በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ

በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተከሰተዉን የእሳት ቃጠሎ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

     ለእምነት ነጻነት ሲታገሉ የታሰሩ አያሌ ሙስሊም ወንድሞችና እህቶች፤ በርካታ የፖለቲካ መሪዎች፤ ጋዜጠኞች እንዲሁም ሌሎች ታስረዉ በሚገኙበት የቂሊንጦ እስር ቤት ተከሰተ በተባለዉ የእሳት ቃጠሎ ሳቢያ የሞቱና የተጎዱ ወገኖች መጠን ሲነገር መስማታችን በጣም አሳዝኖናል። በእስር ቤት የሚገኙ አካላት በመንግስት ጥላ ስር ያሉ እንደመሆናቸዉ መጠን ልዩ  እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግላቸዉ ሲገባ በዚህ መልኩ ህይወታቸዉ ማለፉ አጠያያቂ ጉዳይ ነዉ። በመንግስት በኩልም የተስተካከለና ግልጽነት ያለዉ ወቅታዊ የሆነ መግለጫ አለመሰጠቱም ቃጠሎዉ በአደጋ ተፈጸመ ለማለት አጠራጣሪ እንደሆነ ዜጎችና የዉጭ ታዛቢዎች አስተያየት እየሰጡበት ይገኛሉ።  

     መንግስት በማረሚያ ቤቶች ላሉ ዜጎችም ሆነ ለመላዉ ማህበረሰብ ሰላምና ጸጥታ ሀላፊነት ያለበት ሲሆን በሰዉ ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ ህይወታቸዉ ሲጠፋ ግልጽነትና ፍጥነት ባለዉ መልኩ ለዜጎች ማሳወቅ ግዴታዉ ነዉ። ከዚህም አኳያ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ ምክንያቱን በአፋጣኝ አጣርቶ  ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ ለመጠቆም እንወዳለን።  

    በድር ኢትዮጵያ ለተጎዱ ታሳሪዎችና ለሟች ቤተሰቦች መጽናናርን እየተመኘ ፤ ይህንን ጉዳይ በአንክሮ እየተከታተልን መሆኑን ለማሳወቅ እንፈልጋለን። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ነጻነት ማስከበር ሰላማዊ እንቅስቃሴ ዛሬም እንደ  ቀድሞዉ  አጋርነቱን በጽናት ሲገልጽ ለሚደረጉ የሰላማዊ ትግሉ ተኮር እንቅስቃሴዎች በማንኛዉም መልኩ ለመደገፍና የበኩሉን ድርሻ  ለመወጣት ዛሬም በዚህ ፈታኝ ወቅትም ሆነ እስከመጨረሻዉ ዝግጁ መሆኑን እንገልጻለን።

  ህዝበ ሙስሊሙም  ለታሳሪዎች እና ለቤተሰቦቻቸዉ የተለመደዉን እስላማዊ ትብብር እና እገዛዉን በማጠናከር ድጋፍ እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ ለማስታወስ እንወዳለን።

           ለእምነት ነጻነት መታገል የአላማ ጽናት ወሳኝ ነዉና በአላማችን የምንጸና አላህ ያድርገን !!!                                        

                                                                                                                                          

            በድር ኢትዮጵያ የዳይሬክተሮች ቦርድ   

        ሰሜን አሜሪካ

                                                      september 7 2016