነው›› ከማለት ይልቅ፣ ከህዝባዊው አብዮት ባህሪ በመነጨ ደርግ የተከተለው ርዕዮተ ዓለም ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የትምህርት ዕድልም ከዚህ ባልተለየ መነፅር የሚታይ ነው፡፡ እንደ መብት ይጠቀስ ከተባለ ደርግ ሙስሊሙን አማክሎ የወሰደው አዎንታዊ እርምጃ ቢኖር እስላማዊ በዓላትን ብሔራዊ በዓላት ማድረጉ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ያደረገው በጽሑፉ ላይ እንደተጠቀሰው ‹‹ከሙስሊሙ በኩል የንጉሡ ዓይነት ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥመው በመስጋት›› ነው ማለት ብዙም የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ወታደራዊውን ደርግ ሊያሰጋ የሚችል የተደራጀ ኃይል አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ የአዎንታዊ እርምጃዎቹን ፖለቲካዊ መነሾ ‹‹የህዝበ ሙስሊሙን ድጋፍ ለማግኘት›› የታለመ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

የሃይማኖት ነጻነት በዘመነ-ኢህአዴግ

ከሃይማኖት ነፃነት አኳያ ከ1983 ወዲህ ያለውን የኢህአዴግ ዘመን ከዘመነ ደርግ ጋር አነጻጽሮ ከላይ በተጠቀሱት በዘመነ ደርግ የተከሰቱ ለውጦች መነሻነት ‹‹ዘመነ ደርግ ከዘመነ ኢህአዴግ ይሻል ነበር›› ማለት ሚዛናዊም፣ ፍትኃዊም፣ ትክክለኛም አያሰኝም፡፡ እንዲህ ያለ ድምዳሜ በአንድ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም መንፀባረቁ ለእኔ ያስተላለፈልኝ መልዕክት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢህአዴግ በሃይማኖት ዙርያ፣ በተለይም በኢስላምና በሙስሊሞች ጉዳይ ላይ እያራመደ ያለው አቋም በሙስሊሙ ዘንድ ምን ያህል የከፋ ጥላቻ እያተረፈለት እንደሆነ ነው፡፡

በእኔ እምነት ከ21 ዓመታት የዘለለውን የኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ እየታዩ ባሉ የገዢው ፓርቲ ግልፅ የአቋም ለውጦች ላይ ተመሥርቶ መዳኘት ትክክል አይመስለኝም፡፡ ባይሆን ከስሜታዊነት በራቀና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተለወጡ ያሉ አዝማሚያዎችን በተገቢው ዐውድ አስቀምጦ ነገሮችን በጥሞና ለመመዘን ዘመነ ኢህአዴግን ቅድመ ሚሌኒየም እና ድኅረ ሚሌኒየም በሚል ከፋፍሎ ማየትን ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡

ዘመነ-ኢሕአዴግ - ቅድመ-ሚሌኒየም

ከግንቦት ወር 1983 እስከ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም (2000 ዓ.ል) ያለውን የ17 ዓመታት ጊዜ ከሃይማኖት ነጻነት አከባበር አኳያ ለመመዘን የሚነሳ ሰው በተቀዳሚነት ከሐምሌ 1983 እስከ ሕዳር 1987 አገሪቱ በተዳደረችበት የሽግግር ወቅት ቻርተር፣ እና ከሕዳር ወር 1987 አንስቶ እስካሁን እየተዳደረችበት ባለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ የሠፈሩ ድንጋጌዎችን ማውሳቱ ግድ ነው፡፡ እነዚህ ገዢ ሰነዶች በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የመንግሥትን እና የሃይማኖትን መለያየት ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት፣ የእምነት እና የአስተሳሰብ ነፃነትንም በግልፅ ደንግገዋል፡፡ እነዚህ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች አንዳችም ያስገኙት ነገር የለም ብሎ መካድ፣ ቁልጭ ያለ ክህደት አልያም አላዋቂነት ነው፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 27፣ ንዑስ አንቀጽ 1፣ ‹‹ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነጻነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል›› ተብሎ ተደንግጓል፡፡ ባለፉት 21 ዓመታት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአገሪቱ ውስጥ ካሉት የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች እኩል የዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ሙሉ ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ የዚህ ዋነኛ መገለጫ ሃይማኖታዊ ትምህርትን በፈለጉት ቋንቋ በመጻሕፍት፣ በመጽሔቶች እና በጋዜጦች፣ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ደግሞ በኤሌክትሮኒክ ዘዴዎችም ጭምር አትሞ ለማሠራጨት የቻሉበት ተጨባጭ ዕውነታ መኖሩ ነው፡፡የሃይማኖታዊ ትምህርት እና/ወይም ዕውቀት መጻሕፍትን አይደለም በአገርኛ ቋንቋ፣ በአረብኛ ቋንቋም እንኳ እንደልቡ እንዳያገኝ ከፍተኛ ገደብ ተጥሎበት ለኖረው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ይህ መብት በዘመነ ኢሕአዴግ የተገኘ መሆኑን መካድ ይቻላልን?! … [ጎበዝ! የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች አተገባበር እንከን አልባ ነበር አላልኩም፡፡] …

