በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ    

 ለዓላማ ስኬት በጽናት እንቁም

      በሀገራችን ኢትዮጵያ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አንግቦ የተነሳዉ እምነትን በነጻነት የመተግበርና ህገመንግስታዊ መብትን ሳይሸራረፍ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ በይፋ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል። በነዚህ ወቅቶችም በርካታ ፋይዳ ያላቸዉ ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም በአንጻሩ የተከፈለዉ መስዋእትነትም የትየለሌ ነዉ። ይህም የሚያሳየዉ በትግሉ ጉዞ ዉስጥ በህዝበ ሙስሊሙም ሆነ በመሪዎች ላይ በደረሰዉ የእስር፤ የመሰደድና የድብደባ ሰቆቃ በተፈራረቀበት ወቅትም እንኳ ቢሆን ከመርሁ ሳይዛነፍ ቆይቷል።

     በድር ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የሙስሊሞች ድርጅትም ሰላማዊ እንቅስቃሴዉ ከመጀመሩ በፊትም ይሁን በኋላ አቅም በፈቀደ ሁናቴ የኡማዉ አካል በመሆን በአጋርነት ተሳትፎዋል ፤ ሰላማዊ መፍትሄ በመሻትም ሩቅ ርቀት ተጉዟል። በቅርቡ ከመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችን ‘’አቋምን በግልጽ ስለማሳወቅ በሚል የወጣዉ መግለጫም ይህንኑ የሚያስገነዝበን ሲሆን ድርጅታችንም በዚሁ በተቀየሰዉ መንገድ ሲጓዝ እንደነበር ለመግለጽ እንወዳለን።

     ህብረተሰቡም  ይህንኑ በግልጽ ተገንዝቦ ልዩነቶችን በማጥበብ እና አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር ከጅምሩ የተጠየቁ ሶስቱን መሰረታዊ የእምነት እና የመብት ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ በህዝባችን ላይ የተጋረጠዉን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ብሎም በእስር የሚማቅቁ ወንድሞቻችንን ለማስፈታት ጥረታችንን  መቀጠልና  በአዲስ መልክ በጋራ ርብርቦሽ በማድረግ የአቋም ጽናታችንን ዳግም መገንባት እንደሚጠበቅብን እናምናለን።

                                          የበድር ዳይሬክተሮች ቦርድ                                                                                                           ሰሜን አሜሪካ                                                                                                                       ኦገስት 16, 2017