logo

 Image result for in the name of allah in arabic

   (በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ)

   ኢድ ሙባረክ!

በተቀደሰዉ የረመዳን ወር ሙስሊሙ ማሕበረሰብ ከጾሙ ባሻገር በግል እና በጋራ ቁርዓን በመቅራት ፣ በስግደትና በዱኣ በየኮሚኒቲውና በየመስጂዱ በመሰባሰብ የኢፍጣር ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት በዱአና በዒባዳ ያሳልፋል።

ሙስሊሙ ህብረተሰብ የረመዳንን ወር በጉጉት እንደሚጠብቀዉ ሁሉ የአማኞች ሁሉ መደሰቻ የሆነው ለዒድ ኣል ፈጥር በአልም በወሩ መጨረሻ ልዩ እይታ አለዉ።

በእስር ለሚገኙ ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ያለንን ክብር እና አጋርነት ስንገልጽ ሁሌም በደስታ ነዉ። በድር ኢትዮጵያ ለ1436ኛው የኢድ ኣል ፈጥር በዓል አላህ(ሱወ) እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እያለ መጭው ጊዜ ለመብት ጥያቄዎቻችን መልስ የምናገኝበት፣ የሰላምና የብልጽግና ፣ በኣገራችንና ብሎም በዓለም ሰላምና መረጋጋት ይሰፍን ዘንድ ዱዐ እናደርጋለን።

በመሪዎቹ መታሰር ከሶስት ዓመት በላይ ላይ ታች ሲል የኖረው የሙስሊሙ ዜጋ ኣሁንም ለመሪዎቹ ያለውን ድጋፍና አክብሮት እየገልጸ ቢሆንም በዓሉን አስመልክቶ የኮሚቴዎቻችን ቤተሰቦችንና በየ ክልሉ በእስር የሚገኙ ወገኖቻችንን በመዘየር አጋርነታችንን ይበልጥ እናጎልብት እንላለን።

በመንግስት ቅንና አወንታዊ ርምጃ መረጋጋትና መተማመን ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎች ከማመቻቸት አንጻር ይህን የበዓል አጋጣሚ በመጠቀም የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ከቤተሰባቸውና ከመረጣቸው ሙስሊም ሕዝብ ጋር እሚቀላቀሉበትን መንገድ ይፈጥራል ብለንም እንገምታለን።

የሙስሊሙ ማሕበረሰብ ለኣገሩ ልማትና እድገት ካደረገውና እያደረገ ካለዉ አስትዋጾ ኣንጻር መንግስት በኣሉን የበለጠ ሊያሳምሩ የሚችሉ ርምጃዎችን መውሰዱ ተገቢ ነውም እንላለን ።

በድር ኢትዮጵያ መልካም በዓል እንዲሆንላችሁ እየተመኘ፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትብብርና መደጋገፍ የሚያስፈለግበት ጊዜ አሁን ነው በማለት ከጁላይ 30 እስከ ኦገስት 2 ካናዳ በሚካሄደዉ በ15ኛው የበድር ጉባኤ ተገናኝተን በሙስሊሙ ጉዳይ ላይ በጥልቅ በመወያየት ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለማምጣት የምንችልበትን መንገድ እንቀይስ በማለት ጥሪዉን ያቀርባል።

ኩሉ አሚን ወአንቱም ቢኸይር አላሁ አክበር!

በድር ኢትዮጵያ አለም-አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት

የዳይሬክተሮች ቦርድ

ሰሜን አሜሪካ

July 17, 2015

logo

 

Image result for in the name of allah in arabic

    (በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ)

በኢትዮጵያ  ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች

ላይ የተላለፈዉን ዉሳኔ በተመለከተ በድር ኢትዮጵያ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ፍጹም ሰላማዊና ህገ-መንግስትን መሰረት ያደረገ የመብት ጥያቄን ለመንግስት እንዲያደርሱለት ህዝቡ በራሱ ፍላጎት በፊርማዉ ባደባባይ መርጦ የላካቸዉ ተወካዮቹ ( ኮሚቴዎቹ ) በተራዘመ ፍትህ ከሶስት አመት በላይ በእስር ላይ መቆየታቸዉ የሚታወቅ ነዉ። እነዚህ ብርቅዬ የሙስሊሙ ተወካዮች ለመንግስት እንዲያደርሱ የተሰጣቸዉን ሶስት መሰረታዊ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄዎች በጽሁፍም በአካልም በመገናኘት ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር ሲያስረዱና ሲደራደሩ ቆይተዋል።

