በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ               

ኢ ድ   ሙ ባ ረ ክ

 

                         

 

 በኢትዮጵያ እና በመላዉ ዓለም ለምትገኙ ሙስሊሞች እንኳን ለ 1438ኛዉ የኢድ-አል አደ(አረፋ) በዓል አላህ (.) በሰላም አደረሳችሁ እያልን መልካም ምኞታችንን ስንገልጽ በተከበረዉና በተቀደሰዉ ቦታ ላይ የሀጅ ስነ ስርዓታቸዉን እያከናወኑ የሚገኙ ሁጃጆች አላህ (.) ወደ የቤተሰቦቻቸዉ በሰላም እንዲመልሳቸዉ እና በዓለም ላይ ሰላም እንዲሰፍን ጸሎትና ምኞታችን ነዉ።

 

    በዓሉን ስናከብርም እስረኞችና ቤተሰቦቻቸዉ ፤ የቲሞችን እና የተቸገሩትን በማስታወስ አላህ (.) ከሰጠን ላይ በመስጠት ይህን የደስታ ቀን በተጎዳ ስሜት እንዳያሳልፉ መጣር ይጠበቅብናል፤ በድር ከአባሎቹና ከደጋፊዎቹ ጋር በመሆን እንደ ድርጅት በዚህ ረገድ የራሱን ድርሻ እያደረገ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን። 

 

    በድር ኢትዮጵያ በሀገራችን በሙስሊሙ ማህበረሰብ ለእምነት ነጻነት ብሎም ለህገ-መንግስታዊ መብት መረጋገጥ በሚደረገዉ ሰላማዊ መብትን የማስከበር እንቅስቃሴ  ሂደት የተጠየቁ ጥያቄዎች እስኪመለሱና በእስር ላይ የሚገኙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ጨምሮ በተያያዥነት ለእስር የተዳረጉ እህትና ወንድሞቻችን እስኪፈቱ ድረስ አጋርነቱን እንደ ከዚህ ቀደሙ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሲገልጽ በዚህ እንቅስቃሴ  ሰበብ የሞቱ ፤ የታሰሩ ፤ የተሰደዱና በተለያየ መልኩ ጉዳት የደረሰባቸዉ ወንድሞችና እህቶቻችን የከፈሉትን መስእዋትነት አላህ (.) በዱንያ ኢማንና ተቅዋን ፤በአኼራ ጀነተል ፌርዶስን እንዲለግሳቸዉ እየለመን ጭምር ነዉ።

 

   ለጋራ ግባችን መሳካትና ዉጤት ለማምጣት ያሉብንን ልዩነቶች በማጥበብ የአንድነቱን መረብ ዛሬም ኑ አብረን በጋራ እንዘርጋዉ እያልን ነዉ። ለዚህም በድር እንደ ሙስሊም ድርጅት ጠንክሮ እንደሚሰራ እየገለጽን በዓሉ የሰላም ፤ የጤና እንዲሁም መጭዉ ጊዜ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አንድነቱን አጠናክሮ ጥቅሙን ለማስጠበቅ በጋራ የሚቆምበት እንዲሆንልን አላህን እንለምናለን።

 

   በድር ኢትዮጵያ

 ኦገስት 31 ,2017