በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ

 

የሳጃ ሙስሊሞች ትኩረት ይሻሉ

     በደቡብ ክልል በየም ልዩ ዞን ሙስሊሙ እና ክርስቲያኑ ማህበረሰብ ለረጅም ዘመናት በጋራ በኖሩባት ሳጃ ከተማ    ሰላምን በማይናፍቁ አካላት መሰሪ ሴራ ምክንያት በተፈጠረዉ ግጭት ብዙ ንጹሀን ሙስሊም የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ በደረሰዉ አዛኝ ክስተት የህይወት መጥፋት እና የንብረት መዉደም ደርሷል።   

     በተለይ ሀገራችን ፍቅርንና አንድነትን መርህ አድርጋ በምትጓዝበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ይህን የመሰለ ኢሰብአዊ ድርጊት በአንድ አካባቢ ለዘመናት በኖሩ ማህበረሰብ መካከል  ሆን ተብሎ ችግር እንዲፈጠር መጣር በጣሙን ከማሳዘኑ ባሻገር የዚህን ድርጊት ተባባሪ የሆኑ ግልሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በህግ መጠየቅ አለባቸዉ። ይህን መሰል የማፈናቀል ተግባር ትኩረት ካልተሰጠዉና ካልተገታ በቀር ስር እየሰደደ ሙስሊሙን ማህበረሰብ ለማጥቃት የታሰበ ሴራ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይገባል።

    በድር ኢትዮጵያም በተፈጠረዉ ቀዉስ የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ አንዳንድ መሰሪ የከተማዉ አስተዳደሮች በህዝቡ መካከል የሀይማኖትና የዘር ግጭት በማስነሳት የአካባቢዉን ሰላም በማደፍረሳቸዉ  በተፈጠረዉ ችግር አብዛኛዉ ሙስሊም ማህበረሰብ አካባቢዉን ለቆ ለመዉጣት እንደተገደደ የአካባቢዉ ነዋሪዎች አሳዉቀዋል ። በድር ኢትዮጵያም ይህን መሰል እጅግ አሳዛኙና ዘግናኝ ድርጊት ፈጻሚዎች ከእኩይ ተግባራቸዉ ታቅብዉ ሰላማዊዉ ህብረተሰብ ቀድሞ ወደ ነበሩበት አንጻራዊ ሰላም እንዲመለሱ ምኞቱ ሲሆን መንግስትም አስፈላጊዉን ትኩረት ሰጥቶ ያለአግባብ ለተፈናቀሉ ወገኖች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ችግሩን በዘላቂነት እንደሚቀርፍ በመተማመን  ጭምር ነዉ።

   አላሁ አክበር

  በድር ኢትዮጵያ       ሰሜን አሜሪካ       ጁላይ 15 2018