የአፄ ኃይለሥላሤ መንግሥት በዚህ ረገድ ከዘመነ ኢህአዴግ ጋር ለውድድር ይቅርና ለንፅፅር እንኳ የሚበቃ አይደለም፡፡ ለግንዛቤ እንዲረዳ ያህል ግን በ1986 መጀመርያ አካባቢ በዓይኔ ካየሁት አንድ የቀ.ኃ.ሥ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የህዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር የወጣ ሰነድ ላይ ያነበብኩትን ላቋድሳችሁ፡፡ በ1960ዎቹ መጀመርያ አካባቢ የእስላማዊ አገሮች ማኅበር (Organization of Islamic Countries) የተባለው ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባውን አካሂዶ በማጠቃለያው ላይ በዓለም ዙርያ የእስልምና ትምህርትን ለማስፋፋት 10 ሚሊዮን ዶላር/ብር በጀት ያፀድቃል፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የህዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር ይህንን ውሳኔ ከዜና ማሰራጫዎች እንደሰማ፣ በመላው አገሪቱ ለሚገኙ የጠረፍ አገር ገዢዎች በጥብቅ ሚስጥርነት የተፈረጀ አንድ ጥብቅ ትዕዛዝ ያስተላልፋል፡፡ ይህም ትዕዛዝ ‹‹የእስላማዊ አገሮች ማኅበር እስልምናን ለማስፋፋት 10 ሚሊዮን ዶላር በጀት ስላፀደቀ፣ የእስልምና ማስተማሪያ መጻሕፍት በጠረፍ በኩል ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከፍተኛ ጥበቃና ቁጥጥር እንዲደረግ በጥብቅ እናሳስባለን›› የሚል ነበር፡፡ ቀደምት አባቶቻችን ዲናቸውን ጠብቀው ለመቆየትና ለትውልድም ለማስተላለፍ ታላቅ ተጋድሎ በማድረጋቸው እንጂ፣ በተለይ በዘውዳዊው ሥርዓት በሙስሊሞች ላይ እንደተሠራው ግፍ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ስንቶቻችን ‹‹አያቴ እኮ ሙስሊም ነበሩ፣ በንጉሡ ዘመን ተጠምቀው ነው እንጂ…›› ባልን ነበር፡፡

ለ17 ዓመታት በዘለቀው የደርግ ዘመንም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሃይማኖት ነጻነት ረገድ፣ ይልቁንም ሃይማኖትን ከማስፋፋት አኳያ ያገኙትና ከዘመነ ኢህአዴግ ጋር ተነጻጽሮ ‹‹የተሻለ›› የሚሰኝ ነገር አለ ለማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹እኩልነት ተጎናጽፈዋል›› የሚለውን ብናይ፣ ደርግ መንግሥታዊ ሃይማኖትን ከማስቀረቱ በቀር ሃይማኖታቸውን በነጻነት ያስፋፉ ዘንድ ለሙስሊሞች ያጎናፀፈው የተለየ መብት የለም፡፡ በዘመነ ደርግ በአማርኛ ቋንቋ ተፅፈው ለህትመት የበቁ የእስልምና መጻሕፍት ቢቆጠሩ ግማሽ ደርዘን እንኳ የሚሞሉ አይመስለኝም፡፡ ግዴለም አንድ ደርዘን ይሞላሉ እንበል፡፡ ታዲያ ይህን (የደርግ) ዘመን እንደምን አድርገን ነው በአገራችን ምሁራን የተዘጋጁና ከተለያዩ የውጭ ቋንቋዎች የተተረጎሙ የኢስላማዊ ትምህርት መጻሕፍት እንደ ልብ ታትመው ለህዝበ ሙስሊሙ ሲቀርቡ በዓይናችን ከምናይበት ከዚህ (የኢህአዴግ) ዘመን ጋር የምናወዳድረው?! በሌሎች ማነጻጸርያዎች አኳያ ብናይም ዕውነታው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ እስከ 1983 ድረስ አዲስ አበባ ውስጥ ምን ያህል መስጂዶች ነበሩ? ዛሬስ ምን ያህል አሉ? እስከ 1983 ምን ያህል እስላማዊ አሳታሚ ድርጅቶች ነበሩ? ዛሬስ ምን ያህል አሉ? እስከ 1983 ምን ያህል እስላማዊ መያዶች ነበሩ? ዛሬስ ምን ያህል አሉ? የማወራው ቅድመ ሚሌኒየም ዘመነ ኢህአዴግን መሆኑ እንዳይረሳ፡፡