መንግስትም በወቅቱ የቀረቡለትን የመብት ጥያቄዎች አግባብ መሆናቸዉን እና የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጨዋነት በተደጋጋሚ መመስከሩ ይታወቃል። ህዝበ ሙስሊሙም ላቀረበዉ ህጋዊ፣ ሰላማዊ እና ህገመንግስታዊ የመብት ጥያቄ ከመንግስት በጎ ምላሽ በትእግስት በመጠባበቅ ላይ ሳለ ነበር ጭራሽ የህዝቡን አደራ ለማድረስ በክብር የተላኩትን ተወካዮች ያለ አግባብ ለእስር የተዳረጉት።

እነዚህ ዉድ የሀይማኖት መሪዎች ከሶስት አመት በላይ በፍትህ እጦት ምክንያት ከቤተሰቦቻቸዉና ከሚወዷቸዉ ህዝብ ተነጥለዉ በእስር እየተንገላቱ ም ሳለ ነበር ሙስሊሙ ማህበረሰብ ግን መንግስት ድምጹን ይሰማዉ ዘንድ በተለያዩ መንገዶች ቀድሞ በጀመረዉ ሰላማዊ መንገድ ብቻ ትግሉን በጽናት ያቀጣጠለዉ።

በድር ኢትዮጵያም ይህንን ሰላማዊ የመብት ጥያቄና ንቅናቄ ከጅምሩ በቅርበት ሲከታተለዉ እንደነበር እና ዉድ የህዝበ ሙስሊሙ ኮሚቴዎችም የተከሰሱበት የሽብርተኝነት ክስ ከነሱ ባህሪና ስነምግባር ጋር በማንኛዉም መልኩ እንደማይገናኙና ህገ መንግስቱ ያጎናጸፋቸዉን መብት ተጠቅመዉ የሀይማኖት ነጻነታቸዉን እንዲከበር በሰላማዊ መንገድ ሲያግባቡ (ሲጠይቁ ) የነበሩ ስለመሆናቸዉ በተለያየ ጊዜያት ሲገልጽ ቆይቷል።

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በአግባቡ በማጤን ማህበረሰቡን የሚያስማማ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ይሰጣል ብለን ብንገምትም በሰኔ 29 2007 መላዉን ሙስሊም ማህበረሰብ ከመንግስት ጋር ሆድና ጀርባ የሚያደርገዉን የፍርድ ዉሳኔ አስተላልፏል። የተሰጠዉ ዉሳኔም መርጦ በላካቸዉ ኮሚቴዉ ብሎም በመላዉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የተላለፈ እንደሆነና አላማዉም ሙስሊሙ ተሸማቆ ባገሩ ባይተዋር ሆኖ እንዲኖር ብሎም ዳግም የመብት ጥያቄ እንዳያነሳ ለማድረግ እንደሆነ ግልጽና አመላካች ነዉ።

መንግስትም ዳግም ጉዳዩን በመመርመር ይህንን የተዛባ የፍርድ ቤት ዉሳኔ እንዲመለከተዉ እና የተዘነበለዉን ፍትህ እንዲያቃና በአንክሮ እየጠየቅን በድር ኢትዮጵያም የተሰጠዉን የጥፋተኝነት ውሳኔ የማይቀበለዉ እና በጽኑ የሚያወግዘዉ መሆኑን እያሳወቅን ሙስሊሙ ማህበረሰብም ሰላማዊ የመብት ጥያቄዉን በአላህ ፈቃድ ከዳር ለማድረ በጽናት ይቆም ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ከመቼዉም ጊዜ የተሻለ ጠንካራ አንድነታችንን እንገንባ

አላሁ አክበር!

በድር ኢትዮጵያ አለም-አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት የዳይሬክተሮች ቦርድ

ሰሜን አሜሪካ

July 7, 2015