ለቢቢኤን ቦርድ

ጉዳዩበኖቬምበር 6, 2016 በምታደርጉት ኮንፈረንስ ላይ እንድንገኝ የቀረበልልን ጥሪ ይመለከታል።

በመጀመሪያ በኮንፈረሳችሁ ላይ እንድንገኝ ላደረጋችሁልን ጥሪ ምሥጋናችንን ለማቅረብ  እንወዳለን።

በድር ኢትዮጵያ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ጠቀሜታና ግልጋሎት በተመለከተ  አጀንዳ አንግበው ከተነሱ ወገኖች ጋር  ተባብሮ የመሥራት ችግር እንደሌለበት ያሳለፍነው ታሪካችን ምስክር ነው። ምክኒያቱም አብሮ መስራት፤ ሕብረት መፍጠርና፤ ለአንድነት መስራት ድርጅታችን ከተመሠረተባቸው አላማዎች አንዱ ነውና። ሆኖም ግን በበድር ኢትዮጵያና በቢቢኤን  መካከል በአሁኑ ወቅት አብረው ለመሥራት የማያስችሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ከናንተም ሆነ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች  የተሰወረ አይደለም።

እንደ ሙስሊም አንድ ልብ ሆነን እንድንሰራ መጀመሪያ በወንድም ላይ ለሰራነው ዙልም አፉ ጠይቀን፤ አለኣግባብ እላፊ ለተናገርነውና ያለመረጃ ላጎደፍናቸው ስሞች፤ እንዲሁም በኮንቬንሺኖቻችን ዙሪያ ለተፈፀሙብን በደሎች ይቅርታ ተጠያይቀን በዳይ ተበዳይን ይቅርታ ጠይቆ ተበዳይም ለአላህ ሲል ይቅር ባላለበት ሁኔታ ላይ ስለምንገኝ በቅድሚያ በነዚህ ሁኔታዎች ዙሪያ ሊሠራባቸው ይገባል የሚል እምነት አለን በአንድ ልብ ሆነን ለኡማቺን እንድንሠራ ከተፈለገ ቢቢኤን በድርጅታችንና በአመራሮች ላይ ላደረሰው ሥም የማጉደፍ ዘመቻና ኦዲዮዎችን ቆርጦ በመቀጠል ላደረሰው በደል ከልብ የመነጨ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል። እንዲሁም በቢቢኤን አመራሮች እጅ የሚገኘውና፤ በኣማና ተሰጥቷቸው ግን አማና በመጣስ በጃቸው ያስቀሩትን የድርጅታችን ንብረቶች መመለስ አለባቸው።

ኢኽላስ ባለው መንገድ አብረን ለመሥራትና አብሮ የመሥራቱ ሁኔታ ቀናና ቀና እንዲሆን በቅድሚያ ይህ የኣፉታና የእርቅ ውይይት በኡለማወቻችን አማካኝነት ሊደረግ ይገባል። ይህ ሳይሆን ሆድ ሲያውቅ ደሮ ማታ እንዲሉ የውሽት ህብረትም ሆነ አንድነት እስላማዊ ያልሆነና በኢኽላስ የማይሰራ የፖሊቲካ ጠቀሜታ ብቻ መገብያ እኩይ ተግባር ስለሚሆን፤ ጥሪያችሁን የበድር አመራር ቦርድ ያልተቀበለው መሆኑንና ባዘጋጃችሁትም መድረክ የማይገኝ መሆኑን በትህትና እንገልጻለን።

 

ሁሉን አዋቂው አላህ (ሱወ) ይቅር ይበለን። ሁላችንንም ቀጥተኛውንም መንገድ ይምራን።

 

የበድር አመራር ቦርድ

 ሰሜን አሜሪካ

ኖቬምበር 5, 2016