በዘመነ-ኢህአዴግ የኢትዮጵያዊው ሙስሊም ሁኔታ - በፕሮቴስታንት ዕይታ

ከጥቂት ዓመታት በፊት The Growth and Influence of Islam In Ethiopia from 1989 to 2000 በሚል ርዕስ ተጽፎ እ.አ.አ ሜይ 27፣ 2002 ይፋ የተደረገ አንድ በፕሮቴስታንቶች የተደረገ ጥናት ነበር፡፡ ይህ ጥናት የሚሸፍነው ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ ሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ አንስቶ እስከ ፈረንጆቹ ሚሌኒየም፣ ማለትም በኢትዮጵያ አቆጣጠር እስከ 1992 ያለውን ጊዜ ነው፡፡

ጽሑፉ በመግቢያው የመጀመርያ አንቀፅ ላይ እንዲህ ይላል፡

Islam is the fastest growing religion in Ethiopia as well as in the globe. Since 1989 Islam has shown rapid growth in spiritual, economic, political and other areas of activity. This dynamic change has resulted in a negative impact on the lives of Christians and the ministry of the church. Witnessing to Muslims became the toughest ministry in the church.

ትርጉም፡

‹‹ኢስላም በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የሚገኝ ሃይማኖት ነው፡፡ ከ1981 ወዲህ ኢስላም በመንፈሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና በሌሎችም መስኮች ፈጣን እድገት አሳይቷል፡፡ ይህ ፈጣን ለውጥ በክርስቲያኖች ህይወት እና በቤተ ክርስቲያን ወንጌልን የማዳረስ ተልዕኮ ላይ አሉታዊ ውጤት አስከትሏል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ወንጌላዊ ሥራ ውስጥ ለሙስሊሞች መመስከር [ሙስሊሞችን ማክፈር ማለቱ ነው] እጅግ አስቸጋሪው ሥራ ሆኗል፡፡››

ጥናታዊ ጽሑፉ ከመግቢያው ለጥቆ ወደ ዋና ርዕሶቹ ሲገባ The Growth of Islam in Ethiopia (‹‹የኢስላም ዕድገት በኢትዮጵያ››) በሚል ዐብይ ርዕስ ስር አራት ንዑሳን ርዕሶችን ይዳስሳል፡፡ እነርሱም (1) Spiritual Growth (መንፈሳዊ ዕድገት); (2) Growth in Publication, Translation, and Distribution of Literature (የጽሑፎች ህትመት፣ ትርጉምና ሥርጭት ዕድገት), (3) Building of Mosques and Qur’an Schools (የመስጂዶች እና የመድረሳዎች ግንባታ), እና (4) Numerical Growth both in Ethiopia and the Horn of Africa (በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ የ[ሙስሊሞች] የቁጥር ዕድገት) የሚሉ ናቸው፡፡

ፀሐፊው በእነዚህ ርዕሶች ስር ለእስልምና መስፋፋት መንስዔ አድርጎ ያቀረበው ትንታኔ ጥቂት የማይባሉ ግድፈቶች፣ የተሳሳቱ ዕይታዎችና ድምዳሜዎች ያሉበት ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ግን በዘመነ ኢህአዴግ የሙስሊሞች ሃይማኖታዊ እውቀትና ንቃተ ኅሊና በከፍተኛ ደረጃ እያደገ በመሄዱ ወንጌልን ለሙስሊሞች መስበክ አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ይናገራል፡፡ … ፀሐፊው ዘመነ ኢህአዴግ ላይ ቆሞ ከደርግ ውድቀት በፊት የነበረውን የሙስሊሞች ሁኔታ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡

There has been a tremendous growth in the spiritual lives of Ethiopian Muslims in the past ten years. Before 1989 the majority of Muslims were just followers of Islam. They did not have a deep knowledge of the Qur’an (Koran), Hadis (authoritative traditions), and Islamic Doctrines. Besides this there were no strong, modern Sheikhs (Muslim religious teachers) in most parts of the country, especially in the rural areas. Many Muslims were worshipping other deities than Allah. Offering sacrifices to lesser spirits or at Muslim saints’ tombs was a common practice. Of course there were some Muslim people who were strong and faithful to their religion. However, after the fall of the Dergue (government), a great paradigm shift came out in Islam in Ethiopia.

