በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ       

ዶ/ር አቢይ አህመድ አሊ በጠቅላይ ሚኒስተርነት መመረጥ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

     ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ለሀይማኖት እኩልነት፤ ለፍትህ እና ለህገ መንግስት መከበር ሰላማዊ በሆነ እንቅስቃሴ ድምጻቸዉን በአደባባይ ማሰማት ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ሰቆቃዊ ችግሮች ፤ የመታሰር ፤ የመሰደድ እንዲሁም የግድያ እጣ ቢደርስባቸዉም በሀገሪቱ የነበረዉን ዝምታ እና አንገት ድፍቶና አጎንብሶ በፍርሀት ተሸማቆ የነበረዉን የትግል መንፈስ ከሸበበዉ ፍርሀትና ከቀዘቀዘዉ መንፈስ በመቀስቀሱና የትግል ስሜቱን በማሟሟቅ አያሌ እንቅስቃሴዎችን በሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች እንዲጧጧፍ ሰበብ ሆኖ የለዉጥ ተምሳሌት ለመሆን በቅቷል።፡      

   የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች የእምነት ነጻነትን አስመልክቶ ያነሱዋቸዉ መሰረታዊ ጥያቄዎች፤ ያነገቡዋቸዉ መፈክሮች ፤ ያሰሙዋቸዉ ድምጾች በሙሉ በሕዝባችን ስነ ልቦና ለዉጥ ማምጫ መንስኤ እና ለሞራሉ መነሳሳት ሰበብ ሆነዉ ለመብቱ ታጋይና አይደፈሬ ጀግና ወጣት እንዲወለድ ብሎም ለዛሬዉ ለዉጥ እንድንደርስ ሀገራዊ አሻራዉን አሳርፏል።

   በድር ኢትዮጵያ የሰላማዊ ትግል ፤ የፍትህና የዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ የለዉጥ ሂደት የደረሰበትን የድል ጉዞ እያወደሰ የዚህ መልካም የትግል ዉጤት አደራ ተረካቢ የሆኑት አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አቢይ አህመድ አሊን እንኳን ለዚህ አበቃዎት እያልን በመጀመሪያዉ እለት ባደረጉት ንግግር ላይ ያነሱዋቸዉን መሰረታዊ ጉዳዮችን ጨምሮ በሀገሪቱ ያሉ በርካታ ዉስብስብ ችግሮችን ለስኬት እንዲያበቁና አገራችን የዲሞክራሲ ብሎም የፖለቲካ ምህዳሯ ሰፍቶ ሁሉም ቅን አሳቢ ልጆቿ በእኩል የሚሳተፉበት መድረክ እንዲሁም ፍትህ የሰፈነበት ምርጫ ተካሂዶ የኢትዮጵያ ህዝብ ያመነበትና የመረጠዉ ፓርቲም ሆነ ድርጅት ስልጣን ተረክቦ በልማትም ሆነ በማህበራዎ  ኑሮ እድገት ለማምጣት በሚደረገዉ ትግል አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚጥሩና ለዉጤትም እንደሚያበቁት በመተማመን ነዉ።

   በድር ኢትዮጵያ የሀገራችን ሙስሊሞችን ጉዳይ በሚመለከት በ2007 ስምንት ያህል ጥያቄዎችን በአስራ ዘጠኝ ገጾች ከነማብራሪያዉ ያዘለ ጽሁፍ አዘጋጅቶ ከቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስተር ጋር በተገናኘበት ጊዜ አቅርቦና ተወያይቶበትም ነበር። እነዚያ ወሳኝ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ወቅታዊ ጥያቄዎች አሁንም ጥያቄዎቻችን መሆናቸዉን እያሳሰብን  በጊዜዉ ምላሽ አግኝተዉ ቢሆን ኖሮ ለበርካታ ሙስሊሞች መንገላታት ፤ መታሰር እና መሰደድ እንዲሁም ሀገሪቱ አሁን የገባችበትን አጣብቂኝና መጠነ ሰፊ ቀዉሶች ዉስጥ ባልገባች ነበር ፤ የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ከአራት ዓመት በኋላም ባልታሰበ ነበር። የሙስሊሞች ዋና ጥያቄ የሀገሪቱን ህገ መንግስታዊ መብትን ተከትሎ የእምነት መሪዎቻችችን ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት በነጻነት መምረጥ መቻልና በሀይማኖታችን አተገባበርም ሆነ በትምህርትና በአምልኮ ተቋሞቻችን መንግስት እጃችሁን አታስገቡ  የሚል ነዉ።

እነዚህንና መሰል በርካታ መሰረታዊ መልስ የተነፈጉ ጥያቄዎችችን በአዲሱ የለዉጥ አራማጅ አስተዳደር መልስ ያገኛሉ ብለን እንገምታለን። ለእነዚህም ክንዋኔዎች ተግባራዊነት ይረዳም ዘንድ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችንን በማነጋገር የመፍትሄዉ አካል ሊያደርጋቸዉ እንደሚገባም እናምናለን፤  በድር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅትም አጋዥ በመሆን የበኩላችንን ለማበርከት ዝግጁ መሆናችንን እየገለጽን ዶክተር አቢይ አህመድ አሊ ለመፈጸም ቃል የገቡትን ሁሉ ተግባራዊ ሆኖ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል መግባባትና መተባበር ጠንክሮና ጎልቶ የዜግነት ግዴታችንን በጋራ ለመወጣት በአንድነት እንድንሰራ ለኀይማኖት መሪዎች ፤ ለፖለቲካና ለሲቪክ ድርጅቶች ሁሉ ቀድሞ ከነበረዉ በተሻለ ሀገራዊ መግባባት ባለዉ መልኩ ለለዉጥ እንነሳ ለማለት እንወዳለን።

                                                                                  በድር ኢትዮጵያ                                                                                                                                                        ሚያዝያ 13, 2018                                                                                                                                 ሰሜን አሜሪካ