በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ

Bottom of Form

አላስፈላጊ ዘለፋና ስም ማጥፋት ዘመቻ ይቁም

 

            وَالَّذِينَ يُؤْذُونَ الْمُؤْمِنِينَ وَالْمُؤْمِنَاتِ بِغَيْرِ مَا اكْتَسَبُوا فَقَدِ احْتَمَلُوا بُهْتَانًا وَإِثْمًا مُّبِينًا       

               እነዚያም ምእመናንንና ምእመናትን ባልሰሩት ነገር በመዝለፍ የሚያሰቃዩ እብለትንና ግልጽ ሀጢአትን በእርግጥ ተሸከሙ

                                                                                                                 አል-አህዛብ : 58

      የኢትዮጵያ ሙስሊሞችች ለዘመናት በአጼዎች መጠነ ሰፊ ግፎች ተፈራርቀዉበታል። አይነቱና ይዘቱን ቢቀይርም አሁንም ጭቆናዉን ከማህበረሰቡ ጀርባ  አሽቀንጥሮ  ለመጣል አልተቻለም። ህዝበ ሙስሊሙ ከመቼዉም ጊዜ  በተሻለ ለእምነቱ ነጻነት እየከፈለ ያለዉ መስዋእትነት ከሁሌዉም በበለጠ ሁኔታ በንቃትና በጽናት ላይም ይገኛል። ይህንኑ ሂደት በመጠቀም  በሀገር ዉስጥ ያለዉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ እና በዲያስፖራ የምንገኝ ሙስሊም ማህበረሰብ በእምነታችን ላይ የደረሰብንና እየደረሰብን ያለዉን ጭቆና በተቻለ መጠን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገርስሶ ለመጣል ያለንን የሰዉ ሀይል ፤ ገንዘብ ፤ እደረጃጀት እና መሰል ሀብቶቻችንን በጋራ በመጠቀም ዉጤት ማምጣት እንደሚጠበቅብን ለሁሉም ግልጽ ሀሳብ ነዉ። ሆኖም ግን በተወሰኑ አካላት በኩል እየተከናወነ ያለዉ በተቃራኒዉ መልኩ ሲፈጸም  ዝም ማለትን አላስቻለንምና ሀሳብ መሰንዘርም ሆነ ሂደቱን ፈር ማስያዝ የግድ ይላልና የበኩላችንን ለመወጣት ተገደናል።

     በቅርቡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ደጋፊዎች ህብረት ለ3ኛ ጊዜ  አመታዊ ጉባኤዉን በዋሽንግተን ዲሲ ባካሄደበት ወቅት የጉባኤዉን መሪቃል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የትግል አቅጣጫ መቀየስ’’ ቢልም በፕሮግራም ከቀረቡ ርእሶች በድርን ፤ የቀድሞ አመራር አካላትን እንዲሁም  ደጋፊ አባላትን እስላማዊ አደብና ስነ ምግባር በጎደለዉ መልኩ በስም እየተጠቀሱ መቅረቡ ፤( ምንም እንኳን የአንድ ግለሰብ ሪፖርት /ሀሳብ/ ነዉ እንኳ ቢባልም  መድረኩን የሚመሩ አካላት እና የእምነት አባቶች ማድረግ የነበረባቸዉ ከአጀንዳና ከእስላማዊ አደብ ወጥተሀልና አቁም ማለት ወይንስ በሳቅ መደገፍ ? አላህ (ሱወ) ልቦና እንዲሰጣቸዉ እንመኛለን)  የሆነ ሆኖ ይህ የድርጅቶች እና የሙስሊም ማህበረሰብ ህልዉናን በግልጽ የሚፈታተን እኩይ ተግባር ሆኖ እግኝተነዋል።

