በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ   

በቢሾፍቱ ከተማ የተፈጸመዉ አሳዛኝ ክስተት

       መስከረም  22/ 2009 በሀገራችን በቢሾፍቱ ከተማ  የኦሮሞ  ብሄረሰብ ዓመታዊ የኢሬቻ  በዓልን ለማክበር በተገኙ ወገኖች ላይ የተፈጸመዉ ግድያና የመቁሰል አደጋ አስከፊና አሳዛኝ ተግባር መሆኑን እየገለጽን በድር ኢትዮጵያም ይህንን ኢሰብአዊ ድርጊት በአጽንኦት ያወግዛል።              

      ዜጎች በተለያዩ ጊዜና ቦታ ብሶታቸዉን ባሰሙና ህገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄ ባነሱ ጊዜ ከመንግስት በኩል የሚጠበቀዉ ሁኔታዎችን በጥሞና አገናዝቦ ህብረተሰብን ያማከለ ዘለቄታዊ መፍትሄ መሻት እንጂ ነገሮችን በሀይል መጨፍለቅና ሰፊዉ ህብረተሰብ ላይ አለመረጋጋትን በመፍጠር ሊመጣ የሚችል አንዳችም አይነት ዉጤት የለም። ይልቁን ይህን አይነቱ ተግባር አለመረጋጋትን ከመፍጠሩ በተጨማሪ የሀገሪቱን ህልዉናም አደጋ ላይ እንደሚጥል ከማንም የተሰወረ አይደለም። ስለዚህ ለሚነሱ የመብት ጥያቄዎችና ብሶቶች ሰላማዊ በሆነ መልኩ መፍትሄ መፈለግና በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጸመዉ ግድያና ሰቃይ እንዲቆም ማድረግ የመንግስት ግዴታ መሆኑን እየገለጽን በዚህ ባህላዊ በዓል ተገኝተዉ ደስታቸዉን ለመግለጽ በመገኘታቸዉ ሳቢያ የህይወት መስዋእት ለሆኑት ሁሉ ጥልቅ ሀዘን የተሰማን መሆኑን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸዉ አላህ (ሱወ)  መጽናናትን እንዲሰጣቸዉና በሀገራችንም ሰላምን እንዲያመጣልን እንማጸናለን።    

   አላህ (ሱወ)ቀጥተኛዉን መንገድ ይምራን አሜን !

 

             የበድር የዳይሬክተሮች ቦርድ                   

                                   ሰሜን አሜሪካ                                          

 ኦክቶበር 3 / 2016

 

                                                                                                            

                                                                  

                                                                            

                                                                                      በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ     

የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችንን መፈታት በተመለከተ ከበድር የተሰጠ መግለጫ

    2004 . የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ያነሷቸዉን ሶስት መሰረታዊ የእምነት ነጻነት እና የመብት ጥያቄዎችን ለመንግስት እንዲያቀርቡለት መርጦ የላካቸዉ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት መሀካል የተወሰነት ላላፉት አራት ዓመታት ያለ ጥፋታቸዉ ከታሰሩበት ወጥተዉ ወደ ናፈቃቸዉ ቤተሰብና ህዝብ በመቀላቀላቸዉ በድር ኢትዮጵያ የተሰማዉን ደስታ በአላህ ስም ለመግለጽ እንወዳለን።

    የኮሚቴ አባላትም ሆናችሁ ከእነሱ ጋር በተያያዘ ለእስር የተዳረጋችሁ ሌሎች ወንድሞችንና እህቶቻችን ምንም ዓይነት ለእስር የሚያበቃ ወንጀል እንዳልፈጸማችሁ ብናምንም ፈጣሪያችን አላህ ባሮቹን  በተለያዩ  ሁኔታ እንደሚፈትን ስለነገረን ያጋጠማችሁን ፈተና ተቋቁማችሁ በቆማችሁለት ሰላማዊ ትግል ጸንታችሁ ለዚህ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን።

   በተመሳሳይ ሁኔታ የህዝብ ተወካይ በመሆናዉ ብቻ ተወንጅለዉና በአንድ አይነት የክስ መዝገብ ተከሰዉ አሁን ተነጥለዉ የቀሩት ወንድሞቻችን በቅርብ ቀን በነጻ እንደሚሰናበቱ አሁንም ተስፋችን በአላህ ላይ የጠነከራ ነዉ። ከምንም በላይ እናንተንና ሌሎች በርካቶችን ለእስርና ለእንግልት እንደዚሁም ለስደትና ለሞት ያበቃዉ ያቀረብናቸዉ ሶስት ቀላል የእምነት ነጻነትና የመብት ጥያቄዎች ተገቢዉን ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ የጀመርነዉ ሰላማዊ ትግል ተጠናክሮ እንደ ሚቀጥል በድምጻችን ይሰማ መግለጫ ተረጋግጧል።

   በድር ኢትዮጵያም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መብት እንዲከበር መጣር ከጀመረ ከአመታት በኋላ በተነሳዉ የህዝብ እንቅስቃሴ አካል በመሆን የሚችለዉን ሲያደርግና በተፈለገበት ቦታ ሁሉ ሲገኝ እንደነበር ሁሉ ወደፊትም ጥያቄዎቻችን እስኪመለሱና የተቀሩት የኮሚቴዉ አባላትና በተያያዘ ሁኔታ የታሰሩት የመብት ጠያቂዎች ለቤታቸዉ እንከሚበቁ ድረስ ትግሉን አጠናክሮ  እንደሚቀጥል ማሳወቅ እንወዳለን። 

    እንዲሁም መንግስት በዉድ ሀገራችንኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ህዝቦች የሚያቀርቡትን ጥያቄ በጥሞና ተመልክቶ አፋጣኝ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ከመጠን ያለፈ ሀይል በመጠቀሙ እየረገፈ ያለዉ የወገኖቻችን ህይወት አሳሳቢ መሆኑን ተረድቶ ለመፍትሄዉ እንዲተጋ ማሳሰብ እንወዳለን። ሀገራችን ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ተረጋግጦ ፍትህ ሰፍኖባት ዜጎቿ በነጻነት ዉለዉ የሚገቡባት እንድትሆን የዘወትር ጸሎታችን ነዉ

    በመጨረሻም በድር ኢትዮጵያ በኢትዮጵያና በየ አለማቱ ለምትገኙ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች እንኳን 1437  . የኢድ አል አድሀ አረፋ በሰላም አደረሳችሁ እያለ መልካም ምኞቱን ይገልጻል።

ትግላችን በአላህ ፈቃድ እድከ ድል ደጃፎች ድረስ ይቀጥላል

አላሁአክበር

                                                                              የበድር ኢትዮጵያ የዳይሬክተሮች ቦርድ           

                                                                                    ሰሜን አሜሪካ                                    

                                                                              September 12, 2016