16th Annual Badr Convention in Nashville (click to see article in English) 

(በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ)

      የአላህ ሰላምና እዝነት በነቢዩ  ሙሀመድ (ሰወ) እና በቤተሰቦቻቸዉ እንዲሁም  የእሳቸዉን  ፈለግ በተከተሉት ላይ ይሁን

"There is no good in many of their conferences except the conferences of such as enjoin charity, or goodness, or the making of peace among men. And who so does that, seeking the pleasure of Allah, We shall soon bestow on him a great reward." (Surah Nisaa: 114)

16ኛዉ የበድር ጉባኤ  በናሽቭል

     በድር ኢትዮጵያ ከተቋቋመ እነሆ አስራ ስድስተኛዉን አመት አስቆጥሯል፤ በእነዚህ አመታት ዉስጥ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናዉን መቆየቱ ይታወቃል፤ከሚያከናዉናቸዉም ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንደኛዉ በየአመቱ በሚካሄደዉ በበድር ኢትዮጵያ አመታዊ ጉባኤ ሙስሊሙን ማህበረሰብ በማገናኘት የዳዋ  ፕሮግራሞችን ከመተግበሩ አልፎ በተለያዩ አበይት ርእሶችና በወቅታዊ ችግሮች ላይ በመወያየት የመፍትሄ  ሀሳቦች መሻትን ያካትታል።

     በዘንድሮም ዓመት አስራስድስተኛዉን የበድር ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዘጋጅነት  በተመረጠዉ  በናሽቭል ተኒሲ እንደሚካሄድ ስናበስር ከታላቅ ደስታ ጋር ነዉ!!   

      በዚህ ታላቅ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ከሰሜን አሜሪካ ግዛቶች እንዲሁም ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎችን ጨምሮ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች አንድነታቸዉን ለመግለጽና እስላማዊ ወንድማማችነታቸዉን ለማጠናከር ብሎም በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ለመመካከር ወደዚሁ ይተማሉ። ከ (ሀምሌ) JULY 28 እስከ 31 /2016 በሚካሄደዉ በዚሁ ታላቅ ጉባኤ ተካፈይ ይሆኑ ዘንድ በድር ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት በታላቅ አክብሮት ጥሪውን ያቀርባል።

አላሁ አክበር !!!

በድር ኢትዮጵያ አለምአቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት

የዳይሬክተሮች ቦርድ

ሰሜን አሜሪካ

DECEMBER  2015

Nov 26, 2015 | Badr Ethiopia

ታላቅ የሀዘን መግለጫ 

إِنَّا للهِ وَإِنَّـا إِلَيْهِ رَاجِعونَ

ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂኡን!!! ታላቁ ሼህ መሀመድ ሲራጅ ማርሶ ሳሊህ አላህ ለጄነት ይበላቸዉና ወደ አሄራ ሄደዋል።

ሼህ መሀመድ ስራጅ ከአባታቸዉ ሥራጅ ማርሶ ሳሊህ እና ከእናታቸዉ ከወ/ሮ መና ኑሩ በ 1343 ዓመተ ሂጅራ በሰፈር ወር 15ኛዉ ቀን በራያ አካባቢ ተወልደዉ በሰፈር ወር 13ኛዉ ቀን በ 1437 ዓመተ ሂጅራ በ 94 ኛዉ እድሜያቸዉ ሞቱ።

ሼህ መሀመድ ሲራጅ በሀገር ዉስጥ በታለያዩ አካባቢ በመዘዋወር የዲን እዉቀትን የተማሩ ሲሆን በቁርዐንና ተፍሲር እንዲሁም ፍቂህ እና ኡሱል ሰርፍ እና ነህዉ በላጋ ቀርተዋል። ከሀገር ዉጭም በየመን እንዲሁም በመካ የዲን ትምህርታቸዉን ተከታትለዋል።

በኋይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት የፓርላማ ተመራጭ በመሆን ለበርካታ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በየመን ሀገር የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ሆነዉ በሹመት ተልከዋል። ከዚያ በኋላ መካ ላይ ራቢጣቱል አለመል ኢስላሚ ሙስተሻር (አማካሪ) በመሆን ሰርተዋል። ድርጅቱንም በመወከል ወደ አሜሪካ ተልከዉ በኒዉዮርክ ሲያገለግሉ ቆይተዉ የአገልግሎት ጊዜያቸዉን ሲያጠናቅቁ ዲሲ አካባቢ ኑሮአቸዉን መስርተዉ በፈርስት ሂጅራ ፋዉንዴሽን ኢማም እና የዳዋ ክፍል ሀላፊ ሆነዉ አገልግለዋል።

በድር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት ሲቋቋም ( ስያሜዉን ጨምሮ) በተለያዩ ስቴቶች በመዟዟር ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞችን በማጠናከርና የዳዕዋ ትምህርት በመስጠት ልዩ አስተዋጽኦ ያደረጉ ታላቅ ሼህ ነበሩ። በህመም የአልጋ ቁራኛ እስከሆኑ ድረስ ዲናቸዉን የካደሙ፤ ሙስሊሙን ማህበረሰብ አንድ የሚሆንበትን የዲን አስተምሮ እያከናወኑ ኖረዋል።

በስተመጨረሻም ቨርጂኒያ አካባቢ ሰፈር 13ኛዉ ቀን ረቡእ እለት በ 1437 ዓመተ ሂጅራ በ 94 ዓመታቸዉ በሞት ተለይተዋል።

አላህ (ሱወ) የሄዱበት አገር አላህ ያሳምርላቸዉ !!!
አላህ (ሱወ) የሄዱበት አገር ከነበሩበት አገር የተሻለ እና የተመቻቸ ያድርግላቸዉ !!! 
ከዋህሸተል ቀብር አላህ ይጠብቃቸዉ !!!

በድር ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት ለቤሰቦቻቸዉና ለዘመዶቻቸዉ አላህ (ሱወ) መጽናናትን እንዲሰጣቸዉ ይመኛል።