ትርጉም፡

‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መንፈሳዊ ህይወት ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ዕድገት ታይቷል፡፡ ከ1981 በፊት አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች በቃ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ብቻ ነበሩ፡፡ የቁርአን፣ የሐዲስ እና የኢስላማዊ አስተምህሮዎች ጠለቅ ያለ እውቀት አልነበራቸውም፡፡ በተጨማሪም፣ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች፣ በተለይ በገጠር አካባቢዎች ጠንካራ እና ዘመናዊ ሸይኾች አልነበሩም፡፡ ብዙ ሙስሊሞች ከአላህ ይልቅ ሌሎች አማልክቶችን (ጣዖታትን) ያመልኩ ነበር፡፡ ለመናፍስት አልያም በሙስሊም ቅዱሳን መቃብር ላይ መስዋዕት ማቅረብ የተለመደ ተግባር ነበር፡፡ እርግጥ የተወሰኑ ጠንካራና የሃይማኖታቸውን ህግጋት ጠብቀው የሚኖሩ ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ ግን በኢትዮጵያ እስልምና ላይ ታላቅ መሠረታዊ ለውጥ ተከሰተ፡፡›› በዚህ ፀሐፊ እምነት ከሃይማኖት አኳያ በዘመነ ኢህአዴግ የተከሰተው ታላቅ ለውጥ የመነጨው የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነጻነትን ካረጋገጠው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት (አንቀፅ 27) ነው፡፡ ይህ ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ለሙስሊሞች ብቻ የወጣ አይደለም፡፡ ኦርቶዶክሱም፣ ፕሮቴስታንቱም፣ የይሆዋ ምስክሩም፣ ካቶሊኩም፣ አድቬንቲስቱም የድንጋጌው ተጠቃሚ ናቸው፡፡ … የመጫወቻ ሜዳው ሁሉንም በእኩልነት እስካስተናገደ ድረስ፣ የትኛው ሃይማኖት ህገ መንግሥታዊው ድንጋጌ ባረጋገጠለት መብቱ ይበልጥ ተጠቀመ?›› የሚል ጥያቄ ሊነሳ አይገባውም፡፡ የሁሉም ሃይማኖትና እምነት ተከታዮች ይህን የህገ መንግሥት ድንጋጌ ለጋራ መንፈሳዊ ብልፅግናቸው እና ለዴሞክራሲያዊ ባህል መዳበር በሚበጅ መልኩ በኃላፊነት ስሜት ሊጠቀሙበት፣ ሊያከብሩት፣ ሊንከባከቡት እና ሊያስከብሩትም ይገባል፡፡ …

ይህ ህገ መንግሥት በአያሌ የኢትዮጵያ ደሃ ገበሬዎች የህይወት መስዋዕትነት ነው የተገኘው፡፡ መንግሥት ይህን በህዝቦች መስዋዕትነት የተገኘ ሕገ መንግሥት የማስከበር ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ የማክበር ግዴታም አለበት፡፡ ራሱ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ሲጥስ ደግሞ፣ ሕገ መንግሥቱ ባረጋገጣቸው መብቶች ተጠቃሚ የሆነው ህዝብ በዝምታ ሊያልፈው አይገባም፡፡ ላለፉት አሥር ወራት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እያደረጉ ያሉት ይህንኑ ነው በዜጎች መስዋዕትነት የተገኘ ህገ መንግሥታዊ መብታቸውን ለማስከበር ሰላማዊ ትግል ይዘዋል፡፡ ይህ የሙስሊሞች ትግል ኢህአዴግ በድኅረ ሚሌኒየም በተለይ በሃይማኖት ረገድ መከተል ከጀመረው ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር የአቅጣጫ ለውጥ የመነጨ ነው፡፡

ይህ የአቅጣጫ ለውጥ እንደምን ሊከሰት ቻለ? የአቅጣጫ ለውጡ መገለጫዎች ምን ምን ናቸው? በዚህ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር የአቅጣጫ ለውጥ ማን ይጠቀማል? ማንስ ይጎዳል? ይህ የአቅጣጫ ለውጥ ለአገራችን ሰላም፣ ልማት እና የዴሞክራሲ ባህል መጎልበት ምን ፋይዳ አለው? ፖለቲካዊ አንድምታውስ ምንድን ነው? ገዢው ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን እንዳሻው ሲጥስ የሚጎዱት ሙስሊሞች ብቻ ናቸውን? … የሚሉና ተዛማጅ ጥያቄዎችን በማንሳት ‹‹ድኅረ ሚሌኒየም የኢሕአዴግ የኋልዮሽ ጉዞ››ን የሚቃኘውን የዚህ ጽሑፍ ቀጣይ ክፍል በቅርቡ አቀርባለሁ፡፡ ኢንሻአላህ!

* * * * * * *

About Us

WHAT WE DO

 • Da'awa
 • Unity
 • Advocancy
 • Development

Departments

 • Da'awa
 • Media
 • Finance
 • Convention
 • Community Relations
 • Badr Sisters
 • Youth
 • Ethiopian Relations
 • International Relations
 • Marriage