በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ

    فَانقَلَبُوا بِنِعْمَةٍ مِّنَ اللَّهِ وَفَضْلٍ لَّمْ يَمْسَسْهُمْ سُوءٌ وَاتَّبَعُوا رِضْوَانَ اللَّهِ ۗ وَاللَّهُ ذُو فَضْلٍ عَظِيمٍ - 3:174

 ከአላህም በኾነ ጸጋና ችሮታ ክፉ ነገር ያልነካቸዉ ኾነዉ ተመለሱ።የአላህንም ዉዴታ ተከተሉ፤አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤትነዉ። (3 ፡174)

መከራ ያልበገረዉ ጽናት

   የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በተለያዩ ዘመናት ከአጼዎች ጀምሮ በእምነታቸዉ ላይ እየተፈራረቀባቸዉ የመጣዉን ግፍና በደል ከላያቸዉ አሽቀንጥሮ ለመጣል ብሎም በሀገሪቱ የእምነት ነጻነት ፤ የህገ መንግስትና የመብት መከበርን ጥያቄ መርህ በማድረግ ከመንግስት ጋር በመነጋገር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንዲቻል ህዝበ ሙስሊሙ በፊርማዉ ወክሎ የላካቸዉን ንጹሀንና ብርቅዬ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ብዙ መከራ ፤ ስቃይ ፤ እስርና እንግልት ሲደርስባቸዉ ቆይቷል። ምንም እንኳን ከፊሎቹ ተወካዮቻችን ቀደም ብለዉ ከእስር በተለያዩ ጊዜያት ቢለቀቁም የተቀሩት ማለትም ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ፤ ኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋ ፤ ኡስታዝ መሀመድ አባተ እና ካሊድ ኢብራሂም ያለአግባብ ተለይተዉ ቢቆዩም በአላህ (.) መልካም ፈቃድ ከእስር ተለቀዉ ከቤተሰቦቻቸዉና ከሚወዱት እና ከሚወዳቸዉ ህዝብ ጋር ተገናኝተዋል፤ መለቀቃቸዉ እጅግ በጣም አስደስቶናል። እንኳን ደስ አላችሁም እንላለን።

      ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በሙሉ ከእስር ቢፈቱም ከእነሱ ጋር ተያያዥነት ባለዉ መልኩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች አሁንም በእስር እንደሚገኙ ይታወቃል። በሌላ መልኩ ከጅምሩ ከተነሱ ሶስቱ መሰረታዊ የእምነት ነጻነት ጥያቄዎቻችን አንዱም ምላሽ አላገኘም። 

      የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብትና የእምነት ነጻነትን አስመልክቶ እንቅስቃሴዉ ሲጀመር በድር ኢትዮጵያ ከሰላማዊ ትግሉ ጎን ቀድሞ የቆመና እስካሁንም ድረስ ከትግሉ ጋር አብሮ ያለ ድርጅት ነዉ።  በኮሚቴዎቻችን ላይ የተወሰደዉ ኢፍትሀዊ ርምጃን ሲያወግዝ ቆይቷል ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታም እንዲፈቱ ያላሰላሰ ጥረት አድርጓል። በዚህ አጋጣሚ ከእስር የተፈቱ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትንና ቤተሰቦቻቸዉን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ በቀጣይም አንድነታችንን ከመቼዉም ጊዜ በተሻለ በማጠናከር የተነሳንለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ብሎም በሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ እኩል ተጠቃሚ  ለመሆን ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባን በድር ኢትዮጵያ በአጽኖት ለመግለጽ እንወዳለን። 

በድር ኢትዮጵያ

ሰሜን አሜሪካ

የካቲት 15/ 2018