በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ

በበድር አካዉንት ተሰብስቦ ስለነበረዉ ገንዘብ ማብራሪያ ስለመስጠት

     የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት የመብት ፤ የእምነት ነጻነት እና የህገ መንግስት መከበር ጥያቄን አስመልክቶ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሲያከናዉኑ መቆየቱ ግልጽ ነዉ።  ከሙስሊሙ ማህበረሰብ የቀረቡ ሶስት መሰረታዊ የእምነት ነጻነት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ብሎም በተቻለ መጠን ሰላማዊነቱን ጠብቆ እንዲጓዝ በብቃት ማስፈጸም የሚችሉ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በማዋቀር እንቅስቃሴዉን በይፋ ጀምረዋል።

    በዲያስፖራ የምንገኝ ሙስሊም ማህበረሰብም ለመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች የዉክልና ፊርማ ከማሳረፍ ጀምሮ ሁሉም አቅም በፈቀደ መጠን ጠንካራ እንቅስቃሴ ያደረጉና በማድረግ ላይ ያሉ ሲሆኑ በተለይ በየኮምዩኒቲዎች ደረጃ የታየዉ እንቅስቃሴ እጅግ በጣም አኩሪ ነበር።

      ከህዝበ ሙስሊሙ ሙሉ ዉክልና የተሰጣቸዉ የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላትም ሆነ ሌሎች ከኮሚቴዉ ጋር ግንኙነት አላቸዉ ተብለዉ የሚገመቱ ወንድሞችና እህቶች በመንግስት በግፍ ለእስር እና መሰል ስቃዮች በመዳረጋቸዉ ሳቢያ እንዲሁም የታሳሪ እና ከሀገር የተሰደዱ ቤተሰቦችን ጨምሮ ለመደገፍ እንዲቻል ከየኮምዩኒቲዎች የገንዘብ ማሰባሰብ መካሄዱና ይህም ገንዘብ በበድር አካዉንት ገቢ ሆኖ ለሚፈለገዉ አገልግሎት እንዲዉል በማሰብ መከናወኑ ይታወቃል።

   የዚህ ገንዘብ አፈጻጸም በወቅቱ በነበረዉ የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ፤ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችን እና ከነሱ ጋር ተያያዥነት ባላቸዉ ጉዳዮች በርካታ የሙስሊሙ ማህበረሰብ በግፍ ለእስር የተዳረገበትና የተለያዩ አይነት ሰቆቃዎች ይፈጸምባቸዉ በነበረበት ወቅት ስለነበር ይህን መሰል መረጃዎች ለህዝብ መልቀቁ በህዝባችን ላይ ሊደርስ የሚችለዉን የከፋ በደልና ችግር እንዲሁም መንግስት ለፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀምበት እንደሚችል በመገመት መረጃዉን ማቆየቱ ይታወቃል። ሆኖም ይህ ሂደት በዲያስፖራ በምንገኝ ሙስሊም ማህበረሰብ መካከል በተፈጠሩ የአካሄድ ልዩነቶች ሳቢያ ሂደቱ አቅጣጫዉን ቀይሮ በአሁኑ ወቅት የችግሮቻችን መሰረት ሆኖ እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል።

      በፋሚሊ ሰፖርት እና ኢመርጀንሲ ፈንድ በሚል የተሰበሰበዉ ገንዘብ በአግባቡ በወቅቱ ለነበሩ የኮሚቴዉ አባላት በማድረስ ስለመረከባቸዉም በፊርማቸዉ ያረጋገጡበትን መረጃ መኖሩ እና ከዚህ ቀደም በሲያትል ኮምዩኒቲ ለአባላት እና በናሽፊል እና ሳንዲያጎ ደግሞ በየዓመቱ በተደረገዉ የበድር ዓመታዊ ኮንቬንሽን ለተሳታፊ አባላት እንዲሁም በቅርቡ ሰላም ፋዉንዴሽን ባዘጋጀዉ የህዝብ ስብሰባ በግልጽ ያስረዳንና መረጃዉንም ለማሳየት ተችሏል። ይህንኑ የበድር አባል ላልሆኑ አካላትም በግልጽ ለማሳወቅ እየወደድን በአሁኑ ወቅት ለመግለጽ የተገደድንበት ሁናቴም በተፈጠሩ አለመግባባቶች ሳቢያ ላሉት ልዩነቶች የችግሩ ምክንያት ገንዘቡን አድርገዉ ያለአግባብ እየተጠቀሙበት ስለሆነና በሌላ መልኩ በአሁን ወቅት በሀገራችን ያለዉን የፖለቲካ ሂደት እንዲሁም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችን ያሉበትን ሁናቴ ግምት ዉስጥ በማስገባት በወቅቱ የተሰበሰበዉ ገንዘብ የደረሰበትን ደረጃ ለህዝብ ይፋ በማድረግ ማሳወቁ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሲሆን ለወደፊትም ቢሆን ይህን መሰል ጥንቃቄ የሚሹ እንቅስቃሴዎች በማንኛዉም ወገን በሚከናወኑበት ጊዜ አንገብጋቢነታቸዉን ግምት ዉስጥ በማስገባት መወሰድ የሚገባቸዉን ጥንቃቄዎች ትኩረት ሰጥተን መንቀሳቀስ እንደሚገባን ለማስገንዘብ እንወዳለን።

 አላህ (ሱወ) ቀጥተኛዉን መንገድ ይምራን

     በድር ኢትዮጵያ   

   ሰሜን አሜሪካ                                                                                                                       

  ጁን 27, 2018