      በድር ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅት ራሱን የቻለ ድርጅት ነዉ። ህገ ደንብ ፤ አላማ ፤ ፕሮግራም ፤ መሪና  ደጋፊ አባላት ያሉት ብሎም አቅም በፈቀደለት መጠን በዲያስፖራ ለሚገኙ ኮምዩኒቲዎችና ለሙስሊሙ ማህበረሰብ በርካታ መልካም ተግባራትን የፈጸመና በመፈጸም ላይ ያለ በተለይ በዲያስፖራ ቀደምትነት ያለዉ ሁሉን አቀፍ እስላማዊ ድርጅት ነዉ። ድርጅቱም ከጁላይ 13 እስከ 16/2017 በሳንዲያጎ  ካሊፎርኒያ ባደረገዉ አመታዊ ጉባኤ ላይ አመታዊ ሪፖርቱን አቅርቦ የተከናወኑና በመሰራት ላይ ያሉ ስራዎችን በተለይ የሂሳብ የኦዲት ሪፖርት ይፋ ካደረገ በኋላ ጉዳዩ እንደ ድርጅት በማይመለከታቸዉና የድርጅቱ አባል ባልሆኑ ግለሰቦች ስለ ሌላ እስላሚ ድርጅትና አባላትን በተመለከተ የተፈጸመዉ የስም ማጠልሸት ተግባር ሂደቱ በግለሰቦች እና በድርጅቶች ላይ የተቃጣ ቢሆንም ነገ በእስልምና ላይ እንደሚተገበር ልብ ልንል ይገባል። በሌላ መልኩ  ለተለያዩ  አላማ ወይንም ጥቅም ለማስፈጸም ብለን የምናካሄደዉ ዛሬ በኡማዉ ነገ ደግሞ በአላህ ፊት የሚያስጠይቅ መሆኑን ፈጽሞ ሊዘነጋ አይገባም እንላለን ።

      ይህን መሰል አሉባልታና ስም ማጥፋት ዘመቻ የተፈጸመዉ ለመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም  በተፈጸሙባቸዉ ጊዜያት ሁሉ ምላሽ ያልሰጠነዉ  እነዚህ ወንድሞቻችን  ቀደም ሲል ለእስልምናና ለድርጅታችን ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ግምት ዉስጥ በማስገባት ፤ ዉሎ  ሲያድር ከድርጊታቸዉ ተጸጸተዉ ይመለሳሉ ብሎ በማመን ፤ በሚካሄዱ የቃላት ልዉዉጥ ሳቢያ በኡማዉ  መካከል ተጨማሪ ፊትና እንዳይፈጠርና ለዚያም ድርጅታችን ምክንያት እንዳይሆን በመስጋትና ሀቁን ላልተገነዘበዉ ክፍል ደግሞ ስሜቱ ተጠብቆለት የራሱን አቅጣጫ እንዲወሰን ለማስቻል በሚል ነበር፤ ሌላዉ አሳዛኙ ነገር አሉባልታዉና የስም ማጣፋቱ ዘመቻ በተለያዩ መልኮች የተከናወኑ ቢሆንም በመፍትሄ አፋላላጊ ኮሚቴዎቻችንና በታዋቂ ኡስታዞቻችንም ላይ የተፈጸመ መሆኑ ሂደቱ ምንን ያሳየናል ? ጉዞአችን ወዴት ነዉ ?  ለማለት እንጂ አታዉቁትም ለማለት አይደም። አሁን ግን ያ ሁሉ ጊዜዉ አልፎበታል ። ትእግስትም ልክ አለዉና እያንዳንዱ ማህበረሰብ ያለዉን ሂደት በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ሊገነዘብ በሚችልበት ደረጃ ላይ ይገኛልና የድርጅታችን ህልዉናና የህዝባችንንም ስሜት መጠበቁ ግድ ይላልና ከአሁን በኋላ በተመሳሳይ መልኩ ለሚፈጸሙ ስም ማጥፋት ዘመቻዎችና መሰረተ ቢስ አሉባልታዎች ሀቅን ተመርኩዘን እስላማዊ አደብን  በተላበሰ መልኩ መልስ የምንሰጥ ስለሆነ ይህንኑ አባላቶቻችን ሆኑ ሌሎች ወገኖች እንዲረዱልን እያሳወቅን የህግ ከለላም አስፈላጊ በሆነበት ደረጃ ላይ ሁሉ መጠቀም እንዳለብን እናምናለን።

      በመጨረሻም የማንኛዉም ድርጅት ብቃት የሚለካዉ ለህብረተሰቡ በሚሰጠዉ አገልግሎት እንጂ በሚወራዉ ዜና ወይንም በሚቀርበዉ ፕሮፓጋንዳ አለመሆን ተረድተን እያንዳንዱ ድርጅት ለቆመለት አላማ ራሱን ችሎ መቆም እንጂ በሌሎች ላይ በመንጠላጠል ተቀባይነትና ለዉጥ ለማምጣት መጣሩ የወደፊት የረጅም ጊዜ ጉዞአችንን አያሳካምና ጥንቃቄ ያሻል እንላለን።

 

     ሁላችንንም አላህ ቀጥተኛዉን መንገድ ይምራን።

 

 የበድር  የዳይሬክተሮች ቦርድ                               

    ሰሜን አሜሪካ                 

     ኦገስት 1/2017

 

 

 

 

 

                                                                                     

                                                                                